ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ 1:1-24

  • ሰላምታ (1, 2)

  • አምላክ በመከራ ሁሉ ያጽናናናል (3-11)

  • ጳውሎስ የጉዞ ዕቅዱን ለወጠ (12-24)

1  በአምላክ ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፣+ በቆሮንቶስ ለሚገኘው የአምላክ ጉባኤ እንዲሁም በመላው አካይያ+ ለሚኖሩ ቅዱሳን ሁሉ፦  አባታችን ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።  የምሕረት* አባትና+ የመጽናናት+ ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት+ ይወደስ፤  እኛ ከአምላክ በምናገኘው መጽናኛ+ በማንኛውም ዓይነት መከራ* ውስጥ ያሉትን ሰዎች ማጽናናት እንድንችል+ እሱ በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል።*+  ስለ ክርስቶስ ብለን የምንቀበለው መከራ ብዙ እንደሆነ ሁሉ+ በክርስቶስ በኩል የምናገኘው መጽናኛም የዚያኑ ያህል ብዙ ነው።  ስለዚህ እኛ መከራ ቢደርስብን ለእናንተ መጽናኛና መዳን ያስገኛል፤ መጽናኛ ብናገኝ ደግሞ በእኛ ላይ የደረሰው መከራ በእናንተም ላይ ሲደርስ እንድትጸኑ የሚረዳ መጽናኛ ይሆንላችኋል።  እናንተን በተመለከተ ያለን ተስፋ የማይናወጥ ነው፤ ይህም የሆነው መከራውን ከእኛ ጋር እንደምትካፈሉ ሁሉ መጽናኛውንም እንደምትካፈሉ ስለምናውቅ ነው።+  ወንድሞች፣ በእስያ አውራጃ ስለደረሰብን መከራ እንድታውቁ እንፈልጋለን።+ ከአቅማችን በላይ የሆነ ከባድ ጫና ደርሶብን ስለነበር በሕይወት የመትረፍ ተስፋችን እንኳ ተሟጦ ነበር።+  እንዲያውም የሞት ፍርድ ተፈርዶብናል የሚል ስሜት አድሮብን ነበር። ይህ የሆነው ግን በራሳችን ሳይሆን ሙታንን በሚያስነሳው አምላክ እንድንታመን ነው።+ 10  እሱ እንዲህ ካለ ለሞት ሊዳርግ የሚችል አደገኛ ሁኔታ አድኖናል፤ ደግሞም ያድነናል፤ ወደፊትም እንደሚያድነን በእሱ ተስፋ እናደርጋለን።+ 11  እናንተም ስለ እኛ ምልጃ በማቅረብ ልትረዱን ትችላላችሁ።+ ይህን ማድረጋችሁ ብዙዎች በሚያቀርቡት ጸሎት የተነሳ ለሚደረግልን ቸርነት ብዙዎች ስለ እኛ የምስጋና ጸሎት እንዲያቀርቡ ያነሳሳቸዋል።+ 12  የምንኮራበት ነገር ይህ ነው፦ በዓለም ውስጥ በተለይም በእናንተ መካከል በቅድስናና አምላካዊ ቅንነት በማሳየት እንደኖርን ሕሊናችን ይመሠክራል፤ ይህን ያደረግነው በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን+ በአምላክ ጸጋ ነው። 13  ልታነብቡትና* ልትረዱት ከምትችሉት በቀር ስለ ሌላ ነገር አንጽፍላችሁም፤ ይህን ነገር በተሟላ ሁኔታ* መረዳታችሁን እንደምትቀጥሉ ተስፋ አደርጋለሁ፤ 14  አንዳንዶቻችሁ በእኛ መኩራት እንደምትችሉ እንደተገነዘባችሁ ሁሉ እኛም በጌታችን በኢየሱስ ቀን በእናንተ እንኮራለን። 15  በመሆኑም በዚህ በመተማመን ዳግመኛ እንድትደሰቱ* በመጀመሪያ ወደ እናንተ ለመምጣት አቅጄ ነበር፤ 16  ወደ መቄዶንያ ስሄድ እግረ መንገዴን እናንተን ለማየት፣ ከዚያም ከመቄዶንያ ተመልሼ ከእናንተ ጋር ለመገናኘትና ወደ ይሁዳ እንድትሸኙኝ ለማድረግ አስቤ ነበር።+ 17  እንዲህ ዓይነት ዕቅድ አውጥቼ የነበረው እንዲሁ ሳላስብበት ይመስላችኋል? ወይስ ማንኛውንም ነገር ሳቅድ በሥጋዊ አስተሳሰብ ተነድቼ በማቀድ አንዴ “አዎ፣ አዎ” ከዚያ ደግሞ “አይሆንም፣ አይሆንም” የምል ይመስላችኋል? 18  አምላክ እምነት የሚጣልበት እንደመሆኑ መጠን እኛ ለእናንተ የምንናገረውም ነገር እውነት ነው። መጀመሪያ ላይ “አዎ” ብለን ከዚያ ደግሞ “አይሆንም” አንልም። 19  ምክንያቱም እኛ ማለትም እኔ፣ ስልዋኖስና* ጢሞቴዎስ+ የሰበክንላችሁ የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ “አዎ” ሆኖ እያለ “አይደለም” ሊሆን አይችልም፤ ከዚህ ይልቅ ከእሱ ጋር በተያያዘ “አዎ” የተባለው “አዎ” ሆኗል። 20  አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች የቱንም ያህል ብዙ ቢሆኑም በእሱ አማካኝነት “አዎ” ሆነዋል።+ ስለዚህ እኛ ለአምላክ ክብር እንድንሰጥ በእሱ አማካኝነት ለአምላክ “አሜን” እንላለን።+ 21  ይሁንና እኛም ሆን እናንተ የክርስቶስ ለመሆናችን ዋስትና የሰጠንና የቀባን አምላክ ነው።+ 22  በተጨማሪም በማኅተሙ ያተመን+ ሲሆን ወደፊት ለሚመጣውም ነገር ማረጋገጫ* ሰጥቶናል፤ ይህም በልባችን ውስጥ ያለው መንፈስ ነው።+ 23  ወደ ቆሮንቶስ እስካሁን ያልመጣሁት ለባሰ ሐዘን እንዳልዳርጋችሁ ብዬ ነው፤ ይህ እውነት ካልሆነ አምላክ በእኔ* ላይ ይመሥክርብኝ። 24  ጸንታችሁ የቆማችሁት በራሳችሁ እምነት ስለሆነ እኛ ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን እንጂ በእምነታችሁ ላይ የምናዝ አይደለንም።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ከርኅራኄ የመነጨ ምሕረት።”
ወይም “ፈተና።”
ወይም “ያበረታታናል።”
“አስቀድማችሁ በሚገባ ከምታውቁትና” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “እስከ መጨረሻው።”
“ሁለት ጊዜ መጠቀም እንድትችሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ሲላስ ተብሎም ይጠራል።
ወይም “ቀብድ፤ ወደፊት ለሚመጣው ነገር ዋስትና (መያዣ)።”
ወይም “በነፍሴ።”