በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አሥራ አራት

ምሕረት ስለ ማሳየት ትምህርት አግኝቷል

ምሕረት ስለ ማሳየት ትምህርት አግኝቷል

1. ዮናስ ከፊቱ ምን ዓይነት መንገድ ይጠብቀዋል? የመጨረሻ መድረሻው ስለሆነችውስ ከተማ ምን ስሜት ነበረው?

ዮናስ ስለተሰጠው ተልእኮ ማሰብ የሚችልበት ብዙ ጊዜ ነበረው። ከ800 ኪሎ ሜትር በላይ የሆነ መንገድ ከፊቱ የሚጠብቀው ሲሆን ጉዞው አንድ ወር ምናልባትም ከዚያ በላይ ሊፈጅበት ይችላል። ዮናስ በመጀመሪያ፣ አቋራጭ ከሆነው መንገድና ረጅም ቢሆንም ለአደጋ ከማያጋልጠው መንገድ አንዱን መምረጥ ይኖርበታል፤ ከዚያም በርካታ ሸለቆዎችንና ተራራማ አካባቢዎችን አቋርጦ በጽናት መጓዝ ይጠበቅበታል። ሰፊ የሆነውን የሶርያ ምድረ በዳ ዳርቻ ተከትሎ መጓዝ፣ እንደ ታላቁ ኤፍራጥስ ያሉ ወንዞችን ማቋረጥ እንዲሁም በሶርያ፣ በሜሶጶጣሚያ እና በአሶር በሚገኙ ከተሞችና መንደሮች ውስጥ ወደሚኖሩ የባዕድ አገር ሰዎች ተጠግቶ ማደር ነበረበት። ቀናት እያለፉ ሲሄዱ ዮናስ በጣም ሲፈራው ወደነበረው መድረሻው ማለትም ወደ ነነዌ ከተማ ይበልጥ እየቀረበ መጣ።

2. ዮናስ ከተሰጠው ተልእኮ መሸሽ እንደማይችል የተገነዘበው እንዴት ነው?

2 ዮናስ ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ ነው፦ ከተሰጠው ተልእኮ በምንም ዓይነት መሸሽ አይችልም። ከዚህ በፊት እንዲህ ለማድረግ ሞክሮ ነበር። ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ ባሕሩ በማዕበል እንዲናወጥ በማድረግና አንድ ትልቅ ዓሣ ተጠቅሞ በተአምር ሕይወቱን በማዳን ዮናስን በትዕግሥት አስተምሮታል። ከሦስት ቀናት በኋላ ዓሣው ዮናስን ምንም ጉዳት ሳያደርስበት ባሕሩ ዳርቻ ላይ ተፋው፤ በዚህ ጊዜ ዮናስ በተከሰተው ሁኔታ በጣም ከመደነቁም በላይ ለመታዘዝ ይበልጥ ፈቃደኛ ሆኖ ነበር።—ዮናስ ምዕራፍ 1 እና 2

3. ይሖዋ ለዮናስ የትኛውን ባሕርይ አሳይቶታል? ሆኖም የትኛው ጥያቄ ይነሳል?

3 ይሖዋ፣ ዮናስን በስተ ምሥራቅ ወደምትገኘው ወደ ነነዌ እንዲሄድ ለሁለተኛ ጊዜ ሲያዘው ነቢዩ ያለ ምንም ማቅማማት ረጅሙን ጉዞ ተያያዘው። (ዮናስ 3:1-3ን አንብብ።) ይሁን እንጂ ዮናስ፣ ይሖዋ የሰጠው ተግሣጽ ሙሉ በሙሉ ለውጥ እንዲያደርግ ረድቶት ይሆን? ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ይህን ነቢይ ባሕር ውስጥ ሰምጦ እንዳይቀር በማድረግ፣ ባመፀበት ወቅት ሳይቀጣው በማለፍ እንዲሁም የተሰጠውን ተልእኮ እንዲወጣ ሌላ ዕድል በመስጠት ምሕረት አሳይቶታል። ታዲያ ዮናስ ይህ ሁሉ ከተደረገለት በኋላ ለሌሎች ምሕረት ማሳየትን ተምሮ ይሆን? ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ምሕረት ማሳየት ይከብዳቸዋል። ዮናስ ይህንን ባሕርይ ለማዳበር ካደረገው ትግል ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ እንመልከት።

ለፍርድ መልእክቱ አስገራሚ ምላሽ ሰጡ

4, 5. ይሖዋ ነነዌን “ታላቂቱ ከተማ” ሲል የጠራት ለምንድን ነው? ይህስ ስለ እሱ ምን ያስተምረናል?

