የዮሐንስ ወንጌል 13:1-38

  • ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ (1-20)

  • ኢየሱስ፣ ይሁዳ ከሃዲ መሆኑን አጋለጠ (21-30)

  • አዲስ ትእዛዝ (31-35)

    • “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ” (35)

  • ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ እንደሚክደው ተናገረ (36-38)

13  የፋሲካ በዓል ተቃርቦ በነበረበት ወቅት ኢየሱስ ይህን ዓለም ትቶ ወደ አብ የሚሄድበት+ ሰዓት እንደደረሰ+ ስላወቀ በዓለም የነበሩትንና የወደዳቸውን ተከታዮቹን* እስከ መጨረሻው ወደዳቸው።+  በዚህ ጊዜ ራት እየበሉ ነበር። ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ ይሁዳ+ ልብ ውስጥ ኢየሱስን አሳልፎ የመስጠት ሐሳብ አሳድሮ ነበር።+  ኢየሱስ፣ አብ ሁሉን ነገር በእጁ እንደሰጠው እንዲሁም ከአምላክ እንደመጣና ወደ አምላክ እንደሚሄድ+ ያውቅ ስለነበር  ከራት ተነስቶ መደረቢያውን አስቀመጠ። ፎጣ ወስዶም ወገቡ ላይ አሸረጠ።+  ከዚያም በመታጠቢያ ዕቃ ውስጥ ውኃ ጨምሮ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠብና ባሸረጠው ፎጣ ማድረቅ ጀመረ።  ከዚያም ወደ ስምዖን ጴጥሮስ መጣ። ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ፣ እግሬን ልታጥብ ነው?” አለው።  ኢየሱስም መልሶ “እያደረግኩት ያለውን ነገር አሁን አትረዳውም፤ በኋላ ግን ትረዳዋለህ” አለው።  ጴጥሮስም “በፍጹም እግሬን አታጥብም” አለው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ካላጠብኩህ+ ከእኔ ጋር ምንም ድርሻ አይኖርህም” ሲል መለሰለት።  ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ፣ እግሬን ብቻ ሳይሆን እጄንና ራሴንም እጠበኝ” አለው። 10  ኢየሱስም “ገላውን የታጠበ ሁለመናው ንጹሕ በመሆኑ ከእግሩ በስተቀር መታጠብ አያስፈልገውም። እናንተ ንጹሐን ናችሁ፤ ሁላችሁም ግን አይደላችሁም” አለው። 11  ምክንያቱም አሳልፎ የሚሰጠው ሰው ማን እንደሆነ ያውቅ ነበር።+ “ሁላችሁም ንጹሐን አይደላችሁም” ያለው ለዚህ ነው። 12  እግራቸውን አጥቦ ካበቃና መደረቢያውን ለብሶ ዳግመኛ በማዕድ ከተቀመጠ በኋላ እንዲህ አላቸው፦ “ምን እንዳደረግኩላችሁ አስተዋላችሁ? 13  እናንተ ‘መምህር’ እና ‘ጌታ’ ብላችሁ ትጠሩኛላችሁ፤ እንደዚያ ስለሆንኩም እንዲህ ብላችሁ መጥራታችሁ ትክክል ነው።+ 14  ስለዚህ እኔ ጌታና መምህር ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብኩ+ እናንተም እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል።*+ 15  እኔ እንዳደረግኩላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ አርዓያ ሆኜላችኋለሁ።+ 16  እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም፤ የተላከም ከላከው አይበልጥም። 17  እነዚህን ነገሮች ስለምታውቁ ብትፈጽሟቸው ደስተኞች ናችሁ።+ 18  ይህን ስል ስለ ሁላችሁም መናገሬ አይደለም፤ የመረጥኳቸውን አውቃለሁ። ይሁንና ‘ከማዕዴ ይበላ የነበረ ተረከዙን በእኔ ላይ አነሳ’*+ የሚለው የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።+ 19  ገና ሳይፈጸም በፊት አሁን የምነግራችሁ፣ በሚፈጸምበት ጊዜ እኔ እሱ መሆኔን እንድታምኑ ነው።