በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለምታገኘው ሃይማኖታዊ አገልግሎት ክፍያ ልትጠየቅ ይገባሃል?

ለምታገኘው ሃይማኖታዊ አገልግሎት ክፍያ ልትጠየቅ ይገባሃል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ለምታገኘው ሃይማኖታዊ አገልግሎት ክፍያ ልትጠየቅ ይገባሃል?

በብዙ አገሮች ክርስቲያን ነን የሚሉም ሆኑ ክርስቲያን ያልሆኑ ሌሎች ሃይማኖቶች ለሚያከናውኑት ሃይማኖታዊ አገልግሎቶች ገንዘብ ያስከፍላሉ። ከእነዚህ ሃይማኖታዊ አገልግሎቶች መካከል ጥምቀት፣ የሠርግና የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ይገኙበታል። ክፍያው በመቶ አንዳንድ ጊዜም በሺህ የሚቆጠር ብር ሊሆን ይችላል።

አንዳንድ ቀሳውስት ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችንና የቅስና አገልግሎቶችን ስለሚፈጽሙ እንዲሁም ሕግ ነክ ተቋማት በየዕለቱ የሚያከናውኑትን ሥራ በጸሎት ስለሚከፍቱ መንግሥት ደሞዝ ይከፍላቸዋል። ሕዝቡ እንዲህ ላሉት አገልግሎቶች አመስጋኝ ሲሆን አብያተ ክርስቲያናትም መክፈል የሚጠበቅባቸው ወጪዎች አሏቸው። ይሁን እንጂ ሃይማኖቶች ለሚያከናውኗቸው እንዲህ ላሉ አገልግሎቶች ክፍያ የሚጠይቁ መሆናቸውን ወይም ሕዝቡ የመክፈል ግዴታ እንዳለበት እንዲሰማው የሚያደርጉ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይደግፋል?

“የንግድ ቤት”?

ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የአይሁድ ሃይማኖታዊ ባለሥልጣናትና ሌሎች ሰዎች ሃይማኖታዊ በዓላት በተለይም የፋሲካ በዓል የሚከበርበትን ወቅት ትርፍ ለማጋበስ ይጠቀሙበት ነበር። ታዲያ ኢየሱስ ይህን ተግባር ደግፎ ነበር? በጭራሽ! እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “የገንዘብ ለዋጮችንም ሳንቲሞች በተነ፤ ጠረጴዛዎቻቸውንም ገለባበጠ” በማለት ይነግረናል። ኢየሱስ ሰዎቹን “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት ማድረጋችሁ ይብቃ!” ብሏቸው ነበር።—ዮሐንስ 2:14-16

በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ይኖር በነበረው በነቢዩ ሚክያስ ዘመን ተመሳሳይ ነገር ተፈጽሞ ነበር። የእስራኤል ሃይማኖታዊ መሪዎች ‘ፍትሕን ይንቁ’ እንዲሁም ካህናቱ ‘ለዋጋ ሲሉ ያስተምሩ’ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይህን ማድረጋቸው ሳያንስ “እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን?” እያሉ የአምላክ ድጋፍ እንዳላቸው ይናገሩ ነበር። (ሚክያስ 3:9, 11) ይሁንና ይሖዋ አምላክ በመካከላቸው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ አድራጎታቸውን ይጸየፍ የነበረ ከመሆኑም በላይ ይህንንም በነቢዩ አማካኝነት በማያሻማ መንገድ ግልጽ አድርጎላቸዋል።

በዛሬው ጊዜም በርካታ ሃይማኖታዊ መሪዎች ስግብግብነት የሚንጸባረቅባቸውን ተመሳሳይ ዘዴዎች የሚጠቀሙ ሲሆን የአምልኮ ቦታዎቻቸውን ‘የንግድ ቤቶች’ እያደረጓቸው ነው። እንዲያውም የሃይማኖት ድርጅቶች በጥቅሉ በንግድ ሥራ የተሰማሩ ከመሆኑም ሌላ ብዙውን ጊዜ ምስሎችንና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሃይማኖታዊ ዕቃዎችን በመሸጥ የጦፈ ንግድ ያካሂዳሉ። *1 ዮሐንስ 5:21

“በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ”

