ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 8:1-39

  • በመንፈስ የሚገኝ ሕይወትና ነፃነት (1-11)

  • ‘የአምላክ ልጆች መሆናችንን መንፈሱ ይመሠክራል’ (12-17)

  • ፍጥረት የአምላክ ልጆች የሚያገኙትን ነፃነት ይጠባበቃል (18-25)

  • ‘መንፈስ ይማልድልናል’ (26, 27)

  • አምላክ አስቀድሞ የወሰናቸው (28-30)

  • በአምላክ ፍቅር አማካኝነት ድል ማድረግ (31-39)

8  ስለዚህ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ያላቸው ኩነኔ የለባቸውም።  ምክንያቱም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላላቸው ሰዎች ሕይወት የሚያስገኘው መንፈስ ሕግ፣ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነፃ አውጥቷችኋል።+  ሕጉ ከሰብዓዊ አለፍጽምና የተነሳ ደካማ በመሆኑ+ ሊፈጽመው ያልቻለውን+ ነገር አምላክ ኃጢአትን ለማስወገድ የገዛ ራሱን ልጅ ኃጢአተኛ በሆኑ ሰዎች አምሳል+ በመላክ+ ፈጽሞታል። እንዲህ በማድረግም የሥጋን ኃጢአት ኮንኗል፤  ይህም የሆነው የሕጉ የጽድቅ መሥፈርት እንደ ሥጋ ፈቃድ ሳይሆን እንደ መንፈስ ፈቃድ+ በምንመላለሰው በእኛ እንዲፈጸም ነው።+  እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ አእምሯቸው በሥጋዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው፤+ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን አእምሯቸው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው።+  በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሞት ያስከትላልና፤+ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ግን ሕይወትና ሰላም ያስገኛል፤+  ሥጋ ለአምላክ ሕግ ስለማይገዛና ደግሞም ሊገዛ ስለማይችል በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር የአምላክ ጠላት ያደርጋል።+  ስለሆነም እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚመላለሱ አምላክን ማስደሰት አይችሉም።  ይሁን እንጂ የአምላክ መንፈስ በእርግጥ በውስጣችሁ የሚኖር ከሆነ ከሥጋ ጋር ሳይሆን ከመንፈስ+ ጋር ስምም ናችሁ። ሆኖም አንድ ሰው የክርስቶስ መንፈስ ከሌለው ይህ ሰው የክርስቶስ አይደለም። 10  ይሁንና ክርስቶስ ከእናንተ ጋር አንድነት ካለው፣+ ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ቢሆንም እንኳ መንፈስ ከጽድቅ የተነሳ ሕይወት ያስገኛል። 11  እንግዲህ ኢየሱስን ከሞት ያስነሳው የአምላክ መንፈስ በእናንተ ውስጥ የሚኖር ከሆነ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሞት ያስነሳው+ እሱ በእናንተ ውስጥ በሚኖረው መንፈሱ አማካኝነት ሟች ሰውነታችሁንም ሕያው ያደርገዋል።+ 12  ስለዚህ ወንድሞች ግዴታ አለብን፤ ይሁንና ግዴታችን እንደ ሥጋ ፈቃድ መኖር አይደለም፤+ 13  እንደ ሥጋ ፈቃድ የምትኖሩ ከሆነ መሞታችሁ የማይቀር ነውና፤ ይሁን እንጂ ሰውነታችሁ የሚፈጽመውን ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ+ በሕይወት ትኖራላችሁ።+ 14  በአምላክ መንፈስ የሚመሩ ሁሉ በእርግጥ የአምላክ ልጆች ናቸውና።+ 15  ዳግመኛ ለፍርሃት የሚዳርጋችሁን የባርነት መንፈስ አልተቀበላችሁም፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ ልጆቹ አድርጎ እንዲወስዳችሁ የሚያስችል መንፈስ አግኝታችኋል፤ ይህም መንፈስ “አባ፣* አባት!”+ ብለን እንድንጣራ ይገፋፋናል። 16  የአምላክ ልጆች+ መሆናችንን ይህ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሠክራል።+ 17  እንግዲህ ልጆች ከሆን ወራሾች ነን፤ ይኸውም ከአምላክ ውርሻ እንቀበላለን፤ ይሁንና የምንወርሰው ከክርስቶስ ጋር ነው፤+ አሁን አብረነው መከራ ከተቀበልን፣+ በኋላ ደግሞ አብረነው ክብር እንጎናጸፋለን።+ 18  በአሁኑ ጊዜ የሚደርስብን መከራ በእኛ ላይ ከሚገለጠው ክብር ጋር ሲነጻጸር ከምንም ሊቆጠር እንደማይችል አምናለሁ።+ 19  ፍጥረት የአምላክን ልጆች መገለጥ በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቀ ነው።