በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ምያንማር

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ምያንማር

“አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው። ስለዚህ የመከሩ ሥራ ኃላፊ ወደ መከሩ፣ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።” (ሉቃስ 10:2) ኢየሱስ ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት የተናገራቸው እነዚህ ቃላት በዛሬው ጊዜ በምያንማር ያለውን ሁኔታ ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በምያንማር ላለው 55 ሚሊዮን ሕዝብ ምሥራቹን እያሰራጩ ያሉት 4,200 ገደማ የሚሆኑ አስፋፊዎች ብቻ ናቸው።

ሆኖም “የመከሩ ሥራ ኃላፊ” የሆነው ይሖዋ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች በደቡብ ምሥራቅ እስያ ወደምትገኘው ወደዚህች አገር ሄደው ለመንፈሳዊው የመከር ሥራ ድጋፍ እንዲያደርጉ ልባቸውን እያነሳሳ ነው። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች የትውልድ አገራቸውን ትተው ወደዚህች አገር ለመሄድ የተነሳሱት ለምንድን ነው? ይህን እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላቸውን እርዳታ ያገኙት እንዴት ነው? ምን በረከትስ አግኝተዋል? ይህ ርዕስ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ይዟል።

“ኑ፣ ተጨማሪ አቅኚዎች ያስፈልጉናል!”

ካዙሂሮ የተባለ በጃፓን የሚኖር አንድ አቅኚ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በሚጥል በሽታ ምክንያት ራሱን ስቶ ሆስፒታል ገባ። ሐኪሙ ለሁለት ዓመት ያህል መኪና መንዳት እንደሌለበት ነገረው። ካዙሂሮ በጣም ደነገጠ። ‘የምወደውን አቅኚነቴን መቀጠል የምችለው እንዴት ነው?’ የሚለው ጉዳይ አሳሰበው። በመሆኑም በአቅኚነት ማገልገሉን መቀጠል የሚችልበትን መንገድ እንዲከፍትለት ይሖዋን አጥብቆ ለመነው።

ካዙሂሮና ማሪ

ካዙሂሮ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ከአንድ ወር በኋላ፣ በምያንማር የሚያገለግል ጓደኛዬ ስለደረሰብኝ አሳዛኝ ሁኔታ ሰማ። ከዚያም ደውሎ እንዲህ አለኝ፦ ‘በምያንማር ዋነኛው መጓጓዣ አውቶቡስ ነው። እዚህ ከመጣህ መኪና ሳያስፈልግህ አገልግሎትህን ማከናወን ትችላለህ!’ እኔም ሐኪሜን የጤናዬ ሁኔታ ወደ ምያንማር ለመሄድ ይፈቅድልኝ እንደሆነ ጠየቅኩት። ሐኪሙም እንዲህ በማለት ያልጠበቅኩት መልስ ሰጠኝ፦ ‘በአሁኑ ጊዜ ጃፓንን እየጎበኘ ያለ ከምያንማር የመጣ አንድ የአንጎል ስፔሻሊስት አለ። ከእሱ ጋር አስተዋውቅሃለሁ። ሌላ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ እሱ ሊረዳህ ይችላል።’ ሐኪሙ ያለኝ ነገር ይሖዋ ለጸሎቴ የሰጠኝ ምላሽ እንደሆነ ተሰማኝ።”

ካዙሂሮ ወዲያውኑ በምያንማር ለሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ኢ-ሜይል በመጻፍ እሱና ባለቤቱ በምያንማር በአቅኚነት ማገልገል እንደሚፈልጉ ገለጸ። ቅርንጫፍ ቢሮውም በአምስት ቀን ውስጥ “ኑ፣ ተጨማሪ አቅኚዎች ያስፈልጉናል!” የሚል ምላሽ ሰጣቸው። ካዙሂሮና ባለቤቱ ማሪ መኪናቸውን ከሸጡና ቪዛቸውን ካገኙ በኋላ የአውሮፕላን ቲኬት ገዙ። በአሁኑ ጊዜ በማንዳሌይ በሚገኘው የምልክት ቋንቋ ቡድን ውስጥ በደስታ በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ካዙሂሮ እንዲህ ብሏል፦ “በሕይወታችን ያጋጠመን ይህ ተሞክሮ አምላክ በመዝሙር 37:5 ላይ ‘መንገድህን ለይሖዋ አደራ ስጥ፤ በእሱ ታመን፤ እሱም ለአንተ ሲል እርምጃ ይወስዳል’ በማለት በገባው ቃል ላይ ያለንን እምነት እንዳጠናከረልን ይሰማናል።”

