ኢዮብ 12:1-25

  • ኢዮብ የሰጠው መልስ (1-25)

    • “ከእናንተ አላንስም” (3)

    • “መሳለቂያ ሆኛለሁ” (4)

    • ‘በአምላክ ዘንድ ጥበብ አለ’ (13)

    • አምላክ ከፈራጆችና ከነገሥታት በላይ ነው (17, 18)

12  ከዚያም ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦   “በእርግጥ አዋቂዎች እናንተ ናችኋ!*ጥበብም ከእናንተ ጋር ትሞታለቻ!   እኔም እኮ ማስተዋል* አለኝ። ከእናንተ አላንስም። እነዚህን ነገሮች የማያውቅ ማን ነው?   ወደ አምላክ ተጣርቼ መልስ የምጠብቅ፣+የባልንጀሮቼ መሳለቂያ ሆኛለሁ።+ ጻድቅና ነቀፋ የሌለበት ሰው፣ የሰዎች መሳለቂያ ነው።   የደላው ሰው ‘መከራ የሚደርሰውእግራቸው በሚብረከረክ* ሰዎች ላይ ብቻ ነው’ ብሎ በማሰብ መከራን ይንቃል።   የዘራፊዎች ድንኳን ሰላም አለው፤+አምላክን የሚያስቆጡ ሰዎችም፣አምላካቸውን* በእጃቸው እንደያዙ ሰዎች የደህንነት ስሜት ይሰማቸዋል።+   ይሁን እንጂ እስቲ እንስሳትን ጠይቅ፤ እነሱም ያስተምሩሃል፤በሰማያት የሚበርሩ ወፎችንም ጠይቅ፤ እነሱም ይነግሩሃል።   ወይም በምድር ላይ ትኩረትህን አድርግ፤* እሷም ታስተምርሃለች፤የባሕር ዓሣም ያሳውቅሃል።   የይሖዋ እጅ ይህን ማድረጉን፣ከእነዚህ ሁሉ መካከል የማያውቅ ማን ነው? 10  የሕያው ነገር ሁሉ ሕይወት፣*የሰውም ሁሉ መንፈስ* በእሱ እጅ ነው።+ 11  ምላስ* የምግብን ጣዕም እንደሚለይ ሁሉ፣ጆሮስ ቃላትን አያመዛዝንም?+ 12  በዕድሜ በገፉት መካከል ጥበብ፣ከረጅም ዕድሜስ ጋር ማስተዋል አይገኝም?+ 13  በእሱ ዘንድ ጥበብና ኃይል አለ፤+ምክርና ማስተዋልም አለው።+ 14  እሱ ያፈረሰውን ነገር መልሶ መገንባት አይቻልም፤+እሱ የዘጋውን ማንም ሰው ሊከፍት አይችልም። 15  ውኃዎችን ሲከለክል ሁሉም ነገር ይደርቃል፤+ሲልካቸውም ምድርን ያጥለቀልቃሉ።+ 16  ብርታትና ጥበብ* በእሱ ዘንድ ናቸው፤+መንገድ የሚስተውም ሆነ የሚያስተው የእሱ ናቸው፤ 17  አማካሪዎችን ባዶ እግራቸውን ያስኬዳቸዋል፤*ፈራጆችንም ያሞኛቸዋል።+ 18  ነገሥታት ያሰሩትን ይፈታል፤+በወገባቸውም ዙሪያ መታጠቂያ ያስራል። 19  ካህናትን ባዶ እግራቸውን ያስኬዳቸዋል፤+በሥልጣን ላይ ተደላድለው የተቀመጡትንም ይገለብጣል፤+ 20  የታመኑ አማካሪዎችን የሚሉትን ነገር ያሳጣቸዋል፤ሽማግሌዎችንም ማስተዋል ይነሳል፤ 21  በታላላቅ ሰዎች ላይ የውርደት መዓት ያዘንባል፤+ብርቱዎችንም ደካማ ያደርጋል፤* 22  ጥልቅ የሆኑ ነገሮችን ከጨለማ ውስጥ ይገልጣል፤+በድቅድቅ ጨለማ ላይ ብርሃን ይፈነጥቃል፤ 23  ያጠፋቸው ዘንድ ብሔራትን ታላቅ ያደርጋል፤ወደ ግዞት ይወስዳቸውም ዘንድ ብሔራትን እንዲስፋፉ ያደርጋቸዋል። 24  የሕዝቡን መሪዎች ማስተዋል* ይነሳል፤መንገድ በሌለበት ጠፍ መሬትም እንዲቅበዘበዙ ያደርጋል።+ 25  ብርሃን በሌለበት ጨለማ፣ በዳበሳ ይሄዳሉ፤+እንደሰከሩ ሰዎች እንዲዳክሩ ያደርጋቸዋል።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ሰዎች እናንተ ናችኋ!”
ቃል በቃል “ልብ።”
ወይም “በሚያዳልጣቸው።”
ጣዖትን እንደሚያመለክት ይታመናል።
“ለምድር ተናገር” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በሕይወት ያለ ነገር ሁሉ ነፍስ።”
ወይም “እስትንፋስ።”
ቃል በቃል “ላንቃ።”
ወይም “ማስተዋል የታከለበት ጥበብ።”
ወይም “ያላቸውን ሁሉ ይገፍፋል።”
ቃል በቃል “የብርቱዎችን መታጠቂያ ያላላል።”
ቃል በቃል “ልብ።”