የሐዋርያት ሥራ 14:1-28

  • በኢቆንዮን የተገኘ እድገትና ያጋጠማቸው ተቃውሞ (1-7)

  • “አማልክት በሰው አምሳል ሆነው ወደ እኛ ወርደዋል!” (8-18)

  • ጳውሎስ በድንጋይ ቢወገርም በሕይወት ተረፈ (19, 20)

  • ጉባኤዎችን አጠናከሩ (21-23)

  • ወደ ሶርያ አንጾኪያ ተመለሱ (24-28)

14  በኢቆንዮን ጳውሎስና በርናባስ አብረው ወደ አይሁዳውያን ምኩራብ ገቡ፤ በዚያም ጥሩ ንግግር ስለሰጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዳውያንና ግሪካውያን አማኞች ሆኑ።  ሆኖም ያላመኑት አይሁዳውያን ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን ሰዎች* በማነሳሳት በወንድሞች ላይ ጥላቻ እንዲያድርባቸው አደረጉ።+  በመሆኑም ከይሖዋ* ባገኙት ሥልጣን በድፍረት እየተናገሩ በኢቆንዮን ረዘም ላለ ጊዜ ቆዩ፤ እሱም ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች በእነሱ አማካኝነት እንዲከናወኑ በማድረግ ስለ ጸጋው የሚነገረው መልእክት ትክክል መሆኑን ያረጋግጥላቸው ነበር።+  ይሁንና የከተማዋ ሕዝብ ተከፋፈለ፤ አንዳንዶቹ ከአይሁዳውያን ጎን ሲቆሙ ሌሎቹ ደግሞ ከሐዋርያት ጎን ቆሙ።  አሕዛብና አይሁዳውያን ከገዢዎቻቸው ጋር ሆነው ሊያንገላቷቸውና በድንጋይ ሊወግሯቸው በሞከሩ ጊዜ+  ጳውሎስና በርናባስ ይህን ስላወቁ ልስጥራና ደርቤ ወደሚባሉት የሊቃኦንያ ከተሞች እንዲሁም በዙሪያቸው ወዳሉት መንደሮች ሸሹ።+  በዚያም ምሥራቹን ማወጃቸውን ቀጠሉ።  በልስጥራም አንድ ሰው ተቀምጦ ነበር። እሱም ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ሽባ የነበረ ሲሆን ፈጽሞ በእግሩ ሄዶ አያውቅም።  ይህ ሰው ጳውሎስ ሲናገር ያዳምጥ ነበር። ጳውሎስም ትኩር ብሎ አየውና ለመዳን የሚያበቃ እምነት እንዳለው ተመልክቶ+ 10  ከፍ ባለ ድምፅ “ተነስና በእግርህ ቁም” አለው። ሰውየውም ዘሎ ተነሳና መራመድ ጀመረ።+ 11  ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ በሊቃኦንያ ቋንቋ “አማልክት በሰው አምሳል ሆነው ወደ እኛ ወርደዋል!” በማለት ጮኹ።+ 12  በርናባስን ዙስ፣ ጳውሎስን ደግሞ ዋና ተናጋሪ ስለነበር ሄርሜስ ብለው ይጠሯቸው ጀመር። 13  በከተማዋ መግቢያ ላይ ይገኝ የነበረው የዙስ ቤተ መቅደስ ካህን፣ ኮርማዎችና የአበባ ጉንጉን ወደ ከተማዋ መግቢያ በማምጣት ከሕዝቡ ጋር ሆኖ መሥዋዕት ሊሠዋላቸው ፈለገ። 14  ይሁን እንጂ ሐዋርያቱ በርናባስና ጳውሎስ ይህን ሲሰሙ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ሮጠውም ሕዝቡ መሃል በመግባት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፦ 15  “እናንተ ሰዎች፣ እንዲህ የምታደርጉት ለምንድን ነው? እኛም እንደ እናንተው ድክመት ያለብን ሰዎች ነን።+ ምሥራቹን እያወጅንላችሁ ያለነውም እነዚህን ከንቱ ነገሮች ትታችሁ ሰማይን፣ ምድርን፣ ባሕርንና በውስጣቸው ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠረውን ሕያው አምላክ እንድታመልኩ ነው።+ 16  ባለፉት ትውልዶች፣ ሕዝቦች ሁሉ በራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ ፈቀደላቸው፤+ 17  ይሁንና ለራሱ ምሥክር ከማቅረብ ወደኋላ አላለም፤+ ከሰማይ ዝናብ በማዝነብና ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠት+ እንዲሁም የተትረፈረፈ ምግብ በማቅረብና ልባችሁን በደስታ በመሙላት መልካም ነገር አድርጓል።”+ 18  ይህን ሁሉ ተናግረው እንኳ ሕዝቡ እንዳይሠዋላቸው ያስጣሉት በብዙ ችግር ነበር። 19  ሆኖም አይሁዳውያን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን መጥተው ሕዝቡን አግባቡ፤+ ጳውሎስንም በድንጋይ ከወገሩት በኋላ የሞተ መስሏቸው ጎትተው ከከተማዋ አወጡት።+ 20  ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በከበቡት ጊዜ ግን ተነስቶ ወደ ከተማዋ ገባ። በማግስቱም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤ ሄደ።+ 21  በዚያች ከተማ ምሥራቹን ሰብከው በርካታ ደቀ መዛሙርት ካፈሩ በኋላ ወደ ልስጥራ፣ ወደ ኢቆንዮንና ወደ አንጾኪያ ተመለሱ። 22  በዚያም “በብዙ መከራ አልፈን ወደ አምላክ መንግሥት መግባት አለብን”+ እያሉ በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ በማበረታታት ደቀ መዛሙርቱን* አጠናከሩ።+ 23  ከዚህም በተጨማሪ በየጉባኤው ሽማግሌዎችን ሾሙላቸው፤+ ከጾሙና ከጸለዩም በኋላ+ ላመኑበት ለይሖዋ* አደራ ሰጧቸው። 24  ከዚያም በጵስድያ በኩል አልፈው ወደ ጵንፍልያ+ መጡ፤ 25  በጴርጌ ቃሉን ካወጁ በኋላ ወደ አታሊያ ወረዱ። 26  ከዚያም ተነስተው በመርከብ ወደ አንጾኪያ ሄዱ፤ ጳውሎስና በርናባስ አሁን ያጠናቀቁትን ሥራ እንዲያከናውኑ ለአምላክ ጸጋ በአደራ የተሰጡት በአንጾኪያ ነበር።+ 27  እዚያም ደርሰው ጉባኤውን ከሰበሰቡ በኋላ አምላክ በእነሱ አማካኝነት ያከናወናቸውን በርካታ ነገሮች እንዲሁም ለአሕዛብ የእምነትን በር እንደከፈተላቸው ተረኩላቸው።+ 28  በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ረዘም ያለ ጊዜ አሳለፉ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን ሰዎች ነፍሳት።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “የደቀ መዛሙርቱን ነፍስ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።