4 ዮናስ ስለ ነነዌ ከይሖዋ የተለየ አመለካከት ነበረው። መጽሐፍ ቅዱስ “በዚህ ጊዜ ነነዌ [“በአምላክ ፊት፣” NW] ታላቅ ከተማ ነበረች” ይላል። (ዮናስ 3:3) ዮናስ ባሰፈረው ዘገባ መሠረት ይሖዋ ነነዌን ሦስት ጊዜ “ታላቂቱ ከተማ” በማለት ጠርቷታል። (ዮናስ 1:2፤ 3:2፤ 4:11) ይሖዋ ይህች ከተማ ታላቅ ወይም ትልቅ ቦታ የሚሰጣት እንደሆነች የተናገረው ለምን ነበር?

5 ነነዌ፣ ከጥፋት ውኃ በኋላ ናምሩድ ከቆረቆራቸው ከተሞች አንዷ በመሆኗ ረጅም ዘመን ያስቆጠረች ጥንታዊ ከተማ ነበረች። ነነዌ እንቅስቃሴ የሚበዛባት፣ ምናልባትም በውስጧ በርካታ ከተሞችን ያቀፈች ትልቅ ከተማ ሳትሆን አትቀርም፤ ከተማዋን በእግር ከአንድ ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ ለማቋረጥ ሦስት ቀን ይፈጃል። (ዘፍ. 10:11፤ ዮናስ 3:3) ነነዌ፣ ግርማ ሞገስ የተላበሱ ግዙፍ ቤተ መቅደሶች፣ ረጃጅም ቅጥሮችና ማራኪ ሕንጻዎች ስለነበሯት በጣም አስደናቂ ከተማ ነበረች። ሆኖም ከተማዋ በይሖዋ ዘንድ ትልቅ ቦታ እንዲሰጣት ያደረጓት እነዚህ ነገሮች አይደሉም። ይሖዋ ትኩረት ያደረገው በሕዝቡ ላይ ነበር። በዚያ ዘመን ከነበሩ ሌሎች ከተሞች አንጻር ነነዌ በጣም ብዙ ሕዝብ ነበራት። ነዋሪዎቿ እጅግ ክፉ የነበሩ ቢሆንም ይሖዋ ያስብላቸው ነበር። ይሖዋ የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው እንዲሁም ማንኛውም ሰው አጋጣሚውን ቢያገኝ ንስሐ ሊገባና ትክክል የሆነውን ነገር ሊያደርግ እንደሚችል ይሰማዋል።

ዮናስ፣ ነነዌ በክፋት የተሞላች ትልቅ ከተማ መሆኗን አስተውሎ ነበር

6. (ሀ) ዮናስ ነነዌ ሲደርስ የፈራው ለምን ሊሆን ይችላል? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።) (ለ) ዮናስ የተሰጠውን የስብከት ተልእኮ ካከናወነበት መንገድ ስለ እሱ ምን እንማራለን?

