በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቤታችሁ አስተማማኝ የእረፍት ቦታ እንዲሆን አድርጉ

ቤታችሁ አስተማማኝ የእረፍት ቦታ እንዲሆን አድርጉ

“ፍቅር የሌላቸው።” መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻው ዘመን’ ተብሎ በሚጠራው በእኛ ዘመን የሚኖሩ ብዙ ሰዎች የሚያሳዩትን ባሕርይ የሚገልጸው በዚህ መንገድ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 3, 4) በቤተሰብ ውስጥ እንደ ወረርሽኝ ተዛምቶ የሚገኘው ልጆችን የማስነወር ድርጊት ይህ ትንቢት እውነት ለመሆኑ ጉልህ ማስረጃ ነው። እንዲያውም “ፍቅር የሌላቸው” ተብሎ የተተረጎመው አስቶርጎስ የሚለው የግሪክኛ ቃል በቤተሰብ አባላት በተለይም በወላጆችና በልጆች መካከል ሊኖር የሚገባው ፍቅር መጥፋቱን የሚያመለክት ነው። * ብዙውን ጊዜም ልጆች የሚነወሩት በቤተሰባቸው አባል ወይም በዘመዳቸው ነው።

አንዳንድ ተመራማሪዎች፣ በቤት ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ የፆታ ጥቃት የሚፈጽመው የልጆቹ ወላጅ አባት ወይም የአባትነት ሚና የሚጫወተው ሌላ ወንድ እንደሆነ ይናገራሉ። ወንዶች የሆኑ ሌሎች ዘመዶችም የፆታ ጥቃት ማድረሳቸው የተለመደ ነገር ነው። አብዛኛውን ጊዜ የጥቃቱ ሰለባ የሚሆኑት ሴቶች ልጆች ቢሆኑም በርካታ ወንዶች ልጆችም ይነወራሉ። ልጆችን የሚያስነውሩ ሴቶችም ቢሆኑ እንደምናስበው ጥቂት አይደሉም። ብዙም ሪፖርት ከማይደረጉት የፆታ ጥቃቶች በዋነኝነት የሚጠቀሰው፣ በዕድሜ ታላቅ ወይም ኃይለኛ የሆነው ልጅ ታናሹን ወይም አቅመ ደካማ የሆነውን ወንድሙን ወይም እህቱን አስፈራርቶም ሆነ አባብሎ የፆታ ድርጊት እንዲፈጽም የሚያደርግበት ሁኔታ ሳይሆን አይቀርም። ወላጆች፣ እነዚህ ሁሉ ድርጊቶች በጣም እንደሚዘገንኗችሁ ጥርጥር የለውም።

እነዚህ ችግሮች በቤተሰባችሁ ውስጥ እንዳይከሰቱ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል አስነዋሪ ድርጊቶችን ለማስወገድ የሚረዱ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መማርና እነዚህን መመሪያዎች ከፍ አድርጎ መመልከት እንደሚኖርበት ግልጽ ነው። እንዲህ ዓይነቱ መመሪያ የሚገኝበት ከሁሉ የተሻለ ቦታ ደግሞ የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ነው።

የአምላክ ቃልና የፆታ ግንኙነት

እያንዳንዱ ቤተሰብ አስተማማኝ የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖረው የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መከተል ያስፈልገዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት ክብር ባለው ሆኖም ግልጽና ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ይናገራል። የአምላክ ዓላማ የፆታ ግንኙነት ለባልና ሚስት እውነተኛ እርካታ እንዲያስገኝ መሆኑን ይገልጻል። (ምሳሌ 5:15-20) ይሁን እንጂ ከጋብቻ ዝግጅት ውጪ የሚደረግን የፆታ ግንኙነት ያወግዛል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ በሥጋ ዘመዶች መካከል የሚደረግን የፆታ ግንኙነት በግልጽ ያወግዛል። በዘሌዋውያን ምዕራፍ 18 ላይ በተለያዩ የቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚደረጉ የፆታ ግንኙነቶች ተከልክለዋል። በተለይ ደግሞ የሚከተሉትን ቃላት ልብ እንበል:- “ማንም ሰው ግብረ ሥጋ ለመፈጸም ወደ ማንኛውም የሥጋ ዘመዱ አይቅረብ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”—ዘሌዋውያን 18:6

ይሖዋ በሥጋ ዘመዳሞች መካከል የሚደረግ የፆታ ግንኙነትን በሞት በሚያስቀጡ “አስጸያፊ ድርጊቶች” ዝርዝር ውስጥ አካቶታል። (ዘሌዋውያን 18:26, 29) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በዚህ ረገድ የፈጣሪያችን የሥነ ምግባር መሥፈርት በጣም ከፍ ያለ ነው። በዛሬው ጊዜ ብዙ መንግሥታትም በቤተሰብ ውስጥ ልጆችን በፆታ ማስነወርን የሚከለክል ሕግ በማውጣት ከፈጣሪ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አቋም እየያዙ ነው። ብዙውን ጊዜ ሕጉ፣ አንድ አዋቂ ሰው ከልጅ ጋር የፆታ ግንኙነት ቢፈጽም ልጁ ተገዶ እንደተደፈረ እንደሚቆጠር ይገልጻል። አዋቂው ሰው ልጁ ይህን ድርጊት እንዲፈጽም ለማድረግ በኃይል ተጠቅሞ እስካላስገደደው ድረስ ሕጉ “አስገድዶ መድፈር” የሚለውን ከባድ ቃል የሚጠቀመው ለምንድን ነው?

