በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከማጨስ ጋር በተያያዘ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?

ከማጨስ ጋር በተያያዘ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?

የወጣቶች ጥያቄ

ከማጨስ ጋር በተያያዘ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?

ከዚህ በታች የቀረቡትን ምርጫዎች ተመልከትና የአንተን ስሜት እንደሚገልጽ በሚሰማህ ላይ ✔ አድርግ።

□ የማወቅ ጉጉት አለኝ

□ ውጥረት እንደበዛብኝ ይሰማኛል

□ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት እፈልጋለሁ

□ የሰውነቴ ክብደት ያሳስበኛል

ከላይ ከተዘረዘሩት ቢያንስ በአንዱ ላይ ምልክት አድርገህ ከሆነ ሲጋራ ከሚያጨሱ ወይም ለማጨስ ከሚያስቡ እኩዮችህ ጋር የሚያመሳስልህ ነገር አለ ማለት ነው። * ለምሳሌ ያህል፦

የማወቅ ፍላጎትን ማርካት። “ማጨስ ምን ስሜት እንደሚፈጥር ማወቅ ስለፈለግሁ በትምህርት ቤት ከአንዲት ልጅ ሲጋራ ተቀብዬ በድብቅ አጨስኩ።”​—ትሬሲ

ውጥረትን ማሸነፍና በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት። “በትምህርት ቤት ያሉ ልጆች ውጥረት ሲበዛባቸው ሲጋራ እንደሚያስፈልጋቸው ይሰማቸዋል፤ ትንሽ ሳብ ካደረጉ በኋላ በረጅሙ ተንፍሰው ‘በቃ አሁን የፈለግኩትን ነገር መሥራት እችላለሁ!’ ይላሉ። እኔም ውጥረት ሲያጋጥመኝ እንዲህ ማድረግ ያምረኛል።”—ኒኪ

ክብደት መቀነስ። “አንዳንድ ሴቶች የሚያጨሱት ሸንቃጣ እንደሆኑ መኖር ስለሚፈልጉ ነው፤ በምግብ ክብደትን ከመቆጣጠር ይልቅ ይህ ዘዴ በጣም ቀላል ነው!”​—ሳማንታ

ሲጋራ የምታጨሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ይሁንም አይሁን ሲጋራውን ከመለኮስህ በፊት ቆም ብለህ አስብ። መንጠቆ ላይ የተቀመጠን ምግብ ለመብላት እንደሚጓጓ ዓሣ አትሁን። ዓሣው ትንሽ ጥቅም እንደሚያገኝ እሙን ነው፤ ይሁን እንጂ ሕይወቱን ስለሚያጣ አተርፍ ባይ አጉዳይ ይሆናል! አንተ ግን የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተከተል፤ እንዲሁም ‘በትክክል የማሰብ ችሎታህን’ ተጠቀምበት። (2 ጴጥሮስ 3:1) እስቲ ቀጥሎ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ስጥ።

ከማጨስ ጋር በተያያዘ ምን ያህል ታውቃለህ?

ቀጥሎ ለቀረቡት ጥያቄዎች እውነት ወይም ሐሰት በማለት መልስ ስጥ።

ሀ. ․․․ ማጨስ ውጥረትን ይቀንሳል።

ለ. ․․․ የሳብኩትን ጭስ ሙሉ በሙሉ ወደ ውጭ አወጣዋለሁ ማለት እችላለሁ።

ሐ. ․․․ ዕድሜዬ እስካልገፋ ድረስ ባጨስ ጤንነቴ አይጎዳም።

መ. ․․․ ማጨስ ተቃራኒ ፆታን ይበልጥ ለመማረክ ያስችለኛል።

ሠ. ․․․ ባጨስ ራሴን እንጂ ማንንም አልጎዳም።

ረ. ․․․ የእኔ ማጨስ አለማጨስ አምላክን አያሳስበውም።

መልሶቹ

ሀ. ማጨስ ውጥረትን ይቀንሳል።​—ሐሰት። ማጨስ ከማቆም ጋር ተያይዘው የሚመጡትን ችግሮች ሲጋራ በማጨስ ለጊዜው ማስታገሥ ይቻል ይሆናል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በሲጋራ ውስጥ ያለው ኒኮቲን በውጥረት ጊዜ የሚፈጠሩ ሆርሞኖችን መጠን ከፍ እንደሚያደርገው የሳይንስ ሊቃውንት ደርሰውበታል።

