በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆች ምን ይላሉ?

ወላጆች ምን ይላሉ?

ወላጆች ምን ይላሉ?

ዕድሜው ለትምህርት ያልደረሰ ልጅ ካላችሁ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟችሁ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ልጃችሁ እልኸኛ ሲሆን ምን ማድረግ ይኖርባችኋል? ልጃችሁ ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር ለይቶ እንዲያውቅ ልታስተምሩት እንዲሁም ሚዛናዊ የሆነ ተግሣጽ ልትሰጡት የምትችሉት እንዴት ነው? አንዳንድ ወላጆች እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዴት እንደተወጧቸው እስቲ እንመልከት።

እልኸኝነት

“አንድ ልጅ አስቸጋሪ በሚሆንበት በሁለት ዓመት ዕድሜው አካባቢ የሚፈልገው ሁሉ እንዲደረግለት ይጠብቃል። ልጃችን እንዲህ ዓይነት ችግር ነበረበት። የፈለገው ነገር ካልተደረገለት ዕቃዎችን ይወረውራል። የመጀመሪያ ልጃችን ስለነበረ እንዲህ ያለ የእልኸኝነት ባሕርይ ሲያሳይ ምን ማድረግ እንዳለብን አናውቅም ነበር። እንዲህ ያለው ጠባይ የተለመደ እንደሆነ ሌሎች ሰዎች ቢነግሩንም ይህ ብዙም አልረዳንም።”​—ሱዛን፣ ኬንያ

“ልጃችን በሁለት ዓመቷ ወለሉ ላይ ተኝታ የመጮህ፣ የማልቀስና የመንፈራገጥ ልማድ ነበራት። . . . ሁኔታው ትዕግሥትን የሚፈትን ነበር! በዚያ ሰዓት ከእሷ ጋር ለመነጋገር መሞከር የማይቻል ነገር ነበር። በመሆኑም እኔና ባለቤቴ እልዃ እስኪበርድላት ድረስ ክፍሏ ውስጥ እንድትቆይ እንነግራታለን፤ ከዚያም ስትረጋጋ ተመልሳ መምጣት እንደምትችልና በጉዳዩ ላይ እንደምንወያይበት ረጋ ብለን እንገልጽላታለን። ከተረጋጋች በኋላ አንዳችን ወደ ክፍሏ በመሄድ ይህ ጠባይዋ ተገቢ ያልሆነው ለምን እንደሆነ እናስረዳታለን። ይህ ዘዴ ስኬታማ ሆኖ አግኝተነዋል። እንዲያውም በአንድ ወቅት አምላክ ይቅር እንዲላት ስትጸልይ ሰምተናታል። ከጊዜ በኋላ እልኸኛ መሆኗን እየተወች የመጣች ሲሆን በመጨረሻም እንዲህ ማድረጓን ተወች።”​—ዮላንዳ፣ ስፔን

“ሕፃናት፣ ከተሰጣቸው ገደብ ምን ያህል አልፈው መሄድ እንደሚችሉ ለማየት ወላጆቻቸውን ይፈትናሉ። ሕፃኑ በግልጽ ከልክላችሁት የነበረውን ነገር ሲያደርግ ዝም ብትሉት ግራ ታጋቡታላችሁ። ጥብቅ እና ቃላችንን የማንለዋውጥ መሆናችን ልጆቻችን፣ በመጮኽ የፈለጉትን ነገር ማግኘት እንደማይችሉ ቀስ በቀስ እንዲማሩ እንዳስቻላቸው ተገንዝበናል።”​—ኒል፣ ብሪታንያ

ተግሣጽ

“አንድ ሕፃን ከአምስት ዓመት በታች ከሆነ የምንናገረውን ነገር ምን ያህል እንደተረዳን ማወቅ አስቸጋሪ ነው። በዚህ ጊዜ መፍትሔው መደጋገም ነው። በአካላዊ እንቅስቃሴ በመጠቀምና ጠንከር ባለ መንገድ በመናገር ሐሳባችሁን ደግማችሁ ደጋግማችሁ መግለጽ ይኖርባችኋል።”​—ሴርዥ፣ ፈረንሳይ