ብዙ ባለ ሥልጣናት፣ ልጆች አዋቂዎች በሚያስቡበት መንገድ ማሰብ እንደማይችሉ የሚገልጸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ መገንዘብ ችለዋል። ለአብነት ያህል፣ ምሳሌ 22:15 “ሞኝነት በሕፃን ልብ ታስሮአል” ይላል። ሐዋርያው ጳውሎስም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “ልጅ ሳለሁ . . . እንደ ልጅ አስብ ነበር፤ እንደ ልጅም አሰላ ነበር። ከጐለመስሁ በኋላ ግን የልጅነትን ነገር እርግፍ አድርጌ ትቻለሁ።”—1 ቆሮንቶስ 13:11

አንድ ልጅ የፆታ ድርጊት ምን እንደሆነ ሙሉ ለሙሉ ሊገባው አይችልም፤ ወይም ደግሞ ድርጊቱ በቀሪው ሕይወቱ ምን መዘዝ እንደሚያስከትልበት ማስተዋል አይችልም። በመሆኑም ልጆች ጉዳዩን ተረድተውት በፆታ ግንኙነት ለመካፈል ሊስማሙ እንደማይችሉ በሰፊው ይታመንበታል። በሌላ አነጋገር፣ አንድ አዋቂ ሰው (ወይም ልጁን በዕድሜ ብዙ የሚበልጠው ወጣት) ከአንድ ልጅ ጋር የፆታ ግንኙነት ከፈጸመ በኋላ፣ ‘ልጁ ድርጊቱን አልተቃወመም ወይም ደግሞ ልጁ ራሱ ተስማምቶበት ነው’ በማለት ድርጊቱን ሊያስተባብል አይችልም። ይህን ድርጊት የፈጸመው ግለሰብ በልጁ ላይ አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ፈጽሟል። ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ በእስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው። በዚህ ድርጊት በኃላፊነት የሚጠየቀው ሳይፈልግ በድርጊቱ የተካፈለው ልጅ ሳይሆን አስገድዶ የደፈረው ግለሰብ ነው።

የሚያሳዝነው ግን በአሁኑ ጊዜ ባለ ሥልጣናት እንደዚህ ዓይነት ድርጊት ከፈጸሙት ወንጀለኞች ውስጥ አብዛኞቹን አይቀጧቸውም። ለምሳሌ ያህል፣ በአውስትራሊያ ይህን ወንጀል ከሚፈጽሙት ሰዎች ውስጥ ሕግ ፊት የሚቀርቡት 10 በመቶ ብቻ ሲሆኑ ከእነዚህም ውስጥ ጥፋተኛ ተብለው የሚፈረድባቸው ጥቂቶቹ ናቸው። በሌሎች አገሮችም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። መንግሥታት የክርስቲያኖችን ቤተሰብ ለመጠበቅ ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር በጣም አናሳ ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋል ግን ትልቅ ጥበቃ ያስገኛል።

እውነተኛ ክርስቲያኖች ከላይ የተመለከትናቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች በቃሉ ውስጥ ያስመዘገበው አምላክ ዛሬም እንዳልተለወጠ ይገነዘባሉ። የምንፈጽመውን እያንዳንዱን ድርጊት፣ ከሰዎች ተሰውረን የምናደርገውንም ጭምር ይመለከታል። መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ራሳችን መልስ መስጠት በሚገባን በእርሱ ፊት ሁሉም ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው” ይላል።—ዕብራውያን 4:13

ትእዛዛቱን ጥሰን ሌሎችን ብንጎዳ አምላክ ይጠይቀናል። በሌላ በኩል ደግሞ የቤተሰብን ሕይወት አስመልክቶ ያወጣቸውን ጠቃሚ ሕጎች በጥብቅ ስንከተል ይባርከናል። ከእነዚህ ሕጎች ውስጥ አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

በፍቅር የተሳሰረ ቤተሰብ

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ፍቅር ሁሉን በፍጹም አንድነት እንደሚያስተሳስር’ ይነግረናል። (ቈላስይስ 3:14) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተገለጸው ፍቅር እንዲሁ ስሜት ብቻ አይደለም። ፍቅር በሚያሳድረው ተጽዕኖ ይገለጻል፤ ይህም ሲባል ምን ዓይነት ባሕርያትን እንድናፈራ እንደሚያነሳሳን ወይም ከምን ዓይነት ድርጊቶች እንድንቆጠብ እንደሚያደርገን በመመልከት ፍቅር እንዳለን ማየት ይቻላል። (1 ቆሮንቶስ 13:4-8) በቤተሰብ ውስጥ ፍቅር ማሳየት ሲባል እያንዳንዱን የቤተሰብ አባል በአክብሮትና በደግነት መያዝ ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ አምላክ ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ካለው አመለካከት ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ማለት ነው። አምላክ ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የተከበረና በጣም ጠቃሚ የሥራ ድርሻ ሰጥቷል።