+ 20  ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቷልና፤+ የተገዛው ግን በገዛ ፈቃዱ ሳይሆን በተስፋ እንዲገዛ ባደረገው በእሱ አማካኝነት ነው፤ 21  ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከመበስበስ ባርነት ነፃ ወጥቶ+ የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት ማግኘት ነው። 22  ፍጥረት ሁሉ እስካሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በመሠቃየት ላይ እንደሚገኝ እናውቃለን። 23  ይህም ብቻ ሳይሆን የውርሻችንን በኩራት ይኸውም መንፈስን ያገኘን እኛ ራሳችንም በቤዛው አማካኝነት ከሥጋዊ አካላችን ነፃ በመውጣት አምላክ ልጆቹ አድርጎ እንዲወስደን+ በጉጉት እየተጠባበቅን በውስጣችን እንቃትታለን።+ 24  በዚህ ተስፋ ድነናል፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረገው ነገር የሚታይ ከሆነ ተስፋ መሆኑ ይቀራል፤ ደግሞስ አንድ ሰው የሚያየውን ነገር ተስፋ ያደርጋል? 25  የማናየውን ነገር+ ተስፋ የምናደርግ ከሆነ+ ግን ጸንተን በጉጉት እንጠባበቀዋለን።+ 26  በተመሳሳይም መንፈስ በድካማችን ይረዳናል።+ ምን ብለን መጸለይ እንዳለብን ግራ የምንጋባበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመንና ስሜታችንን በቃላት መግለጽ ተስኖን ስንቃትት መንፈስ ራሱ ስለ እኛ ይማልዳል። 27  ይሁንና ልብን የሚመረምረው+ አምላክ የመንፈስን ዓላማ ያውቃል፤ ምክንያቱም መንፈስ ለቅዱሳን የሚማልደው ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ነው። 28  አምላክ ለሚወዱት ይኸውም ከእሱ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ለተጠሩት ሥራውን ሁሉ አቀናጅቶ ለበጎ እንዲሆንላቸው እንደሚያደርግ እናውቃለን፤+ 29  ምክንያቱም መጀመሪያ እውቅና የሰጣቸው ሰዎች የልጁን መልክ እንዲመስሉ+ አስቀድሞ ወስኗል፤ ይኸውም ልጁ ከብዙ ወንድሞች+ መካከል በኩር+ እንዲሆን ነው። 30  ከዚህም በተጨማሪ አስቀድሞ የወሰናቸውን+ እነዚህን ጠራቸው፤+ የጠራቸውን እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው።+ በመጨረሻም ያጸደቃቸውን እነዚህን አከበራቸው።+ 31  እንግዲህ ስለ እነዚህ ነገሮች ምን እንበል? አምላክ ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ሊቃወመን ይችላል?+ 32  ለገዛ ልጁ እንኳ ያልሳሳው፣ ከዚህ ይልቅ ለእኛ ለሁላችን አሳልፎ የሰጠው+ አምላክ፣ ከእሱ ጋር አብሮ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ እንዴት በደግነት አይሰጠንም? 33  አምላክ የመረጣቸውን ማን ሊከሳቸው ይችላል?+ ምክንያቱም የሚያጸድቃቸው አምላክ ራሱ ነው።+ 34  እነሱን የሚኮንን ማን ነው? ምክንያቱም የሞተው ብሎም ከሞት የተነሳውና በአምላክ ቀኝ የተቀመጠው+ እንዲሁም ስለ እኛ የሚማልደው+ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። 35  ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል?+ መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት ወይስ ረሃብ ወይስ ራቁትነት ወይስ አደጋ ወይስ ሰይፍ?+ 36  ይህም “ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ ሞትን እንጋፈጣለን፤ እንደ እርድ በጎችም ተቆጠርን”+ ተብሎ እንደተጻፈው ነው። 37  ከዚህ ይልቅ በወደደን በእሱ አማካኝነት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ሙሉ በሙሉ በድል አድራጊነት እንወጣለን።+ 38  ምክንያቱም ሞትም ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ መንግሥታትም ቢሆኑ፣ አሁን ያሉት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ወደፊት የሚመጡት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ማንኛውም ኃይል+ ቢሆን፣ 39  ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ሌላ ማንኛውም ፍጥረት ቢሆን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ከተገለጸው የአምላክ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

“አባት ሆይ!” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ወይም የአረማይክ ቃል ነው።