ለ. የሳብኩትን ጭስ ሙሉ በሙሉ ወደ ውጭ አወጣዋለሁ ማለት እችላለሁ።​—ሐሰት። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ወደ ውስጥ በምትስበው የሲጋራ ጭስ ውስጥ ከሚገኙት ንጥረ ነገሮች ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት በሰውነትህ ውስጥ ይቀራሉ።

ሐ. ዕድሜዬ እስካልገፋ ድረስ ባጨስ ጤንነቴ አይጎዳም።​—ሐሰት። አንድ ሲጋራ ባጨስክ ቁጥር በጤናህ ላይ ጉዳት የመድረሱ አጋጣሚ እየጨመረ መሄዱ እንዳለ ሆኖ አንዳንዶቹ ችግሮች ወዲያውኑ ሊከሰቱ ይችላሉ። አንዳንድ ሰዎች ገና የመጀመሪያውን ሲጋራ እንዳጨሱ ሱስ ይይዛቸዋል። ሳንባህ አየር የመያዝ አቅሙ የሚቀንስ ሲሆን ቶሎ የማይለቅ ሳል ሊይዝህ ይችላል። እንዲሁም ያለ ዕድሜህ ቆዳህ ይሸበሸባል። በተጨማሪም ማጨስ ስንፈተ ወሲብን፣ በትካዜ መዋጥን እንዲሁም የመንፈስ ጭንቀትን ሊያስከትል ይችላል።

መ. ማጨስ ተቃራኒ ፆታን ይበልጥ ለመማረክ ያስችለኛል።—ሐሰት። ሎይድ ጆንስተን የተባሉ ተመራማሪ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ሲጋራ የሚያጨሱ ልጆች “ተቃራኒ ፆታ ባላቸው አብዛኞቹ ልጆች ዘንድ ተፈላጊነታቸው [እንደሚቀንስ]” ደርሰውበታል።

ሠ. ባጨስ ራሴን እንጂ ማንንም አልጎዳም።​—ሐሰት። ከሚያጨሱ ሰዎች የሚወጣው የሲጋራ ጭስ በየዓመቱ በሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ነው፤ ስለዚህ አንተ የምታጨሰው ሲጋራ ቤተሰቦችህን፣ ጓደኞችህን አልፎ ተርፎም የቤት እንስሳትህን ይጎዳል።

ረ. የእኔ ማጨስ አለማጨስ አምላክን አያሳስበውም።​—ሐሰት። አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች “ሥጋን . . . ከሚያረክስ ነገር ሁሉ” ራሳቸውን ማንጻት አለባቸው። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ማጨስ ሰውነትን እንደሚያረክስ ምንም ጥርጥር የለውም። ሲጋራ በማጨስ ራስህንም ሆነ ሌሎችን የምትጎዳና ንጽሕናህን የምታረክስ ከሆነ የአምላክ ወዳጅ መሆን አትችልም።​—ማቴዎስ 22:39፤ ገላትያ 5:19-21

ተጽዕኖዎችን መቋቋም የሚቻልበት መንገድ

ታዲያ አንድ ልጅ እንድታጨስ ቢጋብዝህ ምን ታደርጋለህ? ብዙውን ጊዜ “አመሰግናለሁ፣ እኔ አላጨስም” በማለት ቀላል ሆኖም ቁርጥ ያለ መልስ መስጠት ይበቃል። ልጁ መጎትጎቱን ቢቀጥል አልፎ ተርፎም ቢያሾፍብህ እንኳ ውሳኔው የአንተ መሆኑን አስታውስ። እንዲህ ልትል ትችላለህ፦

● “ሲጋራ ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ ስለተረዳሁ ላለማጨስ ወስኛለሁ።”

● “ወደፊት ልደርስባቸው ያሰብኳቸው ወሳኝ ግቦች ስላሉኝ ሳንባዬን እፈልገዋለሁ።”

በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሱት ወጣቶች ሁሉ አንተም እንድታጨስ ከፍተኛው ግፊት የሚመጣብህ ከውስጥህ እንደሆነ ትገነዘብ ይሆናል። ሁኔታው ይህ ከሆነ ከታች በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ በማሰላሰል ከውስጥህ የሚመጣውን ግፊት መቋቋም ትችላለህ፦

● ማጨሴ የሚያስገኝልኝ ጥቅም አለ? ለምሳሌ ያህል፣ ከእኩዮቼ ጋር አንድ የሚያደርጉን ሌሎች ነገሮች ሳይኖሩ ሲጋራ ስላጨስኩ ብቻ በእነሱ ዘንድ ተቀባይነት አገኛለሁ? ደግሞስ ጤንነቴ ሲጎዳ ማየት በሚያስደስታቸው ልጆች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መፈለጌ ምን ይባላል?

● ማጨስ በገንዘቤና በጤናዬ ላይ ምን ያህል ኪሳራ ያስከትልብኛል? ሌሎች ለእኔ ያላቸው አክብሮትስ ምን ያህል ይቀንሳል?

● ለሲጋራ ስል ከአምላክ ጋር ያለኝን ወዳጅነት መሥዋዕት ማድረግ እፈልጋለሁ?

ይሁንና ቀድሞውንም በሱስ ተጠምደህ ከሆነስ? ከሱስህ ለመላቀቅ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ማቆም የምትችልበት መንገድ

1. ራስህን አሳምን። ለማቆም ያነሳሱህን የራስህን ምክንያቶች በጽሑፍ አስፍር፤ ከዚያም እነዚህን ምክንያቶች በየጊዜው መለስ እያልክ ተመልከታቸው። በአምላክ ፊት ንጹሕ ሆነህ ለመገኘት ያለህ ፍላጎት ለእርምጃ እንድትነሳሳ የማድረግ ከፍተኛ ኃይል አለው።​—ሮም 12:1፤ ኤፌሶን 4:17-19

2. እርዳታ ጠይቅ። በሽታውን የደበቀ መድኃኒት አይገኝለትምና በድብቅ የምታጨስ ከሆነ ራስህን ግልጽ የምታደርግበት ጊዜ አሁን ነው። በመሆኑም ተደብቀሃቸው ለነበሩት ሰዎች ለማቆም እንዳሰብክና የእነሱን እርዳታ እንደምትፈልግ ንገራቸው። አምላክን ለማገልገል የምትፈልግ ከሆነ ደግሞ እሱ እንዲረዳህ ጸልይ።​—1 ዮሐንስ 5:14

3. የምታቆምበትን ቀን ወስን። ለዝግጅት የሚሆን ሁለት ሳምንት ወይም ከዚያ ያነሰ ጊዜ መድብና በቀን መቁጠሪያህ ላይ የወሰንከውን ዕለት ምልክት አድርግበት። እንዲሁም የምታቆምበትን ቀን ለቤተሰቦችህና ለጓደኞችህ ንገራቸው።

4. በደንብ ፈትሽ፤ መወገድ ያለበትንም አስወግድ። ለማቆም የወሰንክበት ቀን ከመድረሱ በፊት ክፍልህን፣ መኪናህንና ልብስህን በደንብ ፈትሸህ ምንም ሲጋራ አለመኖሩን አረጋግጥ። ካገኘህ አስወግድ። ላይተሮችን፣ ክብሪቶችንና መኮስተሪያዎችን አስወግድ።

5. ከማቆም ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ለመቋቋም ጥረት አድርግ። የፍራፍሬ ጭማቂ ወይም ውኃ በብዛት ጠጣ፤ እንዲሁም ለእንቅልፍ ተጨማሪ ጊዜ መድብ። በማቆምህ ምክንያት የሚያጋጥምህ መጥፎ ስሜት ጊዜያዊ መሆኑንና ጥቅሞቹ ግን ዘላቂ መሆናቸውን አስታውስ!