ይሖዋ መንገዱን ይከፍታል

በ2014 በምያንማር ልዩ የክልል ስብሰባ የተደረገ ሲሆን ከተለያዩ አገሮች የመጡ ወንድሞችና እህቶች በስብሰባው ላይ ተገኝተው ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ የተገኘች ከዩናይትድ ስቴትስ የመጣች በ30ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኝ ሞኒክ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ከስብሰባው ከተመለስኩ በኋላ፣ በሕይወቴ ውስጥ መውሰድ ያለብኝን ቀጣይ እርምጃ በተመለከተ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። በተጨማሪም ስላሉኝ መንፈሳዊ ግቦች ወላጆቼን አማከርኳቸው። ሁላችንም ወደ ምያንማር ተመልሼ መሄዴ ጥሩ እንደሆነ ተሰማን፤ ሆኖም እዚህ ግቤ ላይ ለመድረስ የተወሰነ ጊዜ የወሰደብኝ ከመሆኑም ሌላ ደጋግሜ መጸለይ አስፈልጎኛል።” ሞኒክ ይህ የሆነበትን ምክንያት እንደሚከተለው በማለት ተናግራለች፦

ሞኒክና ሊ

“ኢየሱስ ተከታዮቹን ‘ወጪያቸውን እንዲያሰሉ’ አበረታቷቸዋል። በመሆኑም ራሴን እንዲህ ብዬ ጠየቅኩ፦ ‘ወደዚያ ተዛውሮ ለመኖር የሚያስችል አቅም አለኝ? ረጅም ሰዓት ሰብዓዊ ሥራ መሥራት ሳያስፈልገኝ ወጪዎቼን መሸፈን እችላለሁ?’” ሞኒክ እንዲህ ስትል በግልጽ ተናግራለች፦ “በሌላኛው የምድር ጫፍ ላይ ወደምትገኘው ወደዚህች አገር ለመዛወር በቂ ገንዘብ እንደሌለኝ ወዲያውኑ ተገነዘብኩ።” ታዲያ ወደ ምያንማር ተዛውራ ማገልገል የቻለችው እንዴት ነው?—ሉቃስ 14:28

ሞኒክ እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ቀን አሠሪዬ ልታነጋግረኝ እንደምትፈልግ ገለጸችልኝ። እኔም ከሥራ ልታባርረኝ ይሆናል ብዬ ስላሰብኩ ፈርቼ ነበር። አሠሪዬ ግን እያከናወንኩ ላለሁት ጥሩ ሥራ አመሰገነችኝ። ከዚያም ጉርሻ እንዲሰጠኝ ዝግጅት እንዳደረገች ነገረችኝ፤ የሚገርመው የተሰጠኝ ጉርሻ ዕዳዎቼን ለመክፈል የሚያስፈልገኝ የገንዘብ መጠን ነበር!”

ሞኒክ ከታኅሣሥ 2014 ጀምሮ በምያንማር በማገልገል ላይ ትገኛለች። ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ስለምታከናውነው አገልግሎት ምን ይሰማታል? እንዲህ ብላለች፦ “ወደዚህ በመምጣቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አሉኝ። ከጥናቶቼ መካከል አንዷ 67 ዓመቷ ነው። ሁልጊዜ ወደ እሷ ስሄድ ፈገግ ብላ እቅፍ ታደርገኛለች። ይህች ሴት የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ ስታውቅ አለቀሰች። ከዚያም እንዲህ አለችኝ፦ ‘የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት አሁን ነው። አንቺ ከእኔ በዕድሜ በጣም ታንሺያለሽ፤ ነገር ግን በሕይወቴ ልማራቸው ከምችላቸው ነገሮች ሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር አስተምረሽኛል።’ በዚህ ጊዜ እኔም አለቀስኩ። ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውሮ ማገልገልን በጣም አርኪ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል እንዲህ ያሉ ተሞክሮዎች ይገኙበታል።” በቅርቡ ሞኒክ በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት የመካፈል መብት አግኝታለች።