አባት የቤተሰብ ራስ እንደመሆኑ መጠን ፍቅር በማሳየት በኩል ቀዳሚ መሆን አለበት። ክርስቲያን አባት በሚስቱ ወይም በልጆቹ ላይ ሥልጣኑን ያለአግባብ በመጠቀም አምባገነን ለመሆን ፈቃድ እንዳልተሰጠው ይገነዘባል። ከዚህ ይልቅ በራስነት ረገድ የክርስቶስን ምሳሌነት ይከተላል። (ኤፌሶን 5:23, 25) ስለዚህ ለሚስቱ ርኅሩኅና አፍቃሪ፣ ለልጆቹ ደግሞ ታጋሽና ደግ ነው። በታማኝነት ከጥቃት የሚጠብቃቸው ሲሆን ሰላማቸውን፣ የዋህነታቸውን ወይም የመተማመንና የደህንነት ስሜታቸውን ሊነጥቃቸው የሚችል ምንም ነገር እንዳይደርስባቸው ለመከላከል አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋል።

በተመሳሳይም ሚስትና እናትም በጣም አስፈላጊና የተከበረ ድርሻ አላት። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋና ኢየሱስ ሕዝቦቻቸውን ከአደጋ በመጠበቅ ረገድ ያላቸውን ስሜት ለመግለጽ በእንስሳት ዓለም ውስጥ እናቶች ልጆቻቸው ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለመከላከል በደመ ነፍስ የሚወስዱትን እርምጃ በምሳሌነት ያቀርባል። (ማቴዎስ 23:37) ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘም አንዲት እናት ልጆቿን በቁርጠኝነት ከጉዳት የምትከላከል መሆን ይኖርባታል። በፍቅር በመገፋፋት ከራሷ በላይ የእነሱን ደህንነት ለማስቀደም ትጥራለች። ወላጆች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከልጆቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ሥልጣናቸውን ያለአግባብ አይጠቀሙም፣ እንዲሁም ጉልበተኝነት ወይም ማስፈራራት እንዲኖር አይፈቅዱም፤ ልጆቻቸውም ቢሆኑ እርስ በርሳቸው ባላቸው ግንኙነት እንዲህ ያሉ ባሕርያትን እንዲያሳዩ አይፈቅዱም።

እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ሌላውን በአክብሮት ሲይዝ በቤተሰቡ መካከል ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ይኖራል። ዊሊያም ፕሬንደርጋስት የተባሉ ደራሲ እንደሚከተለው ብለዋል:- “ሁሉም ወላጆች ከትንንሾቹም ሆነ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጆቻቸው ጋር በየዕለቱና ሳያሰልሱ ልብ ለልብ የማውራት ልማድ ሊኖራቸው ይገባል።” አክለውም “ይህ የፆታ ጥቃትን ለመከላከል ከሁሉ የተሻለ መፍትሔ ይመስላል” ብለዋል። መጽሐፍ ቅዱስም እንዲህ ዓይነት ያላሰለሰና ፍቅር የሚንጸባረቅበት የሐሳብ ግንኙነት ማድረግን ያበረታታል። (ዘዳግም 6:6, 7) ይህ መመሪያ በተግባር ሲውል፣ ቤት እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል በነፃነትና ያለ ሥጋት የልቡን አውጥቶ የሚናገርበት ቦታ ይሆናል።

እርግጥ ነው፣ የምንኖረው በጣም ክፉ በሆነ ዓለም ውስጥ በመሆኑ ከሁሉም ዓይነት ጥቃት ነፃ መሆን አይቻልም። ያም ሆኖ አስተማማኝ የእረፍት ቦታ የሆነ ቤት በጣም ትልቅ ልዩነት ያመጣል። አንዳንድ የቤተሰብ አባላት ከቤት ውጪ ጉዳት ቢደርስባቸው የሚያጽናናቸውና የሐዘናቸው ተካፋይ የሚሆን ሰው ለማግኘት ወዴት እንደሚሮጡ ያውቃሉ። እንዲህ ዓይነቱ ቤት በእርግጥም መሸሸጊያ፣ አምባና በዚህ በችግር በታመሰ ዓለም ውስጥ አስተማማኝ የእረፍት ቦታ ነው። ቤታችሁን እንዲህ ዓይነት ሥፍራ ለማድረግ የምታደርጉትን ጥረት አምላክ እንዲባርክላችሁ እንመኛለን!

^ አን.2 ይህ ጥንታዊ ግሪክኛ ቃል “ለዘመዶች ወይም ለቤተሰብ ደንታ ቢስ መሆን” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። በመሆኑም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን ጥቅስ “ለቤተሰቦቻቸው የተፈጥሮ ፍቅር የሌላቸው” በማለት አስቀምጦታል።