ኢየሱስ ሐዋርያቱ ምሥራቹን እንዲሰብኩ፣ ሕሙማንን እንዲፈውሱ ሌላው ቀርቶ ሙታንን እንዲያስነሱ ተልዕኮ በሰጣቸው ጊዜ “በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 10:7, 8) አዎን፣ የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች ለሚያከናውኑት አገልግሎት ገንዘብ አያስከፍሉም ነበር። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ራሱ ሌሎችን ሲያገለግል ክፍያ ባለመጠየቅ ምሳሌ ትቷል።

ሐዋርያው ጳውሎስ የኢየሱስን አርዓያ በመከተል አገልግሎቱን “ያለ ክፍያ” አከናውኗል። (1 ቆሮንቶስ 9:18) ጳውሎስ ገንዘብ በሚያስፈልገው ጊዜ ድንኳን ይሰፋ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 18:1-3) በመሆኑም ጳውሎስ ስለ ራሱም ሆነ አብረውት ያገለግሉ ስለነበሩ ሌሎች ሚስዮናውያን ሲናገር “እኛ እንደ ብዙዎቹ ሰዎች የአምላክን ቃል አንሸቃቅጥም” ለማለት ችሏል። (2 ቆሮንቶስ 2:17) ታዲያ የጉባኤ ወጪዎችን ለመሸፈን ምናልባትም ለአምልኮ የሚያገለግሉ ቦታዎችን ለመግዛት ወይም ለመከራየት የሚያስፈልገው ገንዘብ የሚገኘው እንዴት ነው?

‘አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ይወዳል’

የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ የሚያገኙት በፈቃደኝነት በሚደረጉ መዋጮዎች አማካኝነት ነው። “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ እያንዳንዱ ሰው ቅር እያለው ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ” የሚለውን መመሪያ በሥራ ላይ ያውላሉ። (2 ቆሮንቶስ 9:7) በዚህም ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮች ለጽሑፎቻቸው ወይም እንደ ጥምቀት፣ ሠርግና የቀብር ሥነ ሥርዓት ላሉት ሃይማኖታዊ አገልግሎቶች ገንዘብ አያስከፍሉም። ከዚህም በላይ አሥራት አይጠይቁም አሊያም በስብሰባ ቦታዎቻቸው ሙዳየ ምፅዋት አያዞሩም። ለዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ መዋጮ ማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በአምልኮ ቦታዎቻቸው ውስጥ ትኩረት በማይስብ ቦታ በተቀመጡ የመዋጮ ሣጥኖች ውስጥ ገንዘብ በመክተት ሥራውን መደገፍ ይችላል።

የይሖዋ ምሥክሮች በመላው ዓለም ላሉ የመንግሥት አዳራሾች፣ የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች፣ ቅርንጫፍ ቢሮዎችና ማተሚያዎች ሥራ ማስኬጃ እንዲሁም በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ የእምነት አጋሮቻቸውን ለመርዳት የሚያስፈልገውን ገንዘብ የሚያገኙት በፈቃደኝነት ከሚደረግ መዋጮ ነው። ኢየሱስ እንዳመሰገናት ድሃ መበለት ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች መስጠት የሚችሉት ትንሽ ሊሆን ይችላል። (ሉቃስ 21:2) ሌሎች ደግሞ ብዙ መስጠት ይችላሉ። ያም ሆነ ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መመሪያዎች ተከትለው አቅማቸው የፈቀደውን ያህል የሚሰጡ ሰዎች ውስጣዊ እርካታ፣ የአምላክን የተትረፈረፈ በረከት እንዲሁም እውነተኛ ደስታ ያገኛሉ።—የሐዋርያት ሥራ 20:35፤ 2 ቆሮንቶስ 8:12

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 በነሐሴ 2008 ንቁ! እትም ላይ የወጣውን “መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?—አምላክን በምስሎች ተጠቅመን ማምለክ ይኖርብናል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

ይህን አስተውለኸዋል?

● ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ውስጥ ንግድ ሲያካሂዱ የነበሩ ሰዎችን ምን ብሏቸው ነበር?—ዮሐንስ 2:14-16

● ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ላከናወናቸው ሃይማኖታዊ አገልግሎቶች ክፍያ ተቀብሎ ነበር?—2 ቆሮንቶስ 2:17

● ይሖዋን የሚያስደስተው በምን መንፈስ የሚሰጥ ስጦታ ነው?—2 ቆሮንቶስ 9:7

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የአባቴን ቤት የንግድ ቤት ማድረጋችሁ ይብቃ!”—ዮሐንስ 2:14-16