በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ዩናይትድ ስቴትስ

የግብርና ሚኒስቴር ያወጣው አኃዛዊ መረጃ እንደሚያሳየው በ2012 በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙ ቤተሰቦች መካከል 14.5 በመቶ የሚሆኑት ይኸውም 49 ሚሊዮን ሰዎች፣ በዓመቱ ውስጥ “ለቤተሰቦቻቸው በሙሉ የሚበቃ ምግብ ማግኘት መቻላቸውን እርግጠኞች” ያልሆኑበት ጊዜ ነበር፤ “አሊያም ይህን ማድረግ አልቻሉም ነበር።”

ስፔን

በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው 56 በመቶ የሚሆኑት ሴቶችና 41 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች አልኮል ከመጠን በላይ ይጠጣሉ፤ በዚህ ጥናት መሠረት ከመጠን በላይ መጠጣት የሚባለው በአንድ ዙር ቢያንስ ስምንት ብርጭቆ (ለወንዶች) ወይም ስድስት ብርጭቆ (ለሴቶች) መጠጣት ነው።

ፓስፊክ ውቅያኖስ

መሪያና ትሬንች ከሚባለው 11,000 ሜትር ጥልቀት ላይ ከሚገኘው የባሕር ክፍል ናሙና የወሰዱ የሳይንስ ሊቃውንት፣ በድቅድቅ ጨለማ በተዋጠውና ኃይለኛ ግፊት ባለበት እንዲሁም ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች በሚወርድበት በዚህ ቦታ ባክቴሪያዎችና ሌሎች ረቂቅ ተሕዋስያን ተመችቷቸው እንደሚኖሩ አረጋግጠዋል። እንዲህ ባለ ጥልቅ ቦታ ሕይወት ያለው ነገር የመኖሩ አጋጣሚ በጣም ጠባብ እንደሆነ ይታሰብ ነበር።

ዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስ

የዱባይ ባለሥልጣናት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ከመጠን በላይ የመወፈር ችግር ለመቅረፍ ሲሉ 1 ኪሎ ግራም ለቀነሰ ሰው አንድ ግራም ወርቅ (በወቅቱ 45 የአሜሪካ ዶላር ገደማ ያወጣል) ለመሸለም በቅርቡ ቃል ገብተዋል። አንድ ሰው ወርቁን ለመሸለም ከፈለገ ክብደቱን ማስመዝገብና በረመዳን ጾም ወቅት ቢያንስ 2 ኪሎ ግራም መቀነስ ይኖርበታል።