6 ዮናስ ነነዌ ደርሶ ከ120,000 በላይ የሆነውን የከተማዋን ነዋሪ ሲያይ ይበልጥ ፍርሃት አድሮበት ሊሆን ይችላል። * መልእክቱን ለማሰማት የሚያስችለው ማዕከላዊ ቦታ ለማግኘት ሳይሆን አይቀርም ለአንድ ቀን ያህል በመጓዝ ሕዝብ ወደሚርመሰመስባት ወደዚህች ከተማ መሃል ገባ። ታዲያ ለእነዚህ ሰዎች መልእክቱን የሚነግራቸው እንዴት ነው? የአሦራውያንን ቋንቋ ተምሮ ይሆን? ወይስ ቋንቋውን እንዲናገር ይሖዋ ተአምራዊ ችሎታ ሰጥቶት ይሆን? ስለዚህ ጉዳይ ምንም የምናውቀው ነገር የለም። ዮናስ የአፍ መፍቻ ቋንቋው በሆነው በዕብራይስጥ መልእክቱን ከተናገረ በኋላ አንድ ሰው ለነነዌ ነዋሪዎች እንዲተረጉምላቸው አድርጎ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ፣ “ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትገለበጣለች” የሚለው ግልጽ መልእክቱ ዮናስን በነዋሪዎቹ ዘንድ የሚያስወድደው አልነበረም። (ዮናስ 3:4) መልእክቱን በድፍረትና በተደጋጋሚ ጊዜ አውጇል። በዚህም ከፍተኛ ድፍረትና እምነት እንዳለው ያሳየ ሲሆን በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖችም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እነዚህን ባሕርያት ማዳበር ያስፈልጋቸዋል።

ዮናስ ያወጀው መልእክት ግልጽ ቢሆንም በነዋሪዎቹ ዘንድ የሚያስወድደው አልነበረም

7, 8. (ሀ) የነነዌ ሰዎች ዮናስ ላወጀው መልእክት ምን ምላሽ ሰጡ? (ለ) የነነዌ ንጉሥ ዮናስ ያወጀውን መልእክት ሲሰማ ምን እርምጃ ወሰደ?

7 የነነዌ ሰዎች ለዮናስ መልእክት ጆሯቸውን ሰጡ። ዮናስ ተቃውሞና ጥላቻ እንደሚደርስበት ጠብቆ ሊሆን ይችላል። የሚገርመው ግን የሕዝቡ ምላሽ የተገላቢጦሽ ነበር። ሕዝቡ መልእክቱን አዳምጦ እርምጃ ወሰደ! መልእክቱ እንደ ሰደድ እሳት በፍጥነት ተሰራጨ። ብዙም ሳይቆይ ዮናስ የተናገረው የፍርድ መልእክት በመላው ከተማ ይወራ ጀመር። (ዮናስ 3:5ን አንብብ።) ሀብታም ድሃ፣ ብርቱ ደካማ፣ ወጣት አረጋዊ ሳይል ሁሉም ሰው ንስሐ ገባ። ሁሉም ጾሙ። ሕዝቡ የወሰደው እርምጃ ወዲያው ንጉሡ ጆሮ ደረሰ።

ዮናስ በነነዌ ከተማ ውስጥ ለመስበክ ድፍረትና እምነት አስፈልጎታል

8 ንጉሡም የዮናስን መልእክት ሲሰማ እርምጃ ወሰደ። አምላካዊ ፍርሃት ስላደረበትም ከዙፋኑ ወረደ፤ ልብሰ መንግሥቱንም አውልቆ እንደ ሕዝቡ ማቅ በመልበስ “በዐመድ ላይ ተቀመጠ።” ንጉሡ “ከመሳፍንቱ” ጋር በመሆን፣ ሕዝቡ በራስ ተነሳሽነት የጀመረው ጾም በመንግሥት ደረጃ ተፈጻሚነት እንዲኖረው የሚደነግግ አዋጅ አወጣ። ሕዝቡ ሁሉ፣ ሌላው ቀርቶ የቤት እንስሳትም እንኳ ማቅ እንዲለብሱ አዘዘ። * ከዚህም ሌላ ንጉሡ ሕዝቡ ክፉና ዓመፀኛ በመሆኑ የተነሳ በደለኛ መሆኑን በትሕትና አምኖ ተቀበለ። በተጨማሪም ‘እኛ እንዳንጠፋ አምላክ ከጽኑ ቍጣው ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?’ በማለት እውነተኛው አምላክ ንስሐ መግባታቸውን ሲመለከት ሊራራላቸው እንደሚችል ያለውን ተስፋ ገለጸ።—ዮናስ 3:6-9

9. አንዳንድ ተቺዎች የነነዌ ሰዎች የወሰዱትን እርምጃ በተመለከተ ምን ጥርጣሬ አላቸው? ሆኖም እነዚህ ተቺዎች እንደተሳሳቱ እንዴት እናውቃለን?