አንዳንዶችን ወደ ምያንማር ሄዶ ለማገልገል ያነሳሳቸው በ2013 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ላይ ይህችን አገር አስመልክቶ የወጣውን ዘገባ ማንበባቸው ነው። በ30ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኝ ሊ የተባለች እህት ቀድሞውንም ቢሆን የምትኖረው በደቡብ ምሥራቅ እስያ ነበር። የሙሉ ጊዜ ሥራ የነበራት ቢሆንም በዚህ የዓመት መጽሐፍ ላይ የወጣውን ዘገባ ስታነብ ወደ ምያንማር ሄዳ ለማገልገል አሰበች። እንዲህ ብላለች፦ “በ2014 በያንጎን በተደረገው ልዩ የክልል ስብሰባ ላይ ተገኝቼ ነበር፤ በዚያም ወደ ምያንማር ተዛውረው በቻይንኛ መስክ ላይ የሚያገለግሉ አንድ ባልና ሚስት አገኘሁ። ቻይንኛ ስለምችል ወደ ምያንማር ተዛውሬ በዚያ ያለውን የቻይንኛ ቡድን ለመርዳት ወሰንኩ። ከዚያም ከሞኒክ ጋር አብረን ወደ ማንዳሌይ ተዛወርን። በይሖዋ እርዳታ ሁለታችንም በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ለተወሰነ ሰዓት ያህል ብቻ የምንሠራው የማስተማር ሥራ አገኘን፤ በተጨማሪም እዚያው አቅራቢያ መኖሪያ ቤት ማግኘት ቻልን። ሞቃታማ የሆነውን የአየር ጠባይ ጨምሮ አንዳንድ የማይመቹ ነገሮች ቢኖሩም እዚህ በማከናውነው አገልግሎት ደስተኛ ነኝ። የምያንማር ነዋሪዎች ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ቢሆኑም ሰው አክባሪዎች ናቸው፤ ደግሞም ጊዜያቸውን ሰጥተው ምሥራቹን ለመስማት ፈቃደኞች ናቸው። ይሖዋ ሥራውን ምን ያህል እያፋጠነው እንዳለ መመልከት በጣም አስደሳች ነው። ማንዳሌይ ውስጥ ማገልገሌ የይሖዋ ፈቃድ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ።”

ይሖዋ ጸሎት ሰሚ ነው

ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች ተዛውረው የሚያገለግሉ ብዙ ወንድሞችና እህቶች ጸሎት ያለውን ኃይል በሕይወታቸው ተመልክተዋል። በ30ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የሚገኙትን የጁምፔንና የባለቤቱን የናኦን ተሞክሮ እንመልከት። የሚያገለግሉት ጃፓን ውስጥ በሚገኝ የምልክት ቋንቋ ጉባኤ ነበር። ወደ ምያንማር ለመዛወር የወሰኑት ለምንድን ነው? ጁምፔ እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አገር ተዛውሮ የማገልገል ግብ ነበረን። በነበርንበት የምልክት ቋንቋ ጉባኤ ውስጥ የነበረ አንድ ወንድም ወደ ምያንማር ተዛውሮ ማገልገል ጀመረ። ምንም እንኳ ያጠራቀምነው ገንዘብ አነስተኛ ቢሆንም እኛም በግንቦት 2010 ወደ ምያንማር ሄድን። በዚያ ያሉት ወንድሞችና እህቶች ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልን!” ጁምፔ በምያንማር ስላለው የምልክት ቋንቋ መስክ ምን ይሰማዋል? እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎቹ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። መስማት የተሳናቸው የቤት ባለቤቶች በምልክት ቋንቋ የተዘጋጁ ቪዲዮዎችን ሲያዩ ይገረማሉ። ወደዚህ ተዛውረን ይሖዋን ለማገልገል በመወሰናችን በጣም ተደስተናል!”