“አራቱም ልጆቻችን ያደጉበት ሁኔታ ተመሳሳይ ቢሆንም እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ልዩ ባሕርይ አላቸው። አንዷ ልጃችን እንዳዘንንባት ማወቋ ብቻ ያስለቅሳታል፤ ሌላዋ ግን ካስቀመጥነው ገደብ ምን ያህል አልፋ መሄድ እንደምትችል ለማየት ትፈትነናለች። በአንዳንድ ሁኔታዎች ኮስተር ብሎ ማየት ወይም ቆጣ ብሎ መናገር ይበቃል፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ልጆቻችንን መቅጣት ያስፈልገናል።”​—ናታን፣ ካናዳ

“በአቋም መጽናት አስፈላጊ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ወላጅ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን የሚል ወይም ግትር መሆን አይኖርበትም። አንዳንድ ጊዜ ልጁ በጥፋቱ ከልቡ ከተጸጸተ ምክንያታዊ መሆንና ቀለል ያለ ተግሣጽ መስጠት የተሻለ እንደሆነ ይሰማናል።”​—ማቲዩ፣ ፈረንሳይ

“ብዙ መመሪያዎችን ላለማውጣት እጥራለሁ፤ ይሁን እንጂ ያወጣኋቸው መመሪያዎች ያላንዳች ድርድር ሊፈጸሙ ይገባል። ሦስት ዓመት የሆነው ልጄ አለመታዘዙ የሚያስከትለውን ውጤት ያውቃል፤ ይህም ባሕርይውን እንዲያስተካክል ይረዳዋል። እውነት ነው፣ በደከመኝ ሰዓት ጥፋቶቹን ችላ ብዬ ማለፍ ይቀል ይሆናል። ቃሌን ለመጠበቅ ስል ግን እርምጃ እወስዳለሁ። የተናገሩትን ቃል መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ነው!”​—ናታሊ፣ ካናዳ

የተናገሩትን ቃል መጠበቅ

“ትንንሽ ልጆች አንድ ወላጅ ቃሉን ሳይጠብቅ የቀረባቸውን ጊዜያት ሁሉ በአእምሯቸው ውስጥ መዝግበው የመያዝ ችሎታ ያላቸው ይመስላል።”​—ሚልተን፣ ቦሊቪያ

“አንዳንድ ጊዜ ልጄ፣ የምንሰጠው መልስ ተመሳሳይ መሆን አለመሆኑን ለመፈተን ሲል አንድን ጉዳይ በተለያየ መንገድ ይጠይቃል። ወይም ደግሞ እኔ አንድ ነገር ከተናገርኩ በኋላ እናቱ ሌላ ነገር ከተናገረች ቃላችን አንድ አለመሆኑን ተመልክቶ አጋጣሚውን የፈለገውን ለማድረግ ሊጠቀምበት ይሞክራል።”​—አንሄል፣ ስፔን

“ስሜቴ ጥሩ ከሆነ ልጄ ቢያጠፋም ችላ ብዬ አልፈዋለሁ፤ ተበሳጭቼ ባለሁበት ጊዜ ግን በኃይል እቀጣዋለሁ። እንዲህ ማድረጌ መጥፎ ጠባዩን ከማባባስ በቀር የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ተገንዝቤያለሁ።”​—ጊኦንኦክ፣ ኮሪያ

“ትንንሽ ልጆች፣ ዛሬ ‘ስህተት ነው’ ያልናቸው ነገር ምንጊዜም ስህተት እንደሆነ እንዲገነዘቡ ማድረግ አስፈላጊ ነው።”​—አንቶንዩ፣ ብራዚል

“ወላጆች ቃላቸው የሚለዋወጥ ከሆነ ልጁ፣ አባቱና እናቱ አንድ አቋም እንደሌላቸውና ውሳኔያቸው እንደ ስሜታቸው ሊለዋወጥ እንደሚችል ያስባል። ይሁን እንጂ ወላጆች ያወጡትን መመሪያ ሁልጊዜ የሚያስፈጽሙ ከሆነ ልጆቻቸው ስህተት እንደሆነ የተነገራቸው ነገር ምንጊዜም ስህተት እንደሆነ ያውቃሉ። ይህ ደግሞ ወላጆች፣ ልጆቻቸው የደኅንነት ስሜት እንዲያድርባቸውና እንደሚወደዱ እንዲሰማቸው የሚያደርጉበት አንዱ መንገድ ነው።”​—ጊልማር፣ ብራዚል

