በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነፃ አውጥቷቸዋል

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነፃ አውጥቷቸዋል

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነፃ አውጥቷቸዋል

ኢየሱስ ክርስቶስ ያዳምጡት ለነበሩት ሰዎች “እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 8:32) የሚከተሉት ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት ይህ ዓይነቱ ነፃነት ከመናፍስታዊ ነገሮች በስተጀርባ ካሉትና ውሸታም እንዲሁም አታላይ ከሆኑት አጋንንት ነፃ መውጣትንም ይጨምራል።—ዮሐንስ 8:44

እያንዳንዱ ተሞክሮ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያለውን ነፃ የማውጣት ኃይል ጎላ አድርጎ ያሳያል። አዎን፣ ሰዎችን ነፃ የሚያወጣው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ለምን ራስህ አትመረምርም? ይህን ማድረግህ አያስቆጭህም።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ፎቶግራፎቹ ላይ የሚታዩት ሰዎች ባለታሪኮቹ አይደሉም

ሱዛና በብራዚል የቤተ መቅደስ ካህን ነበረች። የነበራትን ልዩ ኃይል ችግረኞችን ለመርዳት ልትጠቀምበት ትፈልግ ነበር። በተጨማሪም “በሞት ከተለየቻት እናቷ ጋር መነጋገር” ያስደስታት ነበር። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ “እናቷ” ሱዛና ራሷን እንድትገድልና በመንፈሳዊው ዓለም አብራት እንድትኖር ትለምናት ጀመር። ሱዛና ይህ በጣም ያስጨነቃት ከመሆኑም ሌላ ያቃዣት ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ሱዛና እና ባለቤቷ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። ‘ዲያብሎስን በመቃወም’ ረገድ ከባድ ትግል ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም ውሎ አድሮ ዲያብሎስ ‘ከእነሱ ሸሸ።’ (ያዕቆብ 4:7) አሁን ሰላም ያገኙ ሲሆን ሱዛናም እንደ ቀድሞው የሚያቃዣት ነገር የለም። “ይሖዋን የማመሰግንባቸው በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ከሁሉ በላይ የማመሰግነው ግን ከመንፈሳዊ ጨለማ ስላወጣን ነው” ስትል ጽፋለች።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል

ቲሞቲ በምዕራብ አፍሪካ የሚኖር ሲሆን መስማትም ሆነ መናገር የተሳነው ሰው ነው። * የሕክምና ዶክተሮች ሊረዱት ስላልቻሉ በተአምር እንፈውሳለን ወደሚሉ ሰዎች ሄደ፤ ይሁንና እነሱም ሊረዱት አልቻሉም። “በዚያ ባየሁት ማታለል ቅስሜ ተሰብሮ ነበር” ሲል ጽፏል። ከዚያም ቲሞቲ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ፤ እነሱም አምላክ ማንኛውንም ዓይነት የአካል ጉዳትና በሽታ ሙሉ በሙሉ የማስወገድ ዓላማ እንዳለው ገለጹለት። ቲሞቲ “በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ‘የደንቈሮም ጆሮዎች ይከፈታሉ። . . . የድዳውም አንደበት በደስታ ይዘምራል’ የሚለው ትንቢት የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት እጠብቃለሁ” ብሏል። (ኢሳይያስ 35:1-6) እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን በእጅ በሚያዝ የዲቪዲ ማጫወቻ በመጠቀም መስማት የተሳናቸው ሌሎች ሰዎችም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አውቀው እውነተኛ ነፃነት እንዲያገኙ በመርዳት ላይ ይገኛል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 አንዳንድ ሰሞች ተቀይረዋል

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል

ኤቨሊን በኢስቶንያ የምትኖር ስትሆን በመናፍስታዊ ነገሮች በጣም ተጠላልፋ ነበር። ኢየሱስ ያደርግ እንደነበረው ሰዎችን መፈወስ ፈለገች። በተለይ ደግሞ በጠና የታመሙትን እናቷን መርዳት ትፈልግ ነበር። በመሆኑም በፔንዱለም በመጠቀም ከባድ በሽታዎችን መርምራ ማወቅና ማከም የምትችልበትን መንገድ ተማረች። ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን መረመረች። ውጤቱስ? “ምን ያህል ተታልዬ እንደነበረ ተገነዘብኩ” ብላለች። “በመሆኑም መናፍስታዊ ጽሑፎቼንና ፔንዱለሞቼን አቃጠልኩ።” በአሁኑ ጊዜ ኤቨሊን ነፃ የሚያወጣውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለሌሎች ታስተምራለች።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ሜሪ የምትኖረው በፓፑዋ ኒው ጊኒ ከሚገኙት ደሴቶች በአንዱ ነው፤ በዚያ አካባቢ ሰዎች ሙታንን ይፈራሉ። ሜሪ በመንደሯ ሰው ከሞተ፣ ሌላ ሰው አልጋ ሥር ትተኛ ነበር፤ ይህን የምታደርገው ብቻዋን ከሆነች የሞተው ግለሰብ መንፈስ ጉዳት ያደርስብኛል ብላ ስለምትፈራ ነው። ከጊዜ በኋላ ግን ሙታን በሞት አንቀላፍተው እንደሚገኙና ትንሣኤ አግኝተው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር እስከሚጀምሩበት ጊዜ ድረስ በመቃብር ውስጥ እንዳሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማረች። (ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 11:11-14) በመሆኑም አሁን ሙታንን አትፈራም።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

አሊስያ በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ሲሆን ያደገችው በይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ውስጥ ነው፤ አሊስያ ከመናፍስታዊ ነገሮች ጋር የተያያዙ መጻሕፍትንና ፊልሞችን ማንበብና ማየት ጀመረች። በኋላ ላይ ግን ከዚያ ቀደም ስለተማረቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች በጥሞና ማሰብ ጀመረች። አሊስያ ‘ከይሖዋ ማዕድ እና ከአጋንንት ማዕድ ለመካፈል’ ስትሞክር እንደነበር በመገንዘቧ አካሄዷን አስተካከለች፤ አሁን በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና አላት።—1 ቆሮንቶስ 10:21