በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእምነታቸው ምሰሏቸው | ርብቃ

“አዎ፣ እሄዳለሁ”

“አዎ፣ እሄዳለሁ”

ርብቃ ጀንበሯ እያዘቀዘቀች ስትሄድ ወጣ ገባ የሆነውን መልክዓ ምድር አሻግራ ተመለከተች። ለበርካታ ሳምንታት ስትጓዝ ከቆየች በኋላ ግመል ላይ ተቀምጦ ወዲያ ወዲህ መንገላታቱን ተላምዳዋለች። የልጅነት ሕይወቷን ካሳለፈችበት በስተ ሰሜን ምሥራቅ ከሚገኘው ከካራን ብዙ መቶ ኪሎ ሜትሮች ርቃ ተጉዛለች። ቤተሰቧን ዳግመኛ ላታያቸው ትችላለች። የወደፊት ሕይወቷን በተመለከተ በአእምሮዋ ውስጥ የሚጉላሉ ብዙ ጥያቄዎች እንደሚኖሩ ግልጽ ነው፤ በተለይ ጉዞው እየተገባደደ ሲመጣ ይህ መሆኑ የሚጠበቅ ነው።

መደዳውን የሚጓዙት ግመሎች አብዛኛውን የከነዓን ምድር አልፈው እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን የኔጌብን ምድር እያቋረጡ ነው። (ዘፍጥረት 24:62) በዚህ ቦታ ርብቃ በጎች አይታ ሊሆን ይችላል። ምድሩ መጠነ ሰፊ የሆነ የግብርና ሥራ ለማካሄድ የማይመች በጣም ጠፍና በረሃ ሊሆን ቢችልም ለግጦሽ የሚሆን በቂ መስክ አለው። መንገዱን እየመራ ያለው አረጋዊ ሰው ቦታውን በደንብ ያውቀዋል። ለጌታው ምሥራች ለማብሰር ይኸውም ርብቃን ይዞለት እንደመጣ ሊነግረው ጓጉቷል! ርብቃ ግን በዚህ አገር ሕይወቷ ምን ሊመስል እንደሚችል ማሰቧ አይቀርም። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የምታገባው ይስሐቅ ምን ዓይነት ሰው ይሆን? የሚገርመው፣ ከዚህ በፊት ተያይተው እንኳ አያውቁም! እሷን ሲያያት ይደሰት ይሆን? እሷስ ስታየው ምን ይሰማታል?

በዛሬው ጊዜ በአብዛኛው የምድር ክፍል በሌሎች ምርጫ የሚካሄድ ጋብቻ ያልተለመደ ነገር ነው። በአንዳንድ አገሮች ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ ጋብቻ ተቀባይነት አለው። አንተ በምትኖርበት አገር ያለው ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ርብቃ ከፊቷ ምን እንደሚጠብቃት አታውቅም ቢባል ሳትስማማ አትቀርም። እውነቱን ለመናገር፣ ርብቃ አስደናቂ ድፍረትና እምነት ያላት ሴት ነች። እኛም በሕይወታችን ውስጥ ለውጦች ሲያጋጥሙን ድፍረትና እምነት ማሳየት ያስፈልገናል። ርብቃ ካሳየችው እምነት ጋር የሚያያዙ ሌሎች ግሩምና ብርቅዬ ባሕርያትም አሉ።

‘ለግመሎችህም ውኃ እቀዳላቸዋለሁ’

ርብቃ በሕይወቷ ያጋጠማት ትልቅ ለውጥ የመጣው ምንም ሳትዘጋጅበት ነው ሊባል ይችላል። ያደገችው በሜሶጶጣሚያ በምትገኘው በካራን ከተማ አሊያም በአቅራቢያዋ ነበር። ወላጆቿ በካራን ከሚኖሩት አብዛኞቹ ሰዎች የተለዩ ናቸው። የጨረቃ አምላክ የሆነውን ሲንን አያመልኩም። ከዚህ ይልቅ የሚያመልኩት ይሖዋን ነው።—ዘፍጥረት 24:50

