በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዱር እንስሳት

ሙስ—የጫካው ባላባት

ሙስ—የጫካው ባላባት

“ሙስ የተባለው እንስሳ ሲያዩት ደስ የማይል እንግዳ ፍጡር ነው። ለመሆኑ ትከሻው ከፍ ያለው ለምንድን ነው? ፊቱስ ምን እንዲህ አረዘመው?” ይህን የጻፈው የ19ኛው መቶ ዘመን ጸሐፊ ሄንሪ ዴቪድ ቶራው ሲሆን ስለ ሙስ እንዲህ ዓይነት አስተያየት የሰጠው እሱ ብቻ አይደለም። አስቂኝ መልክ ያለው ይህ እንስሳ በደን ውስጥ በብዛት የማይታይ በመሆኑ ሰዎች ወልካፋና ጅላጅል እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል። ታዲያ ይህ እውነት ነው? በሰሜን አሜሪካ እንዲሁም በአውሮፓና በእስያ አገሮች የሚገኙ ተመራማሪዎች ስለዚህ እንግዳ እንስሳ ብዙ ነገር መረዳት ችለዋል።

ሙስ ግዙፍ እንስሳ መሆኑን ማንም አይክድም። ይህ “የጫካ ባላባት” ከርፋፋ መስሎ እንዲታይ የሚያደርጉ ረጃጅም እግሮች ቢኖሩትም በእነዚህ እግሮቹ ተጠቅሞ የተኩላ መንጋ ማባረር ይችላል። ሙሶች በተወለዱ በጥቂት ቀናት ውስጥ መዋኘት ይችላሉ፤ በተጨማሪም ብዙ ኪሎ ሜትር ሲዋኙና የውኃ ውስጥ ተክሎችን ለመብላት እስከ 6 ሜትር ገደማ ድረስ ጠልቀው ሲገቡ ታይተዋል።

ሙስ ወደ ኋላ መዞር ሳያስፈልገው ዓይኖቹን በማንቀሳቀስ ብቻ ከጀርባው እንቅስቃሴ መኖሩን ማወቅ ይችላል። አፍንጫውም ቢሆን የሚያበረክተው ጥቅም የዋዛ አይደለም። የአፍንጫዎቹ ቀዳዳዎች የተራራቁ መሆናቸው አንድ ነገር ያለበትን ትክክለኛ ቦታ ለይቶ የማወቅ ልዩ ችሎታ እንዲኖረው አስተዋጽኦ ሳያደርጉ እንዳልቀረ ተመራማሪዎች ይገምታሉ። ሌላው አስገራሚ የስሜት ሕዋሱ ደግሞ የመስማት ችሎታው ነው። ጆሮው ወደ ሁሉም አቅጣጫዎች መዞር የሚችል ሲሆን ሌሎች ሙሶች ከ3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሆነው የሚያሰሙትን ድምፅ እንኳ መለየት ይችላል!

አንድ ጸሐፊ እንደገለጸው የሙስ ጥጆች ትንሽ በመሆናቸው ደስ የሚሉ ይሁኑ እንጂ መልካቸው ያው የወላጆቻቸው ነው፤ ጥጆቹ የማወቅ ጉጉት ያላቸው ሲሆን ስጋት የሚባል ነገር የሚያውቃቸው አይመስልም። እናቶች ለልጆቻቸው ከፍተኛ ፍቅር ስላላቸው በታማኝነት ይንከባከቧቸዋል። እናትየው ተኩላዎችን፣ ድቦችን ሌላው ቀርቶ ሰዎችን ጨምሮ ልጆቿን ለመንጠቅ በሚመጣ በማንኛውም ጠላት ላይ ጥቃት ትሰነዝራለች። በመጨረሻም ጥጃው አንድ ዓመት ገደማ ሲሆነውና እናቱ በድጋሚ ስታረግዝ ልጇ ራሱን እንዲችል ከአጠገቧ ታባርረዋለች።

