በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኮከብ ቆጠራ የወደፊት ዕጣህን እንድታውቅ ያስችልሃል?

ኮከብ ቆጠራ የወደፊት ዕጣህን እንድታውቅ ያስችልሃል?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ኮከብ ቆጠራ የወደፊት ዕጣህን እንድታውቅ ያስችልሃል?

ሕይወትህን ማሻሻል፣ አልፎ ተርፎም ፍቅርና ገንዘብ በማግኘት ረገድ ስኬታማ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? ብዙ ሰዎች እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ወደ ኮከብ ቆጠራ ዘወር ይላሉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ለማሻሻል ካላቸው ፍላጎት የተነሳ በጋዜጣ ላይ የሚወጡ የኮከብ ቆጠራ ዓምዶችን በየቀኑ ይከታተላሉ። አንዳንድ የዓለም ገዢዎችም በከዋክብት ተመርተው ውሳኔ እንደሚያደርጉ የታወቀ ነው።

ኮከብ ቆጠራ ተዓማኒነት አለው? ኮከብ ቆጣሪዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ትንቢት የሚናገሩት እንዴት ነው? ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን በምን መንገድ መምራት እንዳለባቸው ለመወሰን የሰማይ አካላትን መጠቀም ይኖርባቸዋል?

ኮከብ ቆጠራ ምንድን ነው?

ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዳለው ኮከብ ቆጠራ “የሰማይ አካላት የሰዎችን ባሕርይ አሊያም የወደፊት ዕጣ ለማወቅ የሚያስችል ንድፍ ይሠራሉ በሚል እምነት ላይ የተመሠረተ ነው።” የኮከብ ቆጠራ አማኞች፣ አንድ ሰው በሚወለድበት ጊዜ ፕላኔቶች የሚኖራቸው ትክክለኛ ቦታና የዞዲያክ ምልክቶች በሕይወቱ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላሉ የሚል እምነት አላቸው። * እነዚህ የሰማይ አካላት በአንድ በተወሰነ ጊዜ ላይ የሚኖራቸው ቦታ ሆሮስኮፕ ይባላል።

ኮከብ ቆጠራ ጥንትም የነበረ ነው። ወደ አራት ሺህ ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ባቢሎናውያን ፀሐይ፣ ጨረቃና በግልጽ የሚታዩት አምስት ፕላኔቶች የሚገኙበትን ቦታ ተመርኩዘው ስለ መጪው ጊዜ ይተነብዩ ጀመር። ባቢሎናውያን እነዚህ የሰማይ አካላት በሰው ልጆች ባሕርይ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር የተወሰነ ኃይል አላቸው የሚል እምነት ነበራቸው። በኋላ ላይ ደግሞ የዞዲያክ ምልክቶችን ጨምረው መተንበይ ጀመሩ።

ውድቀትን የሚያሳይ የረጅም ጊዜ ታሪክ

መጽሐፍ ቅዱስ በባቢሎንና በኮከብ ቆጠራ መካከል ያለውን ግንኙነት በጉልህ የሚያሳይ ሲሆን ስለ ባቢሎናውያን ኮከብ ቆጣሪዎችም በተደጋጋሚ ጊዜያት ይናገራል። (ዳንኤል 4:7፤ 5:7, 11) ነቢዩ ዳንኤል በኖረበት ዘመን ኮከብ ቆጠራ በከላውዴዎን (በባቢሎኒያ) እጅግ ከመስፋፋቱ የተነሳ ኮከብ ቆጣሪዎች ለማለት “ከለዳውያን” ይባል ነበር።

ዳንኤል ኮከብ ቆጠራ በባቢሎን ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ብቻ ሳይሆን ኮከብ ቆጣሪዎቿ ስለ ከተማዋ ውድቀት መተንበይ እንዳልቻሉ ጭምር ተመልክቶ ነበር። (ዳንኤል 2:27) ነቢዩ ኢሳይያስ ባቢሎን ከመጥፋቷ ከሁለት መቶ ዓመት በፊት የተናገረውን ትክክለኛ ትንቢት ልብ በል። ኢሳይያስ “እነዚያ ከወር እስከ ወር ከዋክብትን አንጋጦ በማየት የሚተነብዩ፣ ኮከብ ቈጣሪዎች እስቲ ይምጡ፤ ከሚደርስብሽም ነገር እስቲ ያድኑሽ” ካለ በኋላ ‘ራሳቸውን እንኳ ማዳን አይችሉም’ በማለት ተሳልቆባቸዋል።—ኢሳይያስ 47:13, 14

በግልጽ እንደታየው ባቢሎን ከመጥፋቷ ከጥቂት ሰዓታት በፊት እንኳ ኮከብ ቆጣሪዎቿ ውድቀቷን ሊተነብዩ አልቻሉም ነበር። አምላክ ያስተላለፈው የቅጣት ፍርድ በንጉሥ ቤልሻዛር ቤተ መንግሥት ግድግዳ ላይ በታየበት ጊዜም ቢሆን የንጉሡ ኮከብ ቆጣሪዎች የምሥጢር ጽሕፈቱን መተርጎም እንዳልቻሉ ግልጽ ሆኗል።—ዳንኤል 5:7, 8