ርብቃ እጅግ ውብ ወጣት ናት፤ ይሁንና እንዲሁ ውበት ያደላት ሴት ብቻ አይደለችም። ሥራ ወዳድ ሴት ነች፤ ደግሞም የሥነ ምግባር ንጽሕናዋን ጠብቃ ኖራለች። ቤተሰቦቿ አገልጋዮች መቅጠር የሚያስችል ሀብት ነበራቸው። ይሁን እንጂ ርብቃን አሞላቅቀው አላሳደጓትም ወይም እንደ ልዕልት አልቆጠሯትም፤ ያሳደጓት ትጉ ሠራተኛ እንድትሆን አድርገው ነው። በዚያን ዘመን እንደነበሩት እንደ አብዛኞቹ ሴቶች ሁሉ ርብቃም አድካሚ ሥራ ታከናውን ነበር፤ ለምሳሌ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ውኃ ቀድታ ታመጣለች። ጥላ በረድ ሲል እንስራዋን በትከሻዋ ተሸክማ ወደ ምንጩ ታመራለች።—ዘፍጥረት 24:11, 15, 16

አንድ ቀን አመሻሹ ላይ እንስራዋን ውኃ ከሞላች በኋላ አንድ አረጋዊ ወደ እሷ እየሮጠ መጥቶ “እባክሽ ከእንስራሽ ውኃ ልጎንጭ” አላት። ሰውየው ቀላል ነገር ነው የጠየቃት፤ ያውም በአክብሮት! ርብቃ፣ ሰውየው ብዙ መንገድ ተጉዞ እንደመጣ መረዳት ችላለች። በመሆኑም እንስራዋን በፍጥነት ከትከሻዋ ላይ አውርዳ እንዲያው ፉት እንዲል ሳይሆን እስኪረካ ድረስ የሚጠጣው ቀዝቀዝ ያለ ንጹሕ ውኃ ሰጠችው። እዚያው አካባቢ በርከክ ያሉ አሥር ግመሎች እንዳሉት ሆኖም እነሱ የሚጠጡት ውኃ ገንዳው ውስጥ አለመሞላቱን አየች። ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ዓይኖቹ በትኩረት እንደሚከታተሏት ገብቷታል፤ በመሆኑም አቅሟ በሚፈቅደው መጠን ሰውየውን ልትረዳው ፈልጋለች። ከዚያም “ግመሎችህም ጠጥተው እስኪጠግቡ ድረስ ውኃ እቀዳላቸዋለሁ” አለችው።—ዘፍጥረት 24:17-19

ርብቃ ለአሥሩ ግመሎች ውኃ ለመስጠት ሐሳብ ያቀረበችው ጠጥተው እስኪረኩ ድረስ እንጂ እንዲቃመሱ ያህል ብቻ አለመሆኑን ልብ በል። ውኃ የጠማው አንድ ግመል ከ95 ሊትር በላይ ውኃ ሊጠጣ ይችላል! አሥሩም ግመሎች በጣም ጠምቷቸው ከነበረ ርብቃ ብዙ ሰዓት የሚፈጅ አድካሚ ሥራ ይጠብቃታል ማለት ነው። የተፈጸመውን ሁኔታ ስናስብ ግመሎቹ በጣም ተጠምተው ነበር ለማለት አያስደፍርም። * ይሁንና ርብቃ ግመሎቹን ለማጠጣት ሐሳብ ስታቀርብ ይህን ታውቅ ነበር? በጭራሽ። ለአካባቢው ባይተዋር ለሆነው ለዚህ አረጋዊ ሰው፣ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ለማሳየት ስትል ጉልበቷን ሳትቆጥብ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኝነቱም ሆነ ጉጉቱ ነበራት። እሱም በሐሳቧ ተስማማ። ከዚያም እንስራዋን ለመሙላት እየተመላለሰች ገንዳው ውስጥ ውኃ ደጋግማ ስትገለብጥ በመገረም ይመለከታት ነበር።—ዘፍጥረት 24:20, 21

ርብቃ ታታሪና እንግዳ ተቀባይ ነበረች

ርብቃ ከተወችው ምሳሌ ብዙ ቁም ነገሮች ማግኘት እንችላለን። የምንኖረው ራስ ወዳድነት እጅግ በገነነበት ዘመን ላይ ነው። “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ” እንደሚሆኑ፣ ማለትም ሌሎችን የሚጠቅም ነገር ለማድረግ ምንም ፈቅ እንደማይሉ ትንቢት ተነግሮ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ተጽዕኖ እንዳያሳድርባቸው የሚፈልጉ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ ዘመናት በፊት ስለኖረችውና ወደ ጉድጓዱ በፍጥነት እየተመላለሰች ውኃ ስለቀዳችው ስለዚያች ወጣት በያዘው ዘገባ ላይ ማሰላሰላቸው ተገቢ ነው።