9 አንዳንድ ተቺዎች፣ የነነዌ ሰዎች እንዲህ በፍጥነት ልባቸው መቀየሩን መቀበል ይከብዳቸዋል። ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እንደሚገልጹት ከሆነ በአጉል እምነት በተተበተቡትና ስሜታዊ በሆኑት የጥንት ሕዝቦች ዘንድ እንዲህ ማድረግ የተለመደ ነገር ነበር። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ የነነዌ ሰዎች ንስሐ ስለ መግባታቸው መጥቀሱ እነዚህ ተቺዎች የሚሰነዝሩት ሐሳብ የተሳሳተ እንደሆነ እንድንረዳ ያስችለናል። (ማቴዎስ 12:41ን አንብብ።) ኢየሱስ እነዚህ ነገሮች ሲፈጸሙ በሰማይ ሆኖ ስለተመለከተ የተናገረው ነገር በትክክል እንደተፈጸመ አሳምሮ ያውቃል። (ዮሐ. 8:57, 58) ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ሰዎች ምንም ያህል ክፉ ቢሆኑ ንስሐ ሊገቡ አይችሉም ብለን ማሰብ የለብንም። በሰው ልብ ውስጥ ያለውን ማወቅ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው።

የአምላክ ምሕረትና ሰው የሚሰጠው ድርቅ ያለ ፍርድ

10, 11. (ሀ) ይሖዋ የነነዌ ሰዎች ንስሐ መግባታቸውን ሲያይ ምን አደረገ? (ለ) ይሖዋ ያስተላለፈው ፍርድ የተሳሳተ እንዳልነበር እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

10 ታዲያ ይሖዋ የነነዌ ሰዎች ንስሐ መግባታቸውን ሲያይ ምን አደረገ? ከጊዜ በኋላ ዮናስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እውነተኛውም አምላክ ያደረጉትን ነገር ይኸውም ከክፉ መንገዳቸው መመለሳቸውን አየ፤ በመሆኑም በእነሱ ላይ ሊያመጣ ባሰበው ጥፋት ተጸጽቶ ጥፋቱን ከማምጣት ተቆጠበ።”—ዮናስ 3:10 NW

11 ይህ ሲባል ታዲያ ይሖዋ በነነዌ ሰዎች ላይ ያስተላለፈው ፍርድ የተሳሳተ እንደነበር ተሰምቶታል ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ፍርድ ፍጹም እንደሆነ ይገልጻል። (ዘዳግም 32:4ን አንብብ።) ይሖዋ ተጸጸተ የሚለው አገላለጽ በነነዌ ሰዎች ላይ የተቆጣው የጽድቅ ቁጣ መብረዱን የሚያመለክት ነው። ሰዎቹ ያደረጉትን ለውጥ ሲመለከት ቀደም ሲል አስቦት የነበረውን የቅጣት እርምጃ አሁን በእነሱ ላይ መውሰዱ ተገቢ እንደማይሆን ተሰማው። በመሆኑም ይሖዋ ይህን አጋጣሚ ምሕረት ለማሳየት ተጠቀመበት።

12, 13. (ሀ) ይሖዋ ምክንያታዊና ከሁኔታው ጋር የሚስማማ እርምጃ የሚወስድ መሐሪ አምላክ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ዮናስ የተናገረው ትንቢት የተሳሳተ አልነበረም የምንለው ለምንድን ነው?

