ኢሳይያስ 41:1-29

  • ከፀሐይ መውጫ የመጣ ድል አድራጊ (1-7)

  • እስራኤል የአምላክ አገልጋይ እንዲሆን ተመረጠ (8-20)

    • ‘ወዳጄ አብርሃም’ (8)

  • ለአማልክት የቀረበ ፈተና (21-29)

41  “እናንተ ደሴቶች፣ ዝም ብላችሁ አዳምጡኝ፤*ብሔራትም ኃይላቸውን ያድሱ። በመጀመሪያ ይቅረቡ፤ ከዚያም ይናገሩ።+ ለፍርድ አንድ ላይ እንሰብሰብ።   ብሔራትን አሳልፎ ይሰጠውናነገሥታትን ድል ይነሳ ዘንድ+ከፀሐይ መውጫ* አንዱን ያስነሳው፣+በጽድቅ ወደ እግሩ የጠራው* ማን ነው? በሰይፉ ፊት አቧራ የሚያደርጋቸው፣በቀስቱ ፊት በነፋስ እንደተወሰደ ገለባ የሚያደርጋቸው ማን ነው?   እግሩ ባልረገጠው መንገድ በመጓዝምንም ነገር ሳያግደው እነሱን ያሳድዳል።   ይህን የሠራና ያደረገ፣ትውልዶቹንም ከመጀመሪያ አንስቶ የጠራ ማን ነው? እኔ ይሖዋ የመጀመሪያው ነኝ፤+ከመጨረሻዎቹም ጋር እኔ ያው ነኝ።”+   ደሴቶች አይተው ፈሩ። የምድር ዳርቻዎች ተንቀጠቀጡ። ቀረቡ፤ ወደ ፊትም መጡ።   እያንዳንዱም ባልንጀራውን ይረዳል፤ወንድሙንም “አይዞህ፣ በርታ” ይለዋል።   የእጅ ጥበብ ባለሙያውም አንጥረኛውን ያበረታታል፤+በመዶሻ ብረቱን የሚያሳሳውበመስፍ ላይ የሚቀጠቅጠውን ያበረታታዋል። ብየዳውን በተመለከተ “ጥሩ ነው” ይላል። ከዚያም ጣዖቱ እንዳይወድቅ አንድ ሰው በምስማር ይቸነክረዋል።   “እስራኤል ሆይ፣ አንተ ግን አገልጋዬ ነህ፤+ያዕቆብ ሆይ፣ አንተን መርጬሃለሁ፤+የወዳጄ የአብርሃም ዘር ነህ፤+   አንተን ከምድር ዳርቻዎች ወሰድኩህ፤+እጅግ ርቀው ከሚገኙ ቦታዎችም ጠራሁህ። እንዲህ ብዬሃለሁ፦ ‘አንተ አገልጋዬ ነህ፤+እኔ መርጬሃለሁ፤ ገሸሽ አላደረግኩህም።+ 10  እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ።+ እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ።+ አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ፤+በጽድቅ ቀኝ እጄ አጥብቄ እይዝሃለሁ።’ 11  እነሆ፣ በአንተ ላይ የተቆጡ ሁሉ ያፍራሉ፤ ይዋረዳሉም።+ ከአንተ ጋር የሚጣሉ ሁሉ እንዳልነበሩ ይሆናሉ፤ ይጠፋሉም።+ 12  ከአንተ ጋር የሚፋለሙትን ሰዎች ትፈልጋቸዋለህ፤ ሆኖም አታገኛቸውም፤ከአንተ ጋር የሚዋጉ ሰዎች እንደሌሉና ፈጽሞ እንዳልነበሩ ያህል ይሆናሉ።+ 13  ‘አትፍራ። እረዳሃለሁ’ የምልህእኔ፣ አምላክህ ይሖዋ ቀኝ እጅህን ይዣለሁና።+ 14  ትል* የሆንከው አንተ ያዕቆብ አትፍራ፤+እናንተ የእስራኤል ሰዎች፣ እረዳችኋለሁ” ይላል የሚቤዥህ+ የእስራኤል ቅዱስ ይሖዋ። 15  “እነሆ፣ ማሄጃ፣ በሁለቱም በኩል የተሳሉ ጥርሶች ያሉትአዲስ የመውቂያ መሣሪያ አድርጌሃለሁ።+ አንተም ተራሮቹን ረግጠህ ታደቃቸዋለህ፤ኮረብቶቹንም እንደ ገለባ ታደርጋቸዋለህ። 16  ወደ ላይ ትበትናቸዋለህ፤ነፋስም ይወስዳቸዋል፤አውሎ ነፋስ ይበትናቸዋል። በይሖዋ ደስ ይልሃል፤+በእስራኤልም ቅዱስ ትኮራለህ።”+ 17  “ችግረኞችና ድሆች ውኃ ይፈልጋሉ፤ ሆኖም አያገኙም። ከመጠማታቸው የተነሳ ምላሳቸው ደርቋል።