ርብቃ አረጋዊው ሰው ትክ ብሎ እያያት መሆኑን እንደምታስተውል ግልጽ ነው። እርግጥ እንደዚያ ያያት የነበረው በመጥፎ ዓላማ አይደለም፤ አስተያየቱ መገረሙን፣ መደነቁንና መደሰቱን ይጠቁማል። ርብቃ ሥራውን ስትጨርስ ሰውየው ውድ ጌጣ ጌጦች በስጦታ አበረከተላት! ከዚያም “እስቲ ንገሪኝ፣ ለመሆኑ የማን ልጅ ነሽ? በአባትሽ ቤት የምናድርበት ቦታ ይኖር ይሆን?” ሲል ጠየቃት። ቤተሰቦቿ እነማን እንደሆኑ ስትነግረው ደስታው ወደር አልነበረውም። ርብቃ በደስታ ከመፈንደቋ የተነሳ ሳይሆን አይቀርም “ገለባና ብዙ ገፈራ እንዲሁም ለማደሪያ የሚሆን ስፍራ አለን” በማለት አክላ ተናገረች። ከአረጋዊው ሰው ጋር የሚጓዙ ሌሎች ሰዎችም ስላሉ ይህ ብዙ ወጪ የሚያስወጣ ግብዣ ነው። ከዚያም ያጋጠማትን ነገር ለእናቷ ለመንገር ሰውየውን ጥላው እየሮጠች ሄደች።—ዘፍጥረት 24:22-28, 32

ወላጆቿ፣ ርብቃን እንግዳ ተቀባይ አድርገው እንዳሳደጓት በግልጽ መረዳት ይቻላል። በዛሬው ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ እሴት እየጠፋ የመጣ ይመስላል፤ ይህም ይህችን ደግ ወጣት በእምነቷ እንድንመስላት የሚያነሳሳን ተጨማሪ ምክንያት ነው። በአምላክ ላይ ያለን እምነት እንግዳ ተቀባዮች እንድንሆን ሊያነሳሳን ይገባል። ይሖዋ ለሰው ሁሉ ደግነት ስለሚያሳይ እንግዳ ተቀባይ አምላክ ነው ሊባል ይችላል፤ አገልጋዮቹ ደግሞ በዚህ ረገድ እሱን እንዲመስሉ ይፈልጋል። አንዳች ብድራት ለማይመልሱልን ሰዎች ጭምር የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየታችን በሰማይ የሚኖረው አባታችንን ያስደስተዋል።—ማቴዎስ 5:44-46፤ 1 ጴጥሮስ 4:9

“ለልጄ ሚስት አምጣለት”

የውኃው ጉድጓድ ጋ የነበረው ያ አረጋዊ ማን ነው? የርብቃ አያት ወንድም የሆነው የአብርሃም አገልጋይ ነው። በመሆኑም የርብቃ አባት በሆነው በባቱኤል ቤት ጥሩ አቀባበል ተደረገለት። ይህ አገልጋይ ኤሊዔዘር * ሳይሆን አይቀርም። አስተናጋጆቹ ምግብ እንዲበላ አቀረቡለት፤ እሱ ግን የመጣበትን ጉዳይ ሳይናገር ምግብ እንደማይቀምስ ገለጸ። (ዘፍጥረት 24:31-33) ይህን ወሳኝ የሆነ ተልእኮ አምላኩ ይሖዋ እያሳካለት መሆኑን የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ከጥቂት ጊዜ በፊት በማየቱ ስለ ሁኔታው በደስታ ሲናገር በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ለመሆኑ የተፈጸመው ነገር ምን ነበር?

ኤልዔዘር ያጋጠመውን ሁኔታ በሚናገርበት ጊዜ የርብቃ አባት ባቱኤልና ወንድሟ ላባ በጥሞና ሲያዳምጡት ይታይህ። ይሖዋ አብርሃምን በከነአን ምድር እጅግ እንደባረከው እንዲሁም አብርሃምና ሣራ፣ ርስቱን በአጠቃላይ የሚወርስ ይስሐቅ የሚባል ልጅ እንደወለዱ ነገራቸው። አብርሃም ለዚህ አገልጋዩ አንድ ከባድ ተልዕኮ ሰጥቶታል፦ በካራን ከሚኖሩት የአብርሃም ዘመዶች መካከል ለይስሐቅ ሚስት የማምጣት ኃላፊነት ተጥሎበት ነበር።—ዘፍጥረት 24:34-38