6. እንዲያገረሽብህ ከሚያደርጉ ነገሮች ራቅ። አጭስ አጭስ የሚል ስሜት ከሚፈጥሩብህ ቦታዎችና ሁኔታዎች ራቅ። በተጨማሪም ከሚያጨሱ ሰዎች ጋር ያለህን ግንኙነት ማቋረጥ ሊያስፈልግህ ይችላል።​—ምሳሌ 13:20

7. ሰበብ አስባብ አትፍጠር። “አንድ ጊዜ ብቻ ሳብ ባደርግ ምንም ችግር የለውም” እያልክ ራስህን አታታል። እንዲህ ያለ ሰበብ ማቅረብ ብዙውን ጊዜ ሱሱ ሙሉ በሙሉ እንዲያገረሽብህ ያደርጋል።​—ኤርምያስ 17:9

አትሞኝ

የትንባሆ ኩባንያዎች ለማስታወቂያ በየዓመቱ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያወጣሉ። ይህን ሁሉ ወጪ የሚያወጡት በከንቱ ይመስልሃል? ብዙ ወጣቶች በመደለያው ተታለው በወጥመዱ እንደሚያዙና ነገ ከነገ ወዲያ ቋሚ ደንበኛ እንደሚሆኗቸው በደንብ ስለሚያውቁ ነው።

የትንባሆ ኩባንያ ባለቤቶች ኪስህ እንዲገቡ አትፍቀድ። በማባበያቸው ተታለህ ወጥመዳቸው ውስጥ የምትወድቅላቸው ሞኝ ነህ እንዴ? እነሱም ሆኑ የሚያጨሱ እኩዮችህ እንድታጨስ የሚገፋፉህ ለአንተ ተቆርቁረውልህ አይደለም። እነሱን ከመስማት ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምክር በማዳመጥ ለአንተ “የሚበጅህ” ምን እንደሆነ ተማር።​—ኢሳይያስ 48:17

www.watchtower.org/​ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 ይህ ርዕሰ ትምህርት የሚያተኩረው ሲጋራ በማጨስ ላይ ቢሆንም በትምህርቱ ላይ የቀረቡት ከማጨስ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችና አደጋዎች ትንባሆ በሚያኝኩ ላይም ይደርሳሉ።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

እኩዮችህ ምን ይላሉ?

“አንድ ሰው ሲጋራ ለምን እንደማላጨስ ቢጠይቀኝ ‘ሳንባዬን ማቃጠልና ዕድሜዬን ማሳጠር ስለማልፈልግ ነው’ እለዋለሁ።”

“አንድ ሰው ሲጋራ እንኪ ብሎ ቢሰጠኝ ‘አይ አልፈልግም’ እለዋለሁ። ሊጫነኝ ቢሞክር ‘የራሴን ምርጫ የማድረግ መብት የለኝም? ያውም በዚህ ዘመን የሰውን ምርጫ መጋፋት በጣም ያሳፍራል!’ እለዋለሁ።”

[ሥዕሎች]

ቤንጃሚን

ሄዘር

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ይህን ታውቅ ነበር?

የሚታኘክ ትንባሆን የመሰሉ ጭስ አልባ ትንባሆዎች ከሲጋራ የበለጠ ኒኮቲን ወደ ሰውነት የሚያስገቡ ሲሆን ተጠቃሚው ለጉሮሮና ለአፍ ካንሰር ያለውን ተጋላጭነት የሚጨምሩ ከ25 በላይ ካንሰር አምጪ ንጥረ ነገሮችን ይዘዋል።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ወላጆችህን ለምን አትጠይቃቸውም?

የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም ቀላል የሚሆነው አስቀድመህ ከተዘጋጀህ ነው። አንድ ሰው ሲጋራ እንድታጨስ ቢጋብዝህ መልስ ለመስጠት የተዘጋጀህ እንድትሆን ወላጆችህ ከአንተ ጋር ልምምድ እንዲያደርጉ ለምን አትጠይቃቸውም? ወላጅህ እንድታጨስ እንደሚገፋፋህ እኩያህ መሆን ይችላል። ፍንጭ፦ ምን ብለህ መልስ እንደምትሰጥ የሚረዱ ጠቃሚ ሐሳቦችን ለማግኘት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 በገጽ 132 እና 133 ላይ የሚገኘውን “የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም” የሚለውን ሣጥን ተጠቀም።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መንጠቆ ላይ የተቀመጠን ምግብ ለመብላት እንደሚጓጓ ዓሣ አንድ ሰውም ለማጨስ ቢነሳሳ አተርፍ ባይ አጉዳይ ይሆናል