ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ 7:1-40

  • ላገቡና ላላገቡ ሰዎች የተሰጠ ምክር (1-16)

  • ‘እያንዳንዱ ሰው አምላክ ሲጠራው በነበረበት ሁኔታ ይመላለስ’ (17-24)

  • ያላገቡና መበለቶች (25-40)

    • ነጠላነት ያለው ጥቅም (32-35)

    • “በጌታ ብቻ” አግቡ (39)

7  በደብዳቤያችሁ ላይ ያነሳችኋቸውን ጥያቄዎች በተመለከተ፣ አንድ ወንድ አንዲትን ሴት ባይነካ* ይሻላል፤  ይሁንና የፆታ ብልግና* ስለተስፋፋ እያንዳንዱ ወንድ የራሱ ሚስት ትኑረው፤+ እያንዳንዷም ሴት የራሷ ባል ይኑራት።+  ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፤ ሚስትም ብትሆን ለባሏ እንደዚሁ ታድርግለት።+  ሚስት በራሷ አካል ላይ ሥልጣን የላትም፤ ሥልጣን ያለው ባሏ ነው፤ በተመሳሳይም ባል በራሱ አካል ላይ ሥልጣን የለውም፤ ሥልጣን ያላት ሚስቱ ናት።  አንዳችሁ ለሌላው የሚገባውን አትከልክሉ፤ እንዲህ ማድረግ የምትችሉት በጋራ ስምምነት የተወሰነ ጊዜ ለጸሎት ለማዋል ካሰባችሁ ብቻ ነው፤ ደግሞም ራሳችሁን መግዛት አቅቷችሁ ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ እንደገና አብራችሁ ሁኑ።  ይሁን እንጂ ይህን ያልኩት እንዲህ ማድረግ እንደሚቻል ለመግለጽ ነው እንጂ ለማዘዝ አይደለም።  ይሁንና ሰው ሁሉ እንደ እኔ ቢሆን ደስ ባለኝ ነበር። ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው ከአምላክ ያገኘው የራሱ ስጦታ አለው፤+ አንዱ አንድ ዓይነት ስጦታ ሲኖረው ሌላው ደግሞ ሌላ ዓይነት ስጦታ አለው።  ሆኖም ላላገቡና መበለት ለሆኑ እንደ እኔ ሆነው ቢኖሩ የተሻለ ነው እላለሁ።+  ራሳቸውን መግዛት ካቃታቸው ግን ያግቡ፤ በፍትወት ከመቃጠል ማግባት ይሻላልና።+ 10  ላገቡት ሰዎች ይህን መመሪያ እሰጣለሁ፤ ይህ መመሪያ የጌታ እንጂ የእኔ አይደለም፤ ሚስት ከባሏ አትለያይ።+ 11  ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባሏ ጋር ትታረቅ፤ ባልም ሚስቱን መተው የለበትም።+ 12  ለሌሎች ደግሞ እንዲህ እላለሁ፤ ይህን የምለው እኔ እንጂ ጌታ አይደለም፦+ አንድ ወንድም አማኝ ያልሆነች ሚስት ካለችውና አብራው ለመኖር ከተስማማች አይተዋት፤ 13  እንዲሁም አንዲት ሴት አማኝ ያልሆነ ባል ካላትና ባሏ አብሯት ለመኖር ከተስማማ አትተወው። 14  አማኝ ያልሆነ ባል ከሚስቱ ጋር ባለው ዝምድና የተነሳ ተቀድሷልና፤ አማኝ ያልሆነች ሚስትም ከወንድም ጋር ባላት ዝምድና የተነሳ ተቀድሳለች፤ እንዲህ ባይሆን ኖሮ ልጆቻችሁ ርኩሳን በሆኑ ነበር፤ አሁን ግን ቅዱሳን ናቸው። 15  ይሁንና አማኝ ያልሆነው ወገን ለመለየት ከመረጠ ይለይ፤ እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ምንም ዓይነት ግዴታ የለባቸውም፤ አምላክ የጠራችሁ ለሰላም ነውና።+ 16  አንቺ ሚስት፣ ባልሽን ታድኚው እንደሆነ ምን ታውቂያለሽ?+ ወይስ አንተ ባል፣ ሚስትህን ታድን እንደሆነ ምን ታውቃለህ? 17  ያም ሆነ ይህ እያንዳንዱ ሰው ይሖዋ* በሰጠው ድርሻና አምላክ ሲጠራው በነበረበት ሁኔታ ይመላለስ።+ ለጉባኤዎችም ሁሉ ይህን መመሪያ እሰጣለሁ። 18  አንድ ሰው የተጠራው ተገርዞ እያለ ነው?+ እንዳልተገረዘ ሰው አይሁን። አንድ ሰው የተጠራው ሳይገረዝ ነው? ከሆነ አይገረዝ።+ 19  መገረዝ ምንም ማለት አይደለም፤ አለመገረዝም ቢሆን ምንም ማለት አይደለም፤+ ዋናው ነገር የአምላክን ትእዛዛት መጠበቅ ነው።+ 20  እያንዳንዱ ሰው በተጠራበት ጊዜ የነበረበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን በዚያው ይቀጥል።+ 21  የተጠራኸው ባሪያ እያለህ ነው? ይሄ አያስጨንቅህ፤+ ሆኖም ነፃ መውጣት የምትችል ከሆነ አጋጣሚውን ተጠቀምበት። 22  ባሪያ እያለ የተጠራ ማንኛውም የጌታ ደቀ መዝሙር ነፃ የወጣ የጌታ ሰው ነውና፤+ በተመሳሳይም ነፃ እያለ የተጠራ ሰው የክርስቶስ ባሪያ ነው። 