ዛሬም ቢሆን ኮከብ ቆጣሪዎች ጉልህ ክስተቶችን እንኳ መተንበይ የማይችሉ መሆናቸውን አሳይተዋል። ሮበርት ኩልቨር እና ፊልፕ ኢአና የተባሉ የሳይንስ ተመራማሪዎች ከ3,000 በሚበልጡ የኮከብ ቆጠራ ትንበያዎች ላይ ምርምር ካደረጉ በኋላ ትክክለኛ ትንቢት ሆኖ ያገኙት 10 በመቶ ያህሉን ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል። በቂ መረጃ ያለው አንድ ተንታኝ እንኳ ከዚህ የተሻለ መተንበይ አያቅተውም።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ይጋጫል

ይሁን እንጂ ዕብራውያን ነቢያት ኮከብ ቆጠራን ያወገዙት የወደፊቱን ጊዜ በትክክል መተንበይ እንደማይችል ስለተገነዘቡ ብቻ አልነበረም። አምላክ ለሙሴ የሰጠው ሕግ እስራኤላውያን ሞራ እንዳይገልጡ በግልጽ ያስጠነቅቃል። ሕጉ “ሟርተኛ፣ ወይም . . . ሞራ ገላጭ . . . በመካከልህ ከቶ አይገኝ። እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው” በማለት ይናገራል።—ዘዳግም 18:10-12

በዚህ ጥቅስ ላይ ኮከብ ቆጠራ በቀጥታ ባይጠቀስም እንኳ ትእዛዙ ይህን ድርጊትም እንደሚጨምር ግልጽ ነው። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ኮከብ ቆጠራ “ቋሚ ከዋክብትን፣ ፀሐይን፣ ጨረቃንና ፕላኔቶችን ተመልክቶ ፍቺ በመስጠት ስለ ምድራዊ ክስተቶችና ሰዎች ስለሚያጋጥሟቸው ሁኔታዎች አስቀድሞ የሚያሳውቅ የሟርት ዓይነት” እንደሆነ ገልጿል። በከዋክብት አሊያም በሌሎች ነገሮች ላይ ተመሥርቶ የሚፈጸም ማንኛውም ዓይነት ሟርት አምላክ የሰጠውን ትእዛዝ ይቃረናል። ለምን? ለዚህ በቂ ምክንያት አለ።

መጽሐፍ ቅዱስ የሚገጥመንን ስኬትም ሆነ ችግር ከከዋክብት ጋር ከማያያዝ ይልቅ “ሰው የሚዘራውን ያንኑ ያጭዳል” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ገላትያ 6:7) ሕይወታችንን በፈለግነው መንገድ የመምራት ነፃነት ያለን እንደመሆናችን መጠን እያንዳንዳችን የምናከናውነው ነገር በአምላክ ፊት በኃላፊነት ያስጠይቀናል። (ዘዳግም 30:19, 20፤ ሮሜ 14:12) ከቁጥጥራችን ውጪ በሆኑ ነገሮች ምክንያት አንድ ዓይነት አደጋ ወይም ሕመም ሊደርስብን እንደሚችል እሙን ነው። ይሁንና እንዲህ ያሉት አደጋዎች ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚሉት “ጊዜና አጋጣሚ” የሚያስከትላቸው እንጂ ከኮከብ ጋር ግንኙነት ያላቸው አይደሉም።—መክብብ 9:11 NW

ከሰዎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት እንደ ርኅራኄ፣ ቸርነት፣ ትሕትና፣ ጨዋነት፣ ትዕግሥትና ፍቅር የመሳሰሉ መልካም ባሕርያትን እንድንለብስ መጽሐፍ ቅዱስ አጥብቆ ይመክረናል። (ቈላስይስ 3:12-14) እነዚህ ባሕርያት ከሌሎች ጋር ዘላቂ ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስችሉ ከመሆናቸውም በላይ ትዳርን ለማጠናከር ይረዳሉ። “የኮከብ መግጠም” ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ለመምረጥ አስተማማኝ መመዘኛ ሆኖ ሊያገለግል አይችልም። በርናርድ ሲልቨርማን የተባሉ የሥነ ልቦና ባለሞያ 3,500 በሚሆኑ ባለትዳሮች ኮከብ ላይ ጥናት አድርገው የነበረ ሲሆን ከእነዚህ ባልና ሚስቶች መካከል 17 በመቶ የሚሆኑት ከጊዜ በኋላ ተፋትተዋል። እርሳቸው እንዳሉት ‘ኮከባቸው ይገጥማል’ ተብሎ በተጋቡ ባለትዳሮች መካከል የታየው የፍቺ መጠን ከዚህ የሚተናነስ አይደለም።

በግልጽ እንደሚታየው ኮከብ ቆጠራ እምነት የማይጣልበት ከመሆኑም በላይ አሳሳች ነው። ስህተት በምንፈጽምበት ጊዜ ራሳችንን ከመኮነን ይልቅ በከዋክብት ላይ እንድናማርር ያደርገናል። ከምንም በላይ ደግሞ በአምላክ ቃል ውስጥ ፈጽሞ የተወገዘ ድርጊት ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 የዞዲያክ ምልክቶች ኮከብ ቆጣሪዎች ለትንበያ የሚጠቀሙባቸው ቋሚ ቦታ ያላቸው የሚመስሉ 12 ከዋክብት ናቸው።