ምሳሌ 4:1-27

  • ጥበብ ያዘለ አባታዊ ምክር (1-27)

    • ከምንም በላይ ጥበብን አግኝ (7)

    • ከክፉ ጎዳና ራቅ (14, 15)

    • የጻድቃን መንገድ እየደመቀ ይሄዳል (18)

    • “ልብህን ጠብቅ” (23)

4  ልጆቼ ሆይ፣ የአባትን ተግሣጽ ስሙ፤+ማስተዋል እንድታገኙ በትኩረት አዳምጡ፤   ጥሩ መመሪያ እሰጣችኋለሁና፤ትምህርቴን* አትተዉ።+   እኔ ለአባቴ ጥሩ ልጅ ነበርኩ፤+እናቴም ለእኔ ልዩ ፍቅር ነበራት።+   አባቴ እንዲህ ሲል አስተማረኝ፦ “ልብህ ቃሌን አጥብቆ ይያዝ።+ ትእዛዛቴን ጠብቅ፤ በሕይወትም ትኖራለህ።+   ጥበብን አግኝ፤ ማስተዋልንም አዳብር።+ የምናገረውን ነገር አትርሳ፤ ከእሱም ፈቀቅ አትበል።   ጥበብን አትተዋት፤ እሷም ትጠብቅሃለች። ውደዳት፤ እሷም ትከልልሃለች።   ጥበብ በጣም አስፈላጊ* ነገር ናት፤+ ስለዚህ ጥበብን አግኝ፤ደግሞም ባለህ ነገር ሁሉ ማስተዋልን ለማግኘት ጥረት አድርግ።+   ለጥበብ የላቀ ዋጋ ስጥ፤ እሷም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች።+ ብታቅፋት ታከብርሃለች።+   በራስህ ላይ የሚያምር የአበባ ጉንጉን ትደፋልሃለች፤በውበት አክሊልም ታስጌጥሃለች።” 10  ልጄ ሆይ፣ አዳምጥ፤ የምናገረውንም ተቀበል፤የሕይወትህም ዘመን ይረዝማል።+ 11  በጥበብ መንገድ እንድትሄድ አስተምርሃለሁ፤+ቀና በሆነ ጎዳና እመራሃለሁ።+ 12  በምትጓዝበት ጊዜ እርምጃህ አይስተጓጎልም፤ብትሮጥም አትሰናከልም። 13  ተግሣጽን ያዛት፤ አትልቀቃትም።+ ጠብቃት፤ ሕይወትህ ናትና።+ 14  ወደ ክፉዎች መንገድ አትግባ፤በመጥፎ ሰዎች ጎዳናም አትሂድ።+ 15  ከእሱ ራቅ፤ በዚያም አትሂድ፤+ከዚያ ጎዳና ፈቀቅ በል፤ ደግሞም አልፈኸው ሂድ።+ 16  እነሱ ክፋት ካልሠሩ አይተኙምና። ሰውን ለውድቀት ካልዳረጉ እንቅልፍ በዓይናቸው አይዞርም። 17  የክፋት ምግብ ይበላሉ፤የዓመፅም ወይን ጠጅ ይጠጣሉ። 18  የጻድቃን መንገድ ግን ፍንትው ብሎ እንደሚወጣ የማለዳ ብርሃን ነው፤እንደ ቀትር ብርሃን ቦግ ብሎ እስኪበራም ድረስ እየደመቀ ይሄዳል።+ 19  የክፉዎች መንገድ እንደ ጨለማ ነው፤ምን እንደሚያሰናክላቸው አያውቁም። 20  ልጄ ሆይ፣ ቃሌን በትኩረት ተከታተል፤ንግግሬን በጥሞና አዳምጥ።* 21  ከእይታህ አይራቅ፤በልብህ ውስጥ አስቀምጠው፤+ 22  ለሚያገኙት ሕይወት ነውና፤+ለመላ አካላቸውም* ጤና ነው። 23  ከምንም ነገር በላይ ልብህን ጠብቅ፤+የሕይወት ምንጭ ከእሱ ዘንድ ነውና። 24  ጠማማ አንደበትን ከአንተ አስወግድ፤+አታላይ የሆነን ንግግርም ከአንተ አርቅ። 25  ዓይኖችህ በቀጥታ ይዩ፤አዎ፣ ፊት ለፊት በትኩረት ተመልከት።*+ 26  የእግርህን መንገድ ደልዳላ አድርግ፤*+መንገድህም ሁሉ አስተማማኝ ይሆናል። 27  ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር አትበል።+ እግርህን ከክፉ ነገር መልስ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ሕጌን።”
ወይም “ዓይነተኛ።”
ቃል በቃል “ጆሮህን ወደ ንግግሬ አዘንብል።”
ቃል በቃል “ለሥጋቸውም ሁሉ።”
ወይም “ብሩህ ዓይኖችህ ፊት ለፊት ይመልከቱ።”
“ልብ ብለህ አጢን” ማለትም ሊሆን ይችላል።