በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ግልጽና ጠንካራ መልእክት ያዘለ መታሰቢያ”

“ግልጽና ጠንካራ መልእክት ያዘለ መታሰቢያ”

በጃፓን፣ ሂሮሺማ ሲቲ ውስጥ ባለው ሞቶያሱ ወንዝ ምሥራቃዊ ዳርቻ ላይ በ1945 በከፊል የፈራረሰ አንድ ሕንፃ ቆሞ ይታያል። ሕንፃው ወደ 70 ለሚጠጉ ዓመታት ተመልሶ ሳይገነባ የቆየው ለምንድን ነው?

በ1915 በሸክላና በአርማታ ተገንብቶ የተጠናቀቀው ይህ ባለ ሦስት ፎቅ ሕንፃ የኢንዱስትሪ መስፋፋትን የሚያበረታታ የኤግዚቢሽን ማዕከል ሆኖ ያገለግል ነበር። ይሁን እንጂ ነሐሴ 6, 1945 ከጠዋቱ 2:15 ላይ ሁኔታው ተለወጠ። ከዚያ በፊት ለጦርነት ውሎ የማያውቀው አቶሚክ ቦምብ የፈነዳው በዚህ ዕለት ነበር፤ ቦምቡ ከከተማዋ በላይ 550 ሜትር ከፍታ ላይ እንዳለ ልክ በኤግዚቢሽን ማዕከሉ አናት ላይ ፈነዳ። በሕንፃው ውስጥ የነበሩት በሙሉ በዚያው ቅጽበት ሞቱ። የሕንፃው መዋቅር ግን አልፈረሰም።

በዩኔስኮ * የተዘጋጀ አንድ ጽሑፍ እንደገለጸው፣ ምንም ዓይነት እድሳት ሳይደረግለት ባለበት እንዲቆይ የተደረገው ይህ ሕንፃ “የሰው ልጆች እስካሁን ከፈለሰፏቸው አውዳሚ ነገሮች ሁሉ የላቀውን አጥፊ መሣሪያ የሚያስታውስ ግልጽና ጠንካራ መልእክት ያዘለ መታሰቢያ” ነው። በ1996 ይህ ሕንፃ የሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ በሚል ስያሜ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ መዝገብ ውስጥ ተመዝግቧል።

የሚያሳዝነው ግን እንዲህ ያሉ መታሰቢያዎች እያሉም ቢሆን የሰው ልጆች በስግብግብነት፣ በብሔራዊ ስሜት እንዲሁም በዘር፣ በሃይማኖትና በጎሣ ጥላቻ የተነሳ እርስ በርስ መዋጋታቸውን አላቆሙም። ታዲያ ጦርነት ምንጊዜም አብሮን ይኖራል ማለት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ሁኔታው እንዲህ እንደማይሆን ይናገራል። መዝሙር 46:9 “[አምላክ] ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል ቀስትን ይሰብራል፤ ጦርን ያነክታል፤ ጋሻንም በእሳት ያቃጥላል” በማለት ይናገራል። በዚህ ጊዜ አምላክ የሰዎችን አገዛዝ ራሱ ባቋቋመው መንግሥት ይተካዋል፤ ይህ መንግሥት “የነገሥታት ንጉሥ” ተብሎ በተጠራው በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት ነው።—ራእይ 11:15፤ 19:16

ከዚያ በኋላ የጦርነትን መጥፎነት የሚያስታውስ መታሰቢያ ማቆም አያስፈልግም። ኢሳይያስ 65:17 እንደሚናገረው “ያለፉት ነገሮች” ይኸውም በዛሬው ጊዜ ያሉት አሳዛኝና አስጨናቂ ነገሮች “አይታሰቡም፤ አይታወሱም።”

^ አን.4 ዩኔስኮ፣ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት ነው።