በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ያለ ደም የሚሰጡ አማራጭ ሕክምናዎች

ያለ ደም የሚሰጡ አማራጭ ሕክምናዎች

ከአርባ ከሚበልጡ አገሮች የተውጣጡ እውቅ ባለሙያዎች ከግንቦት 20-22, 2011 በተካሄደው የአውሮፓ የልብና የደም ሥር ቀዶ ጥገና ማኅበር 60ኛ ኢዮቤልዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ለመገኘት በሞስኮ ተሰብስበው ነበር። አንድ የሩስያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ “ሐኪሞች ለእንዲህ ዓይነቱ ጉባኤ የሚሰጡት ግምት አትሌቶች ለኦሎምፒክ ከሚሰጡት አይተናነስም” ብሏል።

ስብሰባው በተደረገባቸው በሦስቱም ቀናት የብዙ ሰዎችን ትኩረት የሳበው ያለ ደም የሚሰጡ አማራጭ ሕክምናዎችን አስመልክቶ መረጃ የሚሰጠው ዴስክ ነበር። ይህን ዴስክ ያዘጋጀው የይሖዋ ምሥክሮች የሆስፒታል መረጃ አገልግሎት ነው። ሐኪሞች ወደዚህ ዴስክ በመምጣት በዚህ ወሳኝ ርዕስ ዙሪያ የተዘጋጁ በመቶ የሚቆጠሩ መጻሕፍትን፣ ዲቪዲዎችን፣ የሕክምና ጽሑፎችንና ልዩ ልዩ መረጃዎች የያዙ ፋይሎችን ወስደዋል። በተለይ ያለ ደም የሚሰጡ አማራጭ የሕክምና ዘዴዎች—ቀላል፣ አስተማማኝና ውጤታማ * የተባለው የቪዲዮ ፊልም ያለበት ዲቪዲ በብዙዎች ዘንድ ተፈላጊነት ነበረው።

ዴስኩን የጎበኙ በርካታ ሐኪሞች በቀዶ ሕክምና ወቅት ብዙ ደም እንዳይፈስ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ተስማምተዋል። በስብሰባው ላይ ንግግር ያቀረቡ ከጣሊያን የመጡ አንድ የልብ ቀዶ ሕክምና ባለሙያ፣ የይሖዋ ምሥክሮችን በደንብ እንደሚያውቋቸውና 70 ለሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ሕሙማን በተሳካ ሁኔታ ያለ ደም የልብ ቀዶ ሕክምና እንዳደረጉ ተናግረዋል። በተጨማሪም በክሊኒካቸው ውስጥ ያለ ደም ቀዶ ሕክምና ማድረግ በጣም የተለመደ ነገር መሆኑን ጠቅሰዋል። በጀርመን የበርሊን የልብ ተቋም ፕሮፌሰር የሆኑ አንድ ሐኪም ለራሳቸውና ለሥራ ባልደረባቸው አንድ አንድ ዲቪዲ ወስደዋል። ሐኪሙ፣ 2.5 ኪሎ ግራም ለሚመዝን ሕፃን በቅርቡ ያለ ደም ቀዶ ጥገና እንዳደረጉና ክሊኒካቸው ከዚያ ያነሰ ክብደት ላላቸው ሕፃናት ሳይቀር ያለ ደም የልብ ቀዶ ጥገና እንዳደረገ በስብሰባው ላይ ለተገኙት ሰዎች ተናግረዋል።

የሞስኮው ስብሰባ ከተደረገ ከአንድ ወር በኋላ በሩሲያ ሰሜን ምዕራብ አካባቢ የሚገኙ ማደንዘዣ የሚሰጡ ባለሙያዎች (አኒስቲዚዮሎጂስት) እና ልዩ ክትትል የሚያስፈልጋቸውን ሕሙማንን የሚረዱ ሐኪሞች (ኢንቴንሲቭ ኬር ፊዚሽያን) አራተኛውን የቤሎሞርስክ ሲምፖዚየም አካሂደው ነበር፤ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ሐኪሞች በአርካንጊልስክ ከተማ ውስጥ በተካሄደው በዚህ ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል። የሆስፒታል መረጃ አገልግሎት በዚህ ቦታም ተመሳሳይ ዴስክ ከፍቶ የነበረ ሲሆን ዴስኩ የብዙዎችን ትኩረት ስቦ ነበር። አንድ ሐኪም ዴስኩ ያቀረባቸውን መረጃዎች ሲመለከቱ “እኛ የሚያስፈልገን እንዲህ ዓይነት ነገር ነው!” ብለዋል። እኛ ሐኪም፣ አንዳንድ የሥራ ባልደረቦቻቸው ልማድ ስለሆነባቸው ብቻ በቃጠሎ ለተጎዱ ታካሚዎች ደም መስጠት መቀጠላቸው የሚያሳዝን እንደሆነ ተናግረዋል። አክለውም “እናንተ ያዘጋጃችኋቸው መረጃዎች በቃጠሎ ለተጎዱ ሰዎች የሚሰጠውን ሕክምና አስመልክቶ በሴይንት ፒተርስበርግ ሊደረግ ለታሰበው ጉባኤ በጣም ጠቃሚ ይሆናሉ” በማለት ተናግረዋል።

በመላው ዓለም፣ ቀዶ ጥገናን ጨምሮ ያለ ደም የሚሰጡ ሕክምናዎች ያላቸውን ጠቀሜታ የተረዱ ሐኪሞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ይህ ዓይነቱ ሕክምና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው የሕክምና ዘዴ እስከመሆን ይደርስ እንደሆነ ወደፊት የምናየው ነገር ይሆናል።

^ አን.3 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።