በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አምላክ ምን ይመስላል?

አምላክ ምን ይመስላል?

አምላክ ያለው ምን ዓይነት አካል ነው?

“አምላክ መንፈስ ነው።”—ዮሐንስ 4:24

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ መንፈስ እንደሆነ ይናገራል። (2 ቆሮንቶስ 3:17) በመሆኑም አምላክ ከእኛ እጅግ የላቀ ነው፤ እንዲሁም የሰው ልጆች አእምሮ ውስን በመሆኑ የእሱ አካል ምን እንደሚመስል ሙሉ በሙሉ መረዳት አንችልም። አምላክ ‘የማይበሰብስ፣ የማይታይና የዘላለም ንጉሥ’ እንደሆነ 1 ጢሞቴዎስ 1:17 ይናገራል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “መቼም ቢሆን አምላክን ያየው ማንም የለም” ይላል።—1 ዮሐንስ 4:12

ፈጣሪያችን ከእኛ እጅግ የላቀ በመሆኑ እሱ ምን እንደሚመስል ማሰብ እንኳ አንችልም። ኢሳይያስ 40:18 “እግዚአብሔርን ከማን ጋር ታወዳድሩታላችሁ? ከየትኛውስ ምስል ጋር ታነጻጽሩታላችሁ?” ይላል። በአድናቆት እንድንደመም የሚያደርጉን የሰማይ አካላት እንኳ ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር ሲነጻጸሩ እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደሉም።—ኢሳይያስ 40:22, 26

ይሁን እንጂ አምላክን ማየት የሚችሉ አልፎ ተርፎም ፊት ለፊት ከእሱ ጋር የሚነጋገሩ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት አሉ። እነዚህ ፍጥረታት ይህን ማድረግ የቻሉት እንዴት ነው? እነሱም መንፈሳዊ አካል ያላቸውና በሰማይ የሚኖሩ ስለሆነ ነው። (1 ነገሥት 22:21፤ ዕብራውያን 1:7) ከሰው የላቀ አካል ያላቸውና መላእክት ተብለው የሚጠሩት እነዚህ ፍጥረታት ‘በሰማይ ያለውን የአባቱን ፊት ዘወትር እንደሚያዩ’ ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል።—ማቴዎስ 18:10

 አምላክ በሁሉም ስፍራ ይገኛል?

“እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን።’”—ማቴዎስ 6:9

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በሁሉም ቦታ እንደሚገኝ አያስተምርም፤ አምላክ በሁሉም ቦታ የሚገኝ አካል የሌለው ኃይል አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ በማቴዎስ 6:9 እና 18:10 ላይ ‘አባት’ የሚለውን ቃል መጠቀሙ አምላክ አካል እንዳለው ያሳያል፤ ከዚህም በተጨማሪ አምላክ ‘ማደሪያ’ እንዳለው ይኸውም የሚኖረው በሰማይ እንደሆነ ኢየሱስ በጥቅሶቹ ላይ ከተናገረው ሐሳብ መረዳት እንችላለን።—1 ነገሥት 8:43

ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ “ዓለምን ትቼ ወደ አብ ልሄድ ነው” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 16:28) ክርስቶስ በሥጋ ከሞተና መንፈሳዊ አካል ይዞ ከተነሳ በኋላ “በአምላክ ፊት ይታይ ዘንድ በቀጥታ ወደ ሰማይ ገብቷል።”—ዕብራውያን 9:24

አምላክን በተመለከተ እነዚህን እውነቶች ማወቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። ለምን? አንደኛ፣ አምላክ አካል ያለው ከሆነ ስለ እሱ መማር እንዲሁም ወደ እሱ መቅረብ እንችላለን። (ያዕቆብ 4:8) በሌላ በኩል ደግሞ አምላክን በተመለከተ ይህን እውነት ማወቃችን ከሐሰት አምልኮ ይኸውም ሕይወት የሌላቸው ምስሎችንና ግዑዝ ነገሮችን ከማምለክ ይጠብቀናል። አንደኛ ዮሐንስ 5:21 “ልጆቼ ሆይ፣ ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ” በማለት ይናገራል።

የሰው ልጆች በአምላክ መልክ የተፈጠሩት እንዴት ነው?

“እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።”—ዘፍጥረት 1:27

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የሰው ልጆች እንደ ፍቅር፣ ፍትሕና ጥበብ ያሉትን የአምላክ ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ አላቸው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “የተወደዳችሁ ልጆች በመሆን አምላክን የምትኮርጁ ሁኑ፤ . . . በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ” ይላል።—ኤፌሶን 5:1, 2

ከዚህም በተጨማሪ አምላክ የሰው ልጆችን የፈጠረው የራሳቸውን ምርጫ የማድረግ ነፃነት እንዲኖራቸው አድርጎ ነው፤ በዚህም የተነሳ ትክክል የሆነውን ነገር የመምረጥና በተለያዩ መንገዶች ፍቅራችንን ለሌሎች የመግለጽ ችሎታ አለን። (1 ቆሮንቶስ 13:4-7) በተጨማሪም የተለያዩ ነገሮችን መፍጠር እንዲሁም ውብ የሆኑ ነገሮችንና የፍጥረት ሥራዎችን ማድነቅ እንችላለን። ከሁሉ የበለጠ ደግሞ ፈጣሪያችን፣ መንፈሳዊ ነገሮችን ይኸውም ስለ እሱና ከእኛ ጋር በተያያዘ ስላለው ዓላማ የማወቅ ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ፈጥሮናል።—ማቴዎስ 5:3

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው እውነት የሚጠቅምህ እንዴት ነው? ስለ አምላክ ያለን እውቀት እየጨመረ ሲሄድ እንዲሁም ይበልጥ እሱን ለመምሰል ጥረት ስናደርግ አኗኗራችን ከበፊቱ የበለጠ እሱን የሚያስደስት ይሆናል። ይህም በሕይወታችን ውስጥ እውነተኛ ደስታ እንድናገኝ ያስችለናል፤ ከዚህም ሌላ እውነተኛ እርካታና ውስጣዊ ሰላም ማግኘት እንችላለን። (ኢሳይያስ 48:17, 18) አዎ፣ አምላክ በአስደናቂ ባሕርያቱ ልባቸው የሚነካ ቅን ሰዎችን ወደ ራሱ ይስባቸዋል፤ እንዲሁም የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ይረዳቸዋል።—ዮሐንስ 6:44፤ 17:3