“ወላጆች፣ ልጆቻቸው የጠየቁትን ነገር ከመፍቀድ በቀር ሌላ አማራጭ የሌላቸው በሚመስልበት ጊዜ (ለምሳሌ ሌሎች ሰዎች በሚኖሩበት ወቅት) ልጆች አጋጣሚውን ለመጠቀም ይሞክራሉ። መልሴ አይሆንም የሚል ከሆነ ገና ከመጀመሪያው ይህንኑ የማሳውቀው ሲሆን በተደጋጋሚ ቢለምነኝም ሐሳቤን እንደማልቀይር ለልጄ በግልጽ እነግረዋለሁ።”​—ቻኝሱክ፣ ኮሪያ

“ሁለቱም ወላጆች አቋማቸው አንድ ሊሆን ይገባል። እኔና ባለቤቴ በሆነ ነገር ላይ ካልተስማማን ጉዳዩን ለብቻችን እንነጋገርበታለን። ልጆች ወላጆቻቸው በአንድ ጉዳይ ላይ እንዳልተስማሙ ማስተዋል ስለሚችሉ ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው የፈለጉትን ለማድረግ ይሞክራሉ።”​—ሄሱስ፣ ስፔን

“አንድ ልጅ፣ ወላጆቹ አንድነት እንዳላቸውና እሱ እንደፈለገው ሊጠመዝዛቸው እንደማይችል ሲያውቅ የደኅንነት ስሜት ይሰማዋል። ታዛዥ መሆኑ ወይም አለመሆኑ ምን እንደሚያስከትል ያውቃል።”​—ዳማሪስ፣ ጀርመን

“እኔና ባለቤቴ፣ ለልጃችን አንድ ነገር እናደርግልሻለን ካልናት የተናገርነውን በመፈጸም ቃላችንን እንጠብቃለን። እንዲህ ማድረጋችን የገባነውን ቃል እንደማናጥፍ እንድትተማመን አድርጓታል።”​—ሄንድሪክ፣ ጀርመን

“አሠሪዬ ከሥራዬ ጋር በተያያዘ የሚጠበቅብኝን ነገር በተመለከተ በየጊዜው ሐሳቡን የሚለዋውጥ ከሆነ መበሳጨቴ አይቀርም። ልጆችም ቢሆን እንደዚህ ይሰማቸዋል። ወላጆቻቸው ያወጧቸውን መመሪያዎች በግልጽ ማወቃቸውና መመሪያዎቹ እንደማይለዋወጡ መገንዘባቸው የደኅንነት ስሜት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። በተጨማሪም አለመታዘዝ መዘዝ እንደሚያስከትልና ከዚያም ማምለጥ እንደማይችሉ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል።”​—ግሌን፣ ካናዳ

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አዎ ካላችሁ አዎ ይሁን፣ አይደለም ካላችሁ አይደለም ይሁን።”​—ያዕቆብ 5:12

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አጭር የቤተሰብ ታሪክ

ያልተጠበቀ እርግዝና​—ራሳችንን ከሁኔታው ጋር ማስማማት

ቶም እና ዩንሂ ሃን እንደተናገሩት

ቶም፦ ባለቤቴ ዩንሂ እንደፀነሰች ያወቅነው ገና በተጋባን በስድስት ወራችን ነበር። ዩንሂን ለማጽናናትና ለማበረታታት ስል የተረጋጋሁ መስዬ ለመታየት ብጥርም ውስጤ በጣም ተረብሾ ነበር!