23  በዋጋ ተገዝታችኋል፤+ የሰው ባሪያ መሆናችሁ ይብቃ። 24  ወንድሞች፣ እያንዳንዱ ሰው በተጠራበት ጊዜ የነበረበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን በአምላክ ፊት በዚያው ሁኔታ ይቀጥል። 25  ድንግል የሆኑትን* በተመለከተ ከጌታ የተቀበልኩት ትእዛዝ የለኝም፤ ይሁን እንጂ ጌታ ካሳየኝ ምሕረት የተነሳ እንደ ታማኝ ሰው የራሴን ሐሳብ እሰጣለሁ።+ 26  ስለዚህ አሁን ካለው ችግር አንጻር አንድ ሰው ባለበት ሁኔታ ቢቀጥል የተሻለ ይመስለኛል። 27  በሚስት ታስረሃል? ከሆነ መፈታትን አትሻ።+ ሚስት የሌለህ ነህ? ከሆነ ሚስት ለማግባት አትፈልግ። 28  ይሁንና ብታገባም ኃጢአት ይሆንብሃል ማለት አይደለም። እንዲሁም ድንግል የሆነ ሰው ቢያገባ ኃጢአት ይሆንበታል ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ የሚያገቡ ሰዎች በሥጋቸው ላይ መከራ ይደርስባቸዋል። ነገር ግን የእኔ ምኞት ከዚህ እንድትድኑ ነው። 29  ከዚህም በላይ ወንድሞች፣ የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን ልነግራችሁ እወዳለሁ።+ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስት ያላቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፤ 30  የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፣ የሚደሰቱም እንደማይደሰቱ፣ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው 31  እንዲሁም በዓለም የሚጠቀሙ ሰዎች ሙሉ በሙሉ እንደማይጠቀሙበት ይሁኑ፤ የዚህ ዓለም ትእይንት እየተለዋወጠ ነውና። 32  በመሆኑም ከጭንቀት ነፃ እንድትሆኑ እፈልጋለሁ። ያላገባ ሰው ጌታን እንዴት ደስ ማሰኘት እንደሚችል በማሰብ ስለ ጌታ ነገር ይጨነቃል። 33  ያገባ ሰው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ ማሰኘት እንደሚችል በማሰብ ስለ ዓለም ነገር ይጨነቃል፤+ 34  በመሆኑም ሐሳቡ ተከፋፍሏል። በተጨማሪም ያላገባች ሴትም ሆነች ድንግል በአካሏም ሆነ በመንፈሷ ቅዱስ መሆን ትችል ዘንድ ስለ ጌታ ነገር ትጨነቃለች።+ ይሁን እንጂ ያገባች ሴት ባሏን እንዴት ደስ ማሰኘት እንደምትችል በማሰብ ስለ ዓለም ነገር ትጨነቃለች። 35  ይህን የምለው ግን ለእናንተው ጥቅም ብዬ ነው እንጂ ነፃነት ላሳጣችሁ* ብዬ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ተስማሚ የሆነውን ነገር እንድታደርጉና ሐሳባችሁ ሳይከፋፈል ዘወትር ለጌታ ያደራችሁ እንድትሆኑ ላነሳሳችሁ ብዬ ነው። 36  ይሁንና አንድ ሰው ሳያገባ ቀርቶ ራሱን መቆጣጠር* እንደተሳነው ከተሰማው፣ በተለይ ደግሞ አፍላ የጉርምስና ዕድሜን ያለፈ ከሆነና ማግባቱ የሚመረጥ ከሆነ የፈለገውን ያድርግ፤ ኃጢአት አይሆንበትም። እንዲህ ያሉ ሰዎች ያግቡ።+ 37  ሆኖም አንድ ሰው ልቡ ከቆረጠና ይህን ማድረግ እንደማያስፈልገው ከተሰማው፣ ደግሞም ራሱን መግዛት የሚችል ከሆነና ሳያገባ* ለመኖር በልቡ ከወሰነ መልካም ያደርጋል።+ 38  ስለዚህ የሚያገባ* ሁሉ መልካም ያደርጋል፤ ሳያገባ የሚኖር ሁሉ ደግሞ የተሻለ ያደርጋል።+ 39  አንዲት ሚስት ባሏ በሕይወት ባለበት ዘመን ሁሉ የታሰረች ናት።+ ባሏ በሞት ካንቀላፋ ግን በጌታ ብቻ ይሁን እንጂ ከፈለገችው ሰው ጋር ለመጋባት ነፃ ናት።+ 40  እንደ እኔ ከሆነ ግን እንዳለች ብትቀጥል ይበልጥ ደስተኛ ትሆናለች፤ እኔ ደግሞ የአምላክ መንፈስ እንዳለኝ እርግጠኛ ነኝ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

በፆታ ስሜት መንካትን ያመለክታል።
ፖርኒያ የተባለው ግሪክኛ ቃል ብዙ ቁጥር። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “አግብተው የማያውቁትን።”
ቃል በቃል “ማነቆ ውስጥ ላስገባችሁ።”
ወይም “ከድንግልናው ጋር በሚስማማ ሁኔታ በአግባቡ መኖር።”
ወይም “ድንግልናውን ጠብቆ።”
ወይም “ድንግልናውን በጋብቻ የሚሰጥ።”