12 ብዙውን ጊዜ የሃይማኖት መሪዎች የሚያስተምሩት ትምህርት ሰዎች ይሖዋ ግትር፣ ርኅራኄ የሌለውና ጨካኝ አምላክ እንደሆነ እንዲሰማቸው የሚያደርግ ነው፤ ይሖዋ ግን እንዲህ ዓይነት አምላክ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ምክንያታዊና ከሁኔታዎች ጋር የሚስማማ እርምጃ የሚወስድ መሐሪ አምላክ ነው። በክፉዎች ላይ የቅጣት እርምጃ ከመውሰዱ በፊት በምድር ላይ ያሉ ወኪሎቹን በመላክ ማስጠንቀቂያ ያስነግራል፤ ይህንን የሚያደርገው ክፉ ሰዎች ልክ እንደ ነነዌ ነዋሪዎች ንስሐ ገብተው አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ ስለሚፈልግ ነው። (ሕዝ. 33:11) ይሖዋ ነቢዩ ኤርምያስን እንዲህ ብሎት ነበር፦ “አንድ ሕዝብ ወይም መንግሥት እንዲነቀል፣ እንዲፈርስና እንዲጠፋ በተናገርሁ ጊዜ፣ ያስጠነቀቅሁት ሕዝብ ከክፋቱ ቢመለስ፣ እኔ ላደርስበት ያሰብሁትን ክፉ ነገር እተዋለሁ።”—ኤር. 18:7, 8

አምላክ፣ ክፉዎች ልክ እንደ ነነዌ ሰዎች ንስሐ ገብተው አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ ይፈልጋል

13 ታዲያ ዮናስ የተናገረው ትንቢት የተሳሳተ ነበር ማለት ነው? አይደለም፤ የዚህ ትንቢት ዓላማ ሕዝቡን ማስጠንቀቅ ነበር፤ በመሆኑም የታለመለትን ግብ መቷል። ይህን ማስጠንቀቂያ መስጠት ያስፈለገው የነነዌ ሰዎች ክፉ ድርጊት ይፈጽሙ ስለነበር ነው፤ በኋላ ግን ክፉ ሥራቸውን ትተው ንስሐ ገቡ። የነነዌ ሰዎች እንደገና ወደ ክፉ ሥራቸው ቢመለሱ አምላክ የፍርድ እርምጃ ይወስድባቸዋል። ከጊዜ በኋላ የተከሰተውም ይኸው ነው።—ሶፎ. 2:13-15

14. ዮናስ ይሖዋ ለነነዌ ነዋሪዎች ምሕረት በማሳየቱ ምን ተሰማው?

14 ዮናስ እሱ ባሰበው ጊዜ ከተማዋ አለመጥፋቷን ሲመለከት ምን ተሰማው? ዘገባው “ዮናስ ግን ፈጽሞ አልተደሰተም፤ ስለዚህም ተቈጣ” ይላል። (ዮናስ 4:1) ይባስ ብሎም ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ እያረመ እንዳለ የሚያስመስል ጸሎት አቀረበ! ዮናስ እዚያው አገሩ አርፎ ቢቀመጥ ይሻለው እንደነበር ተናገረ። ነቢዩ፣ ቀድሞውንም ቢሆን ይሖዋ ነነዌን እንደማያጠፋት ያውቅ እንደነበርና ወደ ተርሴስ የሸሸውም ለዚህ እንደሆነ ገለጸ። ከዚያም በሕይወት ከመኖር መሞት እንደሚሻል በመግለጽ እንዲሞት ለመነ።—ዮናስ 4:2, 3ን አንብብ።

15. (ሀ) ዮናስን እንዲመረር ያደረገው ምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ይሖዋ በጭንቀት የተዋጠውን ነቢይ እንዴት ተመለከተው?