አብርሃም በከነአን ከሚኖሩ ሴቶች መካከል ለልጁ ለይስሐቅ ሚስት እንዳይመርጥ ኤልዔዘርን በመሐላ ቃል አስገብቶታል። ለምን? ምክንያቱም ከነአናውያን ለይሖዋ አምላክ አክብሮት የላቸውም፤ እሱንም አያመልኩም። ይሖዋ፣ የምድሪቱ ነዋሪዎች በሚፈጽሙት ክፉ ድርጊት የተነሳ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ እነሱን የመቅጣት ዓላማ አለው፤ አብርሃም ደግሞ ይህን ያውቃል። አብርሃም የሚወደው ልጁ ይስሐቅ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ቁርኝት እንዲፈጥርም ሆነ ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ አኗኗራቸውን እንዲከተል አልፈለገም። ከዚህም በተጨማሪ፣ አምላክ ተስፋ ከሰጣቸው ነገሮች አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ይስሐቅ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተገንዝቧል።—ዘፍጥረት 15:16፤ 17:19፤ 24:2-4

ኤልዔዘር፣ በእንግድነት ለተቀበሉት ሰዎች ካራን አቅራቢያ ያለው የውኃው ጉድጓድ ጋ ሲደርስ ለይሖዋ አምላክ መጸለዩን ነገራቸው። ይህም ይስሐቅ የሚያገባትን ወጣት ይሖዋ እንዲመርጥ የጠየቀ ያህል ነበር። እንዴት? ኤልዔዘር፣ አምላክ የይስሐቅ ሚስት እንድትሆን የሚፈልጋት ወጣት ወደ ውኃው ጉድጓድ እንድትመጣ ጠየቀ። ውኃ አጠጪኝ ሲላት ኤልዔዘርን ብቻ ሳይሆን ግመሎቹንም ጭምር ውኃ ለማጠጣት ፈቃደኛ ልትሆን ይገባል። (ዘፍጥረት 24:12-14) ታዲያ ወደዚያ መጥታ ልክ እንደጠየቀው ያደረገችው ማን ናት? ርብቃ ነች! ኤልዔዘር ለቤተሰቧ ሁኔታውን ሲተርክ ወሬው ወደ ጆሮዋ ጥልቅ ቢል ምን ሊሰማት እንደሚችል ገምት!

ባቱኤልና ላባ፣ ኤልዔዘር በነገራቸው ነገር ልባቸው ስለተነካ “ይህ ነገር ከይሖዋ የመጣ ነው” አሉ። በወቅቱ በነበረው ልማድ መሠረት ርብቃን ለይስሐቅ በማጨት የጋብቻ ቃል ኪዳን ፈጸሙ። (ዘፍጥረት 24:50-54) እንዲህ ሲባል ግን ርብቃ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ተሰሚነት የላትም ማለት ነው?

ከተወሰኑ ሳምንታት በፊት ኤልዔዘር “ሴቲቱ ከእኔ ጋር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆንስ?” በማለት ለአብርሃም ይህንኑ ጉዳይ አንስቶለት ነበር። በዚህ ጊዜ አብርሃም “እንዲህ ካደረግክ ከመሐላህ ነፃ ትሆናለህ” የሚል መልስ ሰጠው። (ዘፍጥረት 24:39, 41) በባቱኤልም ቤት ቢሆን የልጅቷ ምርጫ ትኩረት ተሰጥቶታል። ኤልዔዘር ተልዕኮው በመሳካቱ እጅግ ከመደሰቱ የተነሳ በማግስቱ ርብቃን ይዞ ወዲያውኑ ወደ ከነአን መመለስ ይችል እንደሆነ ጠየቃቸው። ቤተሰቦቿ ግን ከዚህ በኋላ ቢያንስ ለአሥር ቀናት ከእነሱ ጋር እንድትቆይ ፈልገው ነበር። በመጨረሻም “ልጅቷን እንጥራና እንጠይቃት” በማለት ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ተስማሙ።—ዘፍጥረት 24:57