የሰሜኑን ቁር ተቋቁሞ መኖር

ሙሶች በዋነኝነት የሚመገቡት ተክሎችን ሆኖ ሳለ የቅዝቃዜውን ወራት ተቋቁመው ማለፍ የሚችሉት እንዴት ነው? አንዱ መንገድ በሞቃታማው የአየር ጠባይ ወቅት ደህና አድርገው በመመገብ ነው። ሙሶች እስከ 23 ኪሎ ግራም የሚመዝን ምግብ በየቀኑ ይመገባሉ፤ የሚመገቧቸው ተክሎች ከመሬት በላይ ያላቸው ቁመትም ሆነ ከውኃ በታች የሚገኙበት ርቀት እስከ 3 ሜትር ሊደርስ ይችላል። አራት ክፍል ያለው ጨጓራቸው ምግቡን በመፍጨት ለሰውነታቸው የሚያስፈልገውን አልሚ ንጥረ ነገር ስለሚወስድና ይህ ንጥረ ነገር ደግሞ ወደ ስብነት ስለሚቀየር የተመገቡት ምግብ አይባክንም። ይሁን እንጂ ሙስ በቅዝቃዜ ወቅት የሚያጋጥመው አደጋ ይህ ብቻ አይደለም።

አጥንት የሚሰብረው ብርድና የሚከመረው በረዶ ሙስን የሚፈታተኑ ነገሮች ናቸው። በቅዝቃዜው ወራት ብዙ አለመንቀሳቀስ ይመርጣል፤ ይህ ደግሞ ፀጉራም ከሆነው ቆዳው ጋር ተዳምሮ ሙቀት እንዳያባክን ያደርገዋል። በተለይ አካባቢው በረዶ ሲለብስ ከተኩላዎች መሸሽ በጣም አስቸጋሪ ይሆንበታል። ይባስ ብሎ ደግሞ የአዳኞች ሰለባ ሊሆን ወይም በመኪና ሊገጭ ይችላል።

በሰሜን አካባቢ በሚገኙ ብዙ አውራ ጎዳናዎች ላይ በረዶን ለማቅለጥ በሚነሰነሰው ጨው ውስጥ የሚገኘውን ንጥረ ነገር ሙሶች ይወዱታል። ይሁን እንጂ ሙሶች ፀጉራቸው ጥቁር ስለሆነና ጀምበር ከጠለቀች በኋላ መንገድ ማቋረጥ ስለሚያዘወትሩ ሾፌሮች እነሱን በቀላሉ መለየትና ጥንቃቄ ማድረግ ይቸግራቸዋል። በዚህ ምክንያት ሰዎችም ሆነ ሙሶች ሕይወታቸውን ያጣሉ።

ጨዋታ ወዳድ እንስሳ

ሙሶች ከውቅያኖስ ማዕበል ጋር ሲጫወቱና በፍል ውኃዎች ውስጥ ሲንቦራጨቁ ተስተውለዋል። በስሪያ ወቅት በእንስቷና በተባዕቱ መካከል ያለው መዋደድ በግልጽ የሚታይ ሲሆን እናቲቱ ጥጃዋን በመንከባከብ የምታሳየው ታማኝነትም ልብ የሚነካ ነው። ሰዎች ያሳደጓቸው ጥጆች፣ ከጠባቂዎቻቸው ጋር እንኳ የእናትና የልጅ ዓይነት ትስስር መሥርተዋል። ዶክተር ቫሌሪየስ ጊስት “የማይስብ መልክ ያለው ይህ እንግዳ ፍጡር ፈጣን አእምሮ ያለው፣ አፍቃሪና እጅግ ሲበዛ ታማኝ ነው” በማለት ገልጸዋል።

የሙስ ጥጆች የማወቅ ጉጉት ያላቸው ሲሆኑ ስጋት የሚባል ነገር የሚያውቃቸው አይመስልም

ይሁንና አንድ መጠንቀቅ ያለብህ ነገር አለ፦ ሙስ በጣም ጠንካራና ኃይለኛ የዱር እንስሳ ነው። በዱር ውስጥ ካየኸው አክብሮት አሳየው፤ እንዲሁም ነፃነቱን ላለማሳጣት ራቅ ብለህ ቁም። በተለይ እዚያ አካባቢ ጥጆች ካሉ ራቅ ማለትህ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ራቅ ብለህ በመቆምህ ይህን የጫካ ባላባት በደንብ ማየት አልችልም የሚል ስጋት አይደርብህ፤ ካለህበት ሆነህም በዚህ እንስሳ መደነቅህ አይቀርም።