ዩንሂ፦ በጭንቀት ተውጬና ፈርቼ ነበር! ሥራዬ ማልቀስ ብቻ ሆኖ ነበር፤ እናት ለመሆን ዝግጁ እንደሆንኩም ሆነ ብቃቱ እንዳለኝ አልተሰማኝም።

ቶም፦ እኔም አባት ለመሆን ዝግጁ እንደሆንኩ አልተሰማኝም። ይሁን እንጂ ከሌሎች ወላጆች ጋር ስንነጋገር ያልተጠበቀ እርግዝና ካሰብነው በላይ በጣም የተለመደ ነገር መሆኑን ተገነዘብን። በተጨማሪም ሌሎች ወላጆች፣ አባትና እናት መሆን ስለሚያስገኘው ደስታ ሲነግሩን መስማታችን ረድቶናል። ቀስ በቀስ ፍርሃቴና ጥርጣሬዬ ተወግዶልኝ ልጄን በጉጉት መጠባበቅ ጀመርኩ።

ዩንሂ፦ አማንዳ ከተወለደች በኋላ አዲስ ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጠሙን። አማንዳ ያለማቋረጥ ታለቅስ ስለነበር ለብዙ ሳምንታት እንቅልፍ በዓይኔ አልዞረም። የምግብ ፍላጎት አልነበረኝም፤ ከዚህም የተነሳ በጣም ይደክመኝ ነበር። መጀመሪያ ላይ ከሰዎች ጋር መሆን አልፈልግም ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ከሌሎች ራሴን በማግለል ቤት ውስጥ መቀመጤ ምንም እንዳልጠቀመኝ ተገነዘብኩ። ስለዚህ እንደ እኔው ካሉ እናቶች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ጀመርኩ። ይህም ከእነሱ ጋር ስለ ሁኔታዬ እንድወያይና የሚያሳስቡ ሁኔታዎች የሚያጋጥሙኝ እኔ ብቻ እንዳልሆንኩ እንድገነዘብ ረዳኝ።

ቶም፦ የቤተሰባችን የዕለት ተዕለት ልማዶች እንዳይስተጓጎሉ ጥረት አደረግሁ። ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን እኔና ዩንሂ ዘወትር በአገልግሎት ለመካፈልና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔ አድርገን ነበር። በተጨማሪም ልጅ ማሳደግ ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን አንዳንዶቹ ወጪዎች ደግሞ ያልተጠበቁ ናቸው። ለተጨማሪ ውጥረት ሊዳርገን ወደሚችል ዕዳ ውስጥ እንዳንገባ በገቢያችን ልክ ለመኖር ጥረት እናደርግ ነበር።

ዩንሂ፦ ሕፃናት ሊያስቸግሩ ስለሚችሉ በአገልግሎት መካፈል ከባድ እንደሚሆንብኝ ተሰምቶኝ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሰዎች፣ ልጆችን ማየት ያስደስታቸዋል። ይህን መገንዘቤ በአገልግሎት መካፈሌን እንድቀጥልና ስለ ልጄ ይበልጥ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረኝ ረድቶኛል።

ቶም፦ መጽሐፍ ቅዱስ “ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው” ይላል፤ አክሎም ‘በቸርነቱ የተገኙ’ እንደሆኑ ይናገራል። (መዝሙር 127:3) ይህ ሐሳብ፣ ልጅ ውድ ስጦታ እንደሆነ ያስታውሰኛል። ያገኘኸውን ስጦታ በፈለግኸው ዓይነት መንገድ የመጠቀም ምርጫ አለህ፤ በጥበብ ልትጠቀምበት ወይም ልታባክነው ትችላለህ። አንድ ልጅ የሚያልፍበት እያንዳንዱ የእድገት ደረጃ የራሱ የሆነ ልዩ ገጽታ እንዳለው እየተማርኩ ሲሆን ልጄ እያንዳንዱን የእድገት ደረጃ ስታልፍ የራሴን አስተዋጽኦ ማድረግ እፈልጋለሁ፤ ምክንያቱም አጋጣሚው አንዴ ካመለጠኝ መልሼ ላገኘው አልችልም።

ዩንሂ፦ አንዳንድ ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ ያልታሰቡ ሁኔታዎች ይገጥሙናል፤ ያም ሆኖ ሳያስቡበት ልጅ መውለድ መጥፎ ገጠመኝ አይደለም። አሁን አማንዳ ስድስት ዓመቷ ሲሆን ያለ እሷ ሕይወቴ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ይቸግረኛል።

[ሥዕል]

ቶምና ዩንሂ ከልጃቸው ከአማንዳ ጋር