ርብቃ በሕይወቷ ውስጥ ትልቅ ውሳኔ የምታደርግበት ጊዜ ላይ ደርሳለች። መልሷ ምን ይሆን? አባቷና ወንድሟ ማዘናቸውን ሰበብ በማድረግ ወደማታውቀው አገር መሄዱ እንዲቀርባት ትማጸናቸው ይሆን? ወይስ ይሖዋ እያሳካው እንደሆነ በግልጽ በሚታየው ክንውን ውስጥ ድርሻ ያላት መሆኑን እንደ መብት ትቆጥረዋለች? ለቀረበላት ጥያቄ የሰጠችው መልስ በሕይወቷ ውስጥ ስላጋጠማት ስለዚህ ድንገተኛ፣ ምናልባትም አስደንጋጭ የሆነ ለውጥ ምን እንደተሰማት ያሳያል። ምንም ሳታቅማማ “አዎ፣ እሄዳለሁ” አለች።—ዘፍጥረት 24:58

ርብቃ ያሳየችው መንፈስ በእጅጉ የሚደነቅ ነው! በዛሬው ጊዜ ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ያለን ባሕል በጣም የተለየ ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና ከርብቃ ብዙ ነገር መማር እንችላለን። ርብቃ ትልቅ ቦታ የሰጠችው ለግል ምርጫዋ ሳይሆን ለአምላኳ ለይሖዋ ምርጫ ነበር። የአምላክ ቃል ዛሬም ጋብቻን በተመለከተ ከሁሉ የተሻለውን መመሪያ ይዟል፤ ምን ዓይነት የትዳር ጓደኛ መምረጥ እንዳለብንና ጥሩ ባል ወይም ጥሩ ሚስት መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይመክረናል። (2 ቆሮንቶስ 6:14, 15፤ ኤፌሶን 5:28-33) ርብቃ የተወችውን ምሳሌ መከተላችንና ነገሮችን በአምላክ መንገድ ለማከናወን መፈለጋችን እጅግ ይጠቅመናል።

“ያ ሰው ማን ነው?”

የባቱኤል ቤተሰቦች የሚወዷትን ርብቃን መርቀው ሸኟት። ከዚያም ሞግዚቷ ከሆነችው ከዲቦራና ከሴት አገልጋዮቿ ጋር ሆና ከኤልዔዘር እንዲሁም አብረውት ካሉት ሰዎች ጋር ጉዟቸውን ጀመሩ። (ዘፍጥረት 24:59-61፤ 35:8) ብዙም ሳይቆይ ከካራን በጣም ርቀው ተጓዙ። ጉዞው በጣም ረጅም ነው፤ ርቀቱ 800 ኪሎ ሜትር ገደማ ሲሆን እዚያ ለመድረስ ወደ ሦስት ሳምንት ሊፈጅባቸው ይችላል። ጉዞው የሚያንገላታ ሳይሆን አይቀርም። ርብቃ በሕይወት ዘመኗ ብዙ ግመሎች አይታለች፤ ይሁንና ግመል ላይ ተቀምጣ የመሄድ ልምድ አላት ብለን እንድናስብ የሚደርገን ነገር የለም። መጽሐፍ ቅዱስ ቤተሰቧ እረኞች መሆናቸውን እንጂ የግመል ቅፍለት እየነዱ የሚጓዙ ነጋዴዎች እንደሆኑ አይናገርም። (ዘፍጥረት 29:10) ሰዎች በግመል ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጓዙ ጥቂት ከሄዱ በኋላ ጉዞው እንዳንገላታቸው መናገራቸው የተለመደ ነው!

ያም ሆነ ይህ ርብቃ ትኩረቷ ያነጣጠረው ከፊቷ በሚጠብቃት ነገር ላይ ነው፤ ስለ ይስሐቅና ስለ ቤተሰቡ ከኤልዔዘር የቻለችውን ያህል ብዙ ነገር ለመስማት እንደምትሞክር ጥርጥር የለውም። ምሽት ላይ እሳት እየሞቁ አረጋዊው ኤልዔዘር ይሖዋ ለወዳጁ ለአብርሃም ስለገባለት ተስፋ ሲነግራት በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። አምላክ ለሰው ልጆች ሁሉ በረከት የሚያስገኝ አንድ ዘር ከአብርሃም ትውልድ መካከል ያስነሳል። ርብቃ፣ ይሖዋ የሰጠው ተስፋ ባሏ በሚሆነው ሰው፣ በይስሐቅ በኩል በተዘዋዋሪ መንገድ በእሷም በኩል እንደሚፈጸም ስትገነዘብ ልቧ በከፍተኛ አድናቆት ሲሞላ ይታይህ!—ዘፍጥረት 22:15-18