15 ዮናስን ያሳሰበው ምን ነበር? በወቅቱ በአእምሮው ውስጥ ይመላለስ የነበረው ነገር ምን እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ማወቅ ባንችልም ነነዌ እንደምትጠፋ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ማወጁን እናውቃለን። ሕዝቡም አምኖት ነበር። ሆኖም በከተማይቱ ላይ ምንም ጥፋት አልመጣም። ታዲያ ዮናስ፣ ሕዝቡ እንዳያፌዝበትና ሐሰተኛ ነቢይ እንደሆነ አድርጎ እንዳይመለከተው ፈርቶ ይሆን? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ዮናስ ሕዝቡ ንስሐ በመግባቱም ሆነ ይሖዋ ምሕረት በማሳየቱ አልተደሰተም። ከዚህ ይልቅ በሁኔታው እጅግ ከመመረሩም በላይ ክብሩ እንደተነካ ስለተሰማው ለራሱ ማዘን ጀመረ። ይሁን እንጂ መሐሪ የሆነው የዮናስ አምላክ፣ በዚህ ጊዜም ቢሆን ይህ በጭንቀት የተዋጠ ነቢይ ያሉትን መልካም ባሕርያት እንደተመለከተ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ይሖዋ፣ ዮናስ አክብሮት የጎደለው ነገር በመናገሩ ከመቅጣት ይልቅ “በውኑ ልትቈጣ ይገባሃልን?” በማለት ቆም ብሎ እንዲያስብ የሚያደርግ ጥያቄ በደግነት አቀረበለት። (ዮናስ 4:4) ዮናስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ሞክሮ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ምንም የሚናገረው ነገር የለም።

16. የሰዎች አስተሳሰብ ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር የማይጣጣምባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? ዮናስ ካጋጠመው ሁኔታስ ምን ልንማር እንችላለን?

16 ዮናስ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ በማሳየቱ በእሱ ላይ መፍረድ ቀላል ነው፤ ሆኖም ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች አስተሳሰብና የአምላክ አስተሳሰብ የማይጣጣሙባቸው አጋጣሚዎች ሰፊ መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች ይሖዋ አንድ አደጋ እንዳይደርስ ማድረግ ይችል እንደነበር ወይም በክፉዎች ላይ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንደነበረበት አልፎ ተርፎም ይህን ክፉ ዓለም ከዚህ ቀደም ብሎ ሊያጠፋው ይገባ እንደነበር ይሰማቸዋል። ዮናስ ያጋጠመው ሁኔታ አስተሳሰባችን ከይሖዋ አምላክ አስተሳሰብ ጋር በማይጣጣምበት ጊዜ መቼም ቢሆን ማስተካከያ ማድረግ ያለብን እኛ እንጂ እሱ አለመሆኑን ያስገነዝበናል።

ይሖዋ ዮናስን ያስተማረው እንዴት ነው?

17, 18. (ሀ) ዮናስ ነነዌን ለቆ ከወጣ በኋላ ምን አደረገ? (ለ) ይሖዋ ከቅሉ ጋር በተያያዘ የፈጸማቸው ተአምራት በዮናስ ላይ ምን ስሜት አሳደሩበት?

17 በሁኔታው የተከፋው ነቢይ ነነዌን ለቆ ወጣ፤ ከዚያም ወደ አገሩ ከመሄድ ይልቅ ከተማዋን ለማየት ወደሚያስችለው በስተ ምሥራቅ ወደሚገኝ ተራራማ ስፍራ ሄደ። በዚያም ዳስ ሠርቶ በመቀመጥ በነነዌ ላይ የሚደርሰውን ለማየት ይጠባበቅ ጀመር። አሁንም ከተማይቱ ስትጠፋ አያለሁ ብሎ ተስፋ አድርጎ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ በራሱ አመለካከት ብቻ የሚመራውን ይህን ሰው ምሕረት ማሳየት እንዲማር የሚረዳው እንዴት ይሆን?