ናኦና ጁምፔ

ጁምፔና ናኦ፣ የነበረባቸውን የገንዘብ ችግር የተወጡት እንዴት ነው? ጁምፔ እንዲህ ብሏል፦ “ከሦስት ዓመት በኋላ፣ ያጠራቀምነው ገንዘብ እያለቀ ስለመጣ ለቀጣዩ ዓመት የቤት ኪራይ የምንከፍለው በቂ ገንዘብ አልነበረንም። እኔና ባለቤቴ በተደጋጋሚ ከልብ የመነጨ ጸሎት አቀረብን። ከዚያም ፈጽሞ ባልጠበቅነው ሁኔታ ከቅርንጫፍ ቢሮው ጊዜያዊ ልዩ አቅኚዎች ሆነን እንድናገለግል መጋበዛችንን የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰን! እምነታችንን በይሖዋ ላይ ጥለን ነበር፤ እሱም አልተወንም። ይሖዋ በሁሉም መንገድ እየተንከባከበን ነው።” ጁምፔና ናኦም በቅርቡ በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት የመካፈል መብት አግኝተዋል።

ይሖዋ የብዙዎችን ልብ አነሳስቷል

በ40ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የሚገኘውን የጣሊያን ተወላጅ የሆነውን ሲሞኔን እና በ30ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ የምትገኘውን የኒው ዚላንድ ተወላጅ የሆነችውን ባለቤቱን አናን ወደ ምያንማር ለመዛወር ያነሳሳቸው ምንድን ነው? አና “በ2013 የዓመት መጽሐፍ ላይ ስለ ምያንማር የወጣው ዘገባ ነው” በማለት መልሳለች። ሲሞኔ እንዲህ ብሏል፦ “በምያንማር ማገልገል ትልቅ መብት ነው። እዚህ ኑሮ ቀላል ስለሆነ ብዙ ጊዜዬን ለይሖዋ ሥራ መስጠት እችላለሁ። ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ተዛውረን ስናገለግል ይሖዋ የሚያደርግልንን እንክብካቤ ማየት በጣም አስደሳች ነው።” (መዝ. 121:5) አና እንዲህ ብላለች፦ “ከምንጊዜውም ይበልጥ ደስተኛ ነኝ። ኑሯችን በጣም ቀላል ነው። ከባለቤቴ ጋር ከበፊቱ የበለጠ ጊዜ አብረን ስለምናሳልፍ ይበልጥ ተቀራርበናል። በጣም የምንወዳቸውን አዳዲስ ወዳጆች ማፍራት ችለናል። እዚህ ያሉት ሰዎች ለይሖዋ ምሥክሮች ጭፍን ጥላቻ የላቸውም፤ በመስክ የምናገኛቸው ሰዎች ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው!”

ሲሞኔና አና

አና አክላም እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ቀን፣ በገበያ ቦታ ላገኘኋት አንዲት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከመሠከርኩላት በኋላ ድጋሚ ለመገናኘት ተቀጣጠርን። በቀጠሯችን ስንገናኝ አንድ ጓደኛዋን ይዛ መጣች። በቀጣዩ ጊዜ ስንገናኝ ደግሞ ተጨማሪ ጓደኞቿን አመጣች። ከዚያም እንደገና ስንገናኝ ሌሎች ጓደኞቿን ጨምራ ይዛ መጣች። አሁን አምስት የሚያክሉትን እያስጠናኋቸው ነው።” ሲሞኔ እንዲህ ብሏል፦ “በመስኩ ላይ የምናገኛቸው ሰዎች ተግባቢዎችና የማወቅ ጉጉት ያላቸው ናቸው። ብዙዎቹ የመወያየት ፍላጎት አላቸው። እንዲያውም ፍላጎት ያሳዩትን ሁሉ የምንረዳበት በቂ ጊዜ የለንም።”

ሳቺዮና ሚዙሆ

አንዳንዶች ወደ ምያንማር ተዛውረው ለማገልገል ከመወሰናቸው በፊት ምን ተግባራዊ እርምጃዎች ወስደዋል? የጃፓን ተወላጅ የሆነችው ሚዙሆ እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ባለቤቴ ሳቺዮ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ተዛውሮ የማገልገል ፍላጎት ነበረን፤ ግን ‘የት?’ የሚለውን አናውቅም ነበር። በ2013 የዓመት መጽሐፍ ላይ ስለ ምያንማር የወጡትን አስደሳች ተሞክሮዎች ስናነብ ልባችን በጣም ስለተነካ ወደ ምያንማር ተዛውረን ማገልገል እንችል እንደሆነ ማሰብ ጀመርን።” ሳቺዮ እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሯል፦ “የምያንማር ዋና ከተማ የሆነችውን ያንጎንን ለአንድ ሳምንት ያህል ለመጎብኘት፣ በሌላ አነጋገር ምድሪቱን ለመሰለል ወሰንን። በዚያ ያለውን ሁኔታ ለማወቅ ያደረግነው ይህ አጭር ጉዞ ወደዚያ መዛወር እንዳለብን አሳመነን።”

ለጥሪው ምላሽ ትሰጣለህ?

