የማቴዎስ ወንጌል 28:1-20

  • ኢየሱስ ከሞት ተነሳ (1-10)

  • ወታደሮቹ እንዲዋሹ ጉቦ ተሰጣቸው (11-15)

  • ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ተልእኮ ተሰጣቸው (16-20)

28  ከሰንበት ቀን በኋላ በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን* ጎህ ሲቀድ መግደላዊቷ ማርያምና ሌላዋ ማርያም መቃብሩን ለማየት መጡ።+  እነሆም የይሖዋ* መልአክ ከሰማይ ስለወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ተከሰተ፤ መልአኩም መጥቶ ድንጋዩን አንከባለለውና በላዩ ተቀመጠ።+  መልኩ እንደ መብረቅ ያበራ ነበር፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበር።+  ጠባቂዎቹ እሱን ከመፍራታቸው የተነሳ ተንቀጠቀጡ፤ እንደ በድንም ሆኑ።  ሆኖም መልአኩ ሴቶቹን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ፤ በእንጨት ላይ የተሰቀለውን ኢየሱስን እየፈለጋችሁ እንደሆነ አውቃለሁ።+  አስቀድሞ እንደተናገረው ከሞት ስለተነሳ እዚህ የለም።+ ኑና አስከሬኑ አርፎበት የነበረውን ስፍራ እዩ።  ስለሆነም ፈጥናችሁ ሂዱና ለደቀ መዛሙርቱ ከሞት እንደተነሳ ንገሯቸው፤ ‘እነሆ፣ ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል።+ እዚያም ታዩታላችሁ’ በሏቸው። እነሆ ነግሬአችኋለሁ።”+  ስለዚህ ሴቶቹ በፍርሃትና በታላቅ ደስታ ተውጠው ከመታሰቢያ መቃብሩ በፍጥነት በመውጣት ወሬውን ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር እየሮጡ ሄዱ።+  ወዲያውም ኢየሱስ አገኛቸውና “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። እነሱም ወደ እሱ ቀረቡና እግሩን ይዘው ሰገዱለት።* 10  ከዚያም ኢየሱስ “አትፍሩ! ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው፤ እዚያም ያዩኛል” አላቸው። 11  ሴቶቹ በመንገድ ላይ ሳሉ ከጠባቂዎቹ አንዳንዶቹ+ ወደ ከተማ ሄደው የሆነውን ነገር ሁሉ ለካህናት አለቆቹ ነገሯቸው። 12  የካህናት አለቆቹም ከሽማግሌዎቹ ጋር ተሰብስበው ከተማከሩ በኋላ ለወታደሮቹ በርከት ያሉ የብር ሳንቲሞች* በመስጠት 13  እንዲህ አሏቸው፦ “‘ሌሊት ተኝተን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው አስከሬኑን ሰረቁት’ በሉ።+ 14  አትጨነቁ፤ ወሬው ወደ አገረ ገዢው ጆሮ ከደረሰ ሁኔታውን እናስረዳዋለን።”* 15  እነሱም የብር ሳንቲሞቹን ተቀብለው እንደታዘዙት አደረጉ፤ ይህም ታሪክ እስከ ዛሬ ድረስ በአይሁዳውያን ዘንድ በስፋት ይወራል። 16  ይሁንና የኢየሱስ 11 ደቀ መዛሙርት ከእሱ ጋር ለመገናኘት በገሊላ ወደሚገኘው፣ እሱ ወደነገራቸው ተራራ ሄዱ።+ 17  ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤* አንዳንዶች ግን ተጠራጠሩ። 18  ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ አላቸው፦ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል።+ 19  ስለዚህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤+ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣+ 20  ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።+ እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ* መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ይህ ቀን በአሁኑ ጊዜ እሁድ ተብሎ የሚጠራው ቀን ነው። ለአይሁዳውያን የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ነበር።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “እጅ ነሱት።”
ብር ከተባለው ማዕድን የተሠራ ሳንቲም።
ቃል በቃል “እናሳምነዋለን።”
ወይም “እጅ ነሱት።”
ወይም “ዘመኑ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።