+ 20  እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ እኔ የምልከውን የሚቀበል ሁሉ እኔንም ይቀበላል፤+ እኔን የሚቀበል ሁሉ ደግሞ የላከኝንም ይቀበላል።”+ 21  ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ከተናገረ በኋላ መንፈሱ ተረብሾ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል”+ ሲል በግልጽ ተናገረ። 22  ደቀ መዛሙርቱም ስለ ማን እየተናገረ እንዳለ ግራ ገብቷቸው እርስ በርሳቸው ይተያዩ ጀመር።+ 23  ከእነሱ አንዱ ይኸውም ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር+ ኢየሱስ አጠገብ ጋደም ብሎ ነበር። 24  ስምዖን ጴጥሮስም ለዚህ ደቀ መዝሙር ምልክት በመስጠት “ስለ ማን እየተናገረ እንዳለ ንገረን” አለው። 25  እሱም ወደ ኢየሱስ ደረት ጠጋ ብሎ “ጌታ ሆይ፣ ማን ነው?” አለው።+ 26  ኢየሱስም “ይህን የማጠቅሰውን ቁራሽ ዳቦ የምሰጠው ሰው ነው” ሲል መለሰ።+ ከዚያም ዳቦውን አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ስምዖን ልጅ ለይሁዳ ሰጠው። 27  ይሁዳም ቁራሹን ከተቀበለ በኋላ ሰይጣን ገባበት።+ ስለዚህ ኢየሱስ “እያደረግከው ያለኸውን ነገር ቶሎ አድርገው” አለው። 28  ይሁን እንጂ በማዕድ ከተቀመጡት መካከል አንዳቸውም ለምን እንዲህ እንዳለው አልገባቸውም። 29  እንዲያውም አንዳንዶቹ ይሁዳ የገንዘብ ሣጥኑን ይይዝ ስለነበር+ ለበዓሉ የሚያስፈልጉትን ነገሮች እንዲገዛ ወይም ለድሆች የሆነ ነገር እንዲሰጥ ኢየሱስ ያዘዘው መስሏቸው ነበር። 30  ስለዚህ ይሁዳ ቁራሹን ዳቦ ከተቀበለ በኋላ ወዲያውኑ ወጣ። ጊዜውም ሌሊት ነበር።+ 31  ይሁዳ ከሄደ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “አሁን የሰው ልጅ ክብር ተጎናጸፈ፤+ አምላክም በእሱ አማካኝነት ከበረ። 32  አምላክ ራሱም ያከብረዋል፤+ ደግሞም ወዲያውኑ ያከብረዋል። 33  ልጆቼ ሆይ፣ ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ። እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁዳውያን ‘ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም’+ እንዳልኳቸው ሁሉ አሁን ደግሞ ለእናንተ ይህንኑ እላችኋለሁ። 34  እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደወደድኳችሁ+ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።+ 35  እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ+ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” 36  ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ፣ ወዴት ልትሄድ ነው?” አለው። ኢየሱስም “እኔ ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፤ በኋላ ግን ትከተለኛለህ” ሲል መለሰ።+ 37  ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ፣ አሁን ልከተልህ የማልችለው ለምንድን ነው? ሕይወቴን* ስለ አንተ አሳልፌ ለመስጠት ፈቃደኛ ነኝ” አለው።+ 38  ኢየሱስም “ሕይወትህን* ስለ እኔ አሳልፈህ ትሰጣለህ? እውነት እውነት እልሃለሁ፣ ዶሮ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ሲል መለሰ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የራሱ የሆኑትን።”
ወይም “የመተጣጠብ ግዴታ አለባችሁ።”
ወይም “በእኔ ላይ ተነሳ።”
ወይም “ነፍሴን።”
ወይም “ነፍስህን።”