+ እኔ ይሖዋ እመልስላቸዋለሁ።+ እኔ የእስራኤል አምላክ አልተዋቸውም።+ 18  በተራቆቱ ኮረብቶች ላይ ወንዞች እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፤+በሸለቋማ ሜዳዎች መካከል ምንጮችን አፈልቃለሁ።+ ምድረ በዳውን ቄጠማ የሞላበት ኩሬ፣ውኃ የሌለበትንም ምድር የውኃ ምንጭ አደርጋለሁ።+ 19  በበረሃ አርዘ ሊባኖስ፣ግራር፣ አደስና ዘይት የሚሰጥ ዛፍ እተክላለሁ።+ በበረሃማ ሜዳ የጥድ ዛፍ፣የአሽ ዛፍና* የፈረንጅ ጥድ በአንድነት እተክላለሁ፤+ 20  ይህም የሚሆነው የይሖዋ እጅ ይህን እንዳደረገናየእስራኤል ቅዱስ ይህን እንደፈጠረሰዎች ሁሉ እንዲያዩና እንዲያውቁ፣ልብ እንዲሉና በጥልቅ እንዲያስተውሉ ነው።”+ 21  “ሙግታችሁን አቅርቡ” ይላል ይሖዋ። “የመከራከሪያ ሐሳባችሁን አሰሙ” ይላል የያዕቆብ ንጉሥ። 22  “ማስረጃ አቅርቡ፤ እንዲሁም ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች ንገሩን። በጥሞና እንድናስብባቸውና* ፍጻሜያቸውን እንድናውቅስለቀድሞዎቹ* ነገሮች ንገሩን። ወይም የሚመጡትን ነገሮች አሳውቁን።+ 23  አማልክት መሆናችሁን እንድናውቅወደፊት የሚሆነውን ነገር ንገሩን።+ አዎ፣ አይተን በአድናቆት እንድንዋጥመልካምም ሆነ ክፉ፣ የሆነ ነገር አድርጉ።+ 24  እነሆ፣ እናንተ ጨርሶ ሕልውና የሌላችሁ ናችሁ፤ምንም የምታከናውኑት ነገር የለም።+ እናንተን የሚመርጥ ሁሉ አስጸያፊ ነው።+ 25  አንዱን ከሰሜን አስነስቻለሁ፤ እሱም ይመጣል፤+የሚመጣው ከፀሐይ መውጫ*+ ሲሆን ስሜንም ይጠራል። ጭቃውን እንደሚረግጥ ሸክላ ሠሪገዢዎችን* እንደ ሸክላ አፈር ይረግጣቸዋል።+ 26  እኛ እናውቅ ዘንድ ስለዚህ ነገር ከመጀመሪያው የተናገረወይም ‘እሱ ትክክል ነው’ እንድንል ከጥንት ጀምሮ የተናገረ ማን ነው?+ በእርግጥ የተናገረ የለም! ያሳወቀም የለም! ከእናንተ አንዳች ነገር የሰማ የለም!”+ 27  ከማንም በፊት ጽዮንን “ወደፊት የሚሆነውን ነገር ተመልከቺ!” ያልኩት እኔ ነኝ፤+ ለኢየሩሳሌምም ምሥራች ነጋሪ እልካለሁ።+ 28  ሆኖም እኔ መመልከቴን ቀጠልኩ፤ አንድም ሰው አልነበረም፤ከእነሱ መካከል ምክር የሚሰጥ አልነበረም። እኔም መልስ እንዲሰጡ መጠየቄን ቀጠልኩ። 29  እነሆ፣ ሁሉም ቅዠት* ናቸው። ሥራቸው ከንቱ ነው። ከብረት የተሠሩት ምስሎቻቸው* ነፋስና መና ናቸው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “እናንተ ደሴቶች፣ በፊቴ ዝም በሉ።”
ወይም “ከምሥራቅ።”
እሱን እንዲያገለግል የጠራው ማለት ነው።
አቅመ ቢስና ትንሽ መሆኑን ያመለክታል።
እስከ 15 ሜትር የሚደርስ ርዝመት ያለው ትልቅ ዛፍ ነው። ቅጠሎቹ ፈዘዝ ያለ አረንጓዴ ቀለም ያላቸው ሲሆን ቅርንጫፎቹ ደግሞ አመድማ መልክ አላቸው።
ወይም “ልብ እንድናደርግና።”
ቃል በቃል “ስለ መጀመሪያዎቹ።”
ወይም “ከምሥራቅ።”
ወይም “የበታች ገዢዎችን።”
ወይም “ሁሉም ሕልውና የሌላቸው ነገሮች።”
ወይም “ቀልጠው የተሠሩት ሐውልቶቻቸው።”