ጄን፣ ዳኒካ፣ ሮድኒና ጆርዳን

ከአውስትራሊያ የመጡ ሮድኒና ጄን የተባሉ በ50ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ባልና ሚስት ከልጆቻቸው ከጆርዳንና ከዳኒካ ጋር ከ2010 ጀምሮ ወደ ምያንማር ተዛውረው እያገለገሉ ነው። ሮድኒ እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎቹ ያላቸውን መንፈሳዊ ረሃብ መመልከታችን ልባችንን በጥልቅ ነክቶታል። ሌሎች ቤተሰቦችም እንደ ምያንማር ወዳሉ ቦታዎች ተዛውረው እንዲያገለግሉ እናበረታታለን።” ለምን? “እንዲህ ማድረጋችን ለቤተሰባችን ያስገኘው መንፈሳዊ ጥቅም በዋጋ የማይተመን ነው! በርካታ ወጣቶች የሚያስቡት ስለ ስልክ፣ ስለ መኪና፣ ስለ ሥራና ስለመሳሰሉት ነገሮች ነው። የእኛ ልጆች ግን በአገልግሎት ላይ የሚጠቀሙባቸውን አዳዲስ ቃላት በመማር ተጠምደዋል። በተጨማሪም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እምብዛም እውቀት ከሌላቸው ሰዎች ጋር መወያየትና በአገሪቱ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ሐሳብ መስጠት ስለሚችሉበት መንገድ ለመማር ጥረት እያደረጉ ነው፤ ሕይወታቸው በእነዚህና በሌሎች አስደሳች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የተሞላ ነው።”

ኦሊቨርና አና

ከዩናይትድ ስቴትስ የመጣ በ30ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ የሚገኝ ኦሊቨር የተባለ ወንድም በዚህ ዓይነቱ የአገልግሎት መስክ መካፈልን የሚያበረታታው ለምን እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ከለመድኩት ወጣ ባለ ሁኔታ ይሖዋን ማገልገሌ ብዙ ጥቅሞች አስገኝቶልኛል። ከቤት ርቄ መሄዴ፣ በማንኛውም ሁኔታ ሥር በይሖዋ እንድታመንና እንድመካ ረድቶኛል። ከዚህ በፊት ከማላውቃቸው ሆኖም ከእኔ ጋር ተመሳሳይ እምነት ካላቸው ሰዎች ጋር ማገልገሌ በዚህ ዓለም ውስጥ የአምላክን መንግሥት ያህል አስፈላጊ የሆነ ነገር እንደሌለ እንድገነዘብ አስችሎኛል።” በአሁኑ ጊዜ ኦሊቨርና ባለቤቱ አና በቻይንኛ ቋንቋ መስክ በቅንዓት በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

ትራዜል

ከአውስትራሊያ የመጣች በ50ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኝ ትራዜል የተባለች እህት ከ2004 ጀምሮ በምያንማር ስታገለግል ቆይታለች። እንዲህ ብላለች፦ “ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸው ሁሉ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ተዛውረው እንዲያገለግሉ አበረታታለሁ። ይሖዋ እሱን የማገልገል ፍላጎት እስካለን ድረስ ጥረታችንን እንደሚባርክ በገዛ ሕይወቴ ተመልክቻለሁ። እንዲህ ያለ ሕይወት እመራለሁ ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም። ላስበው ከምችለው በላይ የሚክስና የሚያረካ ሕይወት ነው።”

በምያንማር የሚያገለግሉት እነዚህ ወንድሞችና እህቶች የተናገሯቸው ከልብ የመነጩ ቃላት ምሥራቹ ባልተሰበከባቸው አካባቢዎች የሚገኙትን ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ለመርዳት እንዲያነሳሳህ ምኞታችን ነው። አዎ፣ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች ተዛውረው የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች “እባካችሁ፣ ወደ ምያንማር ተሻገሩና እርዱን!” የሚል ጥሪ እያቀረቡ ነው።