ርብቃ ብርቅ የሆነና የሚደነቅ ትሕትና አሳይታለች

በመጨረሻ፣ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የጠቀስነው ቀን ደረሰ። በሰልፍ የሚሄዱት ግመሎች ኔጌብን እያቋረጡ ባሉበትና ጀንበሯ መጥለቅ በጀመረችበት ሰዓት ርብቃ አንድ ሰው መስኩ ላይ እየተራመደ ሲሄድ አየች። ሰውየው የሆነ ነገር እያሰላሰለ ያለ ይመስላል። ዘገባው “ከግመሉ ላይ በፍጥነት ወረደች” ይላል፤ ምናልባትም ግመሉ በርከክ እስኪል ደረስ አልጠበቀች ይሆናል፤ ከዚያም ወደዚህ አገር ያመጣትን ሰው “ከእኛ ጋር ለመገናኘት ሜዳውን አቋርጦ የሚመጣው ያ ሰው ማን ነው?” ስትል ጠየቀችው። ግለሰቡ ይስሐቅ መሆኑን ስታውቅ ፊቷን ሸፈነች። (ዘፍጥረት 24:62-65) ለምን? እንዲህ ማድረጓ ወደፊት ባሏ ለሚሆነው ሰው ያላትን አክብሮት የሚያሳይ እንደሆነ ግልጽ ነው። በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች እንዲህ ዓይነት ተገዢነት ጊዜ ያለፈበት ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ወንዶችም ሆንን ሴቶች ርብቃ ካሳየችው ትሕትና ትምህርት መቅሰም እንችላለን፤ ምክንያቱም ከእኛ መካከል ይህ ግሩም ባሕርይ የስብዕናው ክፍል እንዲሆን የማይፈልግ ማን አለ?

በወቅቱ 40 ዓመት ገደማ የሚሆነው ይስሐቅ ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት እናቱን ሣራን በሞት በማጣቱ ከደረሰበት ሐዘን ገና አልተጽናናም ነበር። ከዚህ በመነሳት ይስሐቅ አፍቃሪና ሩኅሩኅ ሰው ነው ብለን መደምደም እንችላለን። እንዲህ ያለው ሰው ትጉ ሠራተኛ፣ እንግዳ ተቀባይና ትሑት የሆነች ሚስት በማግኘቱ ምንኛ ታድሏል! ለመሆኑ ይስሐቅና ርብቃ ተጣጥመው ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ በአጭሩ “እሱም ወደዳት” ይላል።—ዘፍጥረት 24:67፤ 26:8

ይህ ከሆነ ወደ 3,900 የሚጠጉ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም እንኳ በዛሬው ጊዜ ያለን ሰዎችም ርብቃን መውደድ አይከብደንም። የርብቃን ድፍረት፣ ታታሪነት፣ እንግዳ ተቀባይነትና ትሕትና ለማድነቅ አትገደድም? ወጣቶችም ሆን በዕድሜ የገፋን፣ ወንዶችም ሆን ሴቶች፣ ያገባንም ሆን ያላገባን ሁላችንም ርብቃን በእምነቷ መምሰላችን ይጠቅመናል!

^ አን.10 ርብቃ ውኃ ልትቀዳ የሄደችው አመሻሽ ላይ ነበር። ዘገባው የውኃው ጉድጓድ ጋ ብዙ ሰዓት እንዳሳለፈች ምንም ፍንጭ አይሰጥም። በተጨማሪም ሥራውን ጨርሳ ስትመጣ ቤተሰቦቿ ተኝተው እንደጠበቋት ወይም የተላከችበትን ጉዳይ ለመፈጸም በጣም በመዘግየቷ እሷን ፍለጋ የመጣ ሰው መኖሩን አይጠቁምም።

^ አን.15 በዚህ ዘገባ ላይ ኤልዔዘር በስም አልተጠቀሰም፤ ይሁንና በታሪኩ ላይ የተጠቀሰው አገልጋይ እሱ የመሆኑ አጋጣሚ ሰፊ ነው። አብርሃም ወራሽ የሚሆን ልጅ ካጣ ንብረቱን በሙሉ ለኤልዔዘር የማውረስ ሐሳብ እንዳለው በአንድ ወቅት ገልጾ ነበር፤ በመሆኑም ከአብርሃም አገልጋዮች መካከል በዕድሜ አንጋፋውና ከፍተኛ እምነት የሚጣልበት እሱ እንደነበር ግልጽ ነው። በዘገባው ላይ ይህ አገልጋይ የተገለጸውም በዚህ መንገድ ነው።—ዘፍጥረት 15:2፤ 24:2-4