18 ይሖዋ አንድ የቅል ተክል በአንድ ጀምበር እንዲበቅል አደረገ። ዮናስ ማለዳ ላይ ሲነሳ እሱ ከሠራት አነስተኛ ዳስ ይበልጥ ጥላ ሊሰጠው የሚችለውን ሰፋፊ ቅጠሎች ያሉትን ይህን ተክል ተመለከተ። በዚህ ጊዜ በጣም ተደሰተ። ዮናስ ቅሉ ተአምራዊ በሆነ መንገድ መብቀሉ አምላክ እንደባረከውና እንደተደሰተበት የሚያሳይ ምልክት እንደሆነ ስለተሰማው ሳይሆን አይቀርም “ስለ ቅሉ እጅግ ደስ አለው።” ሆኖም ይሖዋ ይህን ያደረገው ዮናስ ጥላ እንዲያገኝ ለማድረግና ቁጣውን ለማብረድ ብቻ አይደለም። የዮናስን ልብ የሚነካ ትምህርት ለመስጠት ፈልጎ ነበር። በመሆኑም አምላክ ሌሎች ተአምራትን ፈጸመ። አንድ ትል ተክሉን እንዲበላና እንዲያደርቀው አደረገ። ከዚያም “የሚያቃጥል የምሥራቅ ነፋስ” አመጣ፤ በዚህ ጊዜ ዮናስ ከሙቀቱ የተነሳ “ተዝለፈለፈ።” አሁንም ዮናስ መንፈሱ በጣም ስለተደቆሰ እንዲሞት አምላክን ለመነ።—ዮናስ 4:6-8

19, 20. ይሖዋ ቅሉን በተመለከተ ዮናስን በምክንያታዊነት ያስረዳው እንዴት ነው?

19 ዮናስ ቅሉ በመድረቁ የተነሳ ስለተቆጣ ይሖዋ ዮናስን “ልትቈጣ ይገባሃል?” በማለት በድጋሚ ጠየቀው። ዮናስ ስህተቱን አምኖ ከመቀበል ይልቅ “በእርግጥ እስከ ሞት ልቈጣ ይገባኛል” በማለት ድርጊቱ ትክክል እንደሆነ ተናገረ። አሁን ይሖዋ ዮናስን ሊያስተምረው የፈለገውን ቁም ነገር ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ የሚያስረዳበት ጥሩ አጋጣሚ አገኘ።—ዮናስ 4:9

አምላክ ዮናስን ምሕረት ስለ ማሳየት ለማስተማር አንድን የቅል ተክል ተጠቅሟል

20 ይሖዋ ይህ ነቢይ እሱ ያልተከለውም ሆነ ያላሳደገው በአንድ ጀምበር የበቀለ ተክል በመድረቁ ማዘኑን በመግለጽ በምክንያታዊነት ያስረዳው ጀመር። እንዲህ አለው፦ “ታዲያ እኔ ቀኝና ግራቸውን ለይተው መናገር የማይችሉ፣ ከአንድ መቶ ሃያ ሺህ በላይ ሰዎችና አያሌ እንስሶች ለሚኖሩባት ለታላቋ ከተማ ለነነዌ ማዘን አይገባኝምን?”—ዮናስ 4:10, 11 *

21. (ሀ) ይሖዋ ዮናስን ምሳሌ ተጠቅሞ ምን ትምህርት አስተማረው? (ለ) የዮናስ ታሪክ ራሳችንን በሐቀኝነት እንድንመረምር ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

21 ይሖዋ በዚህ ምሳሌ አማካኝነት ለማስተማር የፈለገውን ትልቅ ቁም ነገር አስተዋልክ? ዮናስ ያንን ተክል ለመንከባከብ ያደረገው አንዳች ነገር የለም። በሌላ በኩል ግን ይሖዋ፣ ለነነዌ ሰዎች ሕይወት ከመስጠት ባሻገር በምድር ላይ ለሚኖሩ ፍጥረታት በሙሉ እንደሚያደርገው ለእነሱም በሕይወት እንዲኖሩ የሚያስችላቸውን ነገር ሁሉ አሟልቶላቸዋል። ዮናስ 120,000 የሚሆኑት ሰዎችና እንስሶቻቸው ሕይወት ሳያሳስበው እንዴት ለአንዲት ተክል ሊቆረቆር ይችላል? እንዲህ የተሰማው የራስ ወዳድነት ዝንባሌ እንዲያድርበት ስለፈቀደ አይደለም? ደግሞም ዮናስ ለተክሉ ያዘነው ለእሱ ጥቅም ስላስገኘለት ብቻ ነው። ነነዌ ባለመጥፋቷ የተበሳጨውስ ቢሆን ቃሉ ባለመፈጸሙ ለኀፍረት እንዳይዳረግ ስለፈራ፣ በሌላ አነጋገር ራስ ወዳድ ስለነበር አይደለም? የዮናስ ታሪክ ራሳችንን በሐቀኝነት እንድንመረምር ይረዳናል። ከመካከላችን እንዲህ ዓይነቱ የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ሊያጠቃው የማይችል ማን አለ? ይሖዋ ራስ ወዳድነትን እንድናስወግድ እንዲሁም ልክ እንደ እሱ ይበልጥ ሩኅሩኆችና መሐሪዎች እንድንሆን በትዕግሥት ስለሚያስተምረን አመስጋኞች ልንሆን ይገባናል!

22. (ሀ) ዮናስ ምሕረት ማሳየትን በተመለከተ ይሖዋ ከሰጠው ጥበብ ያዘለ ትምህርት ጥቅም ያገኘው እንዴት ነው? (ለ) እኛስ ምን ትምህርት ልናገኝ ይገባናል?

22 አሁን የሚነሳው ጥያቄ፣ ‘ዮናስ ከዚህ ተሞክሮ ትምህርት አግኝቷል?’ የሚል ነው። በስሙ የተሰየመው መጽሐፍ የሚያበቃው ይሖዋ በጠየቀው ጥያቄ ሲሆን ይህ ጥያቄ እስካሁን መልስ አላገኘም። አንዳንድ ተቺዎች ዮናስ ለዚህ ጥያቄ ፈጽሞ መልስ እንዳልሰጠ ይናገሩ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን መጽሐፉ ራሱ መልስ ነው። በስሙ የተሰየመውን መጽሐፍ የጻፈው ዮናስ ራሱ መሆኑን ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። ይህ ነቢይ በሰላም ወደ አገሩ ተመልሶ ይህን ዘገባ ሲጽፍ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። አስተዋይና ትሑት የሆነ አንድ አረጋዊ ከዚህ ቀደም የሠራውን ስህተት እንዲሁም ያመፀበትንና ምሕረት ለማሳየት እምቢተኛ የነበረበትን ወቅት እያሰበ በጸጸት ጭንቅላቱን ሲነቀንቅ መመልከት ትችላለህ። ዮናስ፣ ይሖዋ ከሰጠው ጥበብ ያዘለ ትምህርት እንደተጠቀመ ግልጽ ነው። በእርግጥም ምሕረት ማሳየትን ተምሯል። እኛስ?—ማቴዎስ 5:7ን አንብብ።

^ አን.6 በዮናስ ዘመን አሥሩን ነገድ ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት ዋና ከተማ የነበረችው ሰማርያ ከ20,000 እስከ 30,000 የሚጠጋ ሕዝብ ይኖርባት እንደነበር ይገመታል፤ የነነዌ ሕዝብ ደግሞ ከዚህ አራት እጥፍ ገደማ ይበልጣል። ነነዌ በብልጽግናዋ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰችበት ወቅት በዓለም ላይ ትልቋ ከተማ ሳትሆን አትቀርም።

^ አን.8 ንጉሡ የወሰደው እንዲህ ያለው እርምጃ ያልተለመደ ነገር ሊመስል ቢችልም ከዚያ በፊት ተደርጎ የማያውቅ ነገር አይደለም። ግሪካዊው የታሪክ ምሁር ሄሮዶተስ፣ የጥንቶቹ ፋርሳውያን አንድ ተወዳጅ ጄኔራል በሞተ ጊዜ በሐዘን ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከብቶቻቸውም እንዲካፈሉ እንዳደረጉ ገልጿል።

^ አን.20 አምላክ የነነዌ ሰዎች ቀኝና ግራቸውን ለይተው መናገር እንደማይችሉ ሲገልጽ ልክ እንደ ልጆች መለኮታዊ መሥፈርቶችን ማስተዋል የማይችሉ መሆናቸውን መናገሩ ነበር።