በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ልጆች ታዛዥ እንዲሆኑ ማሠልጠን

ልጆች ታዛዥ እንዲሆኑ ማሠልጠን

ተፈታታኙ ነገር

ከአራት ዓመት ልጃችሁ ጋር እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል ነጋ ጠባ ትጨቃጨቃላችሁ፤ ሁልጊዜ ደግሞ የሚያሸንፈው ልጃችሁ ይሆናል።

  • ማድረግ የማይፈልገውን ነገር እንዲያደርግ ስትነግሩት አይሰማችሁም። *

  • ማድረግ የሚፈልገውን ነገር እንዳያደርግ ስትነግሩት ሽብር ይፈጥራል።

‘እንዲህ እንዲሆን ያደረገው ዕድሜው ይሆን? ሲያድግ መቼም መለወጡ አይቀርም’ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል።

ልጃችሁ ታዛዥ እንዲሆን ማሠልጠን ትችላላችሁ። ልጃችሁን ማሠልጠን የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ከማየታችን በፊት ግን እንዲህ ያለውን መጥፎ ባሕርይ እንዲያሳይ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል አንዱን እንመልከት።

ምክንያቱ ምንድን ነው?

ልጃችሁ ገና እንደተወለደ ዋነኛ ኃላፊነታችሁ እሱን መንከባከብ ነበር። ልጃችሁ የጠየቀውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነበራችሁ። ልጁ ድምፅ ካሰማ ወዲያው ደርሳችሁለት የሚፈልገውን ነገር ታደርጉለታላችሁ። በዚያ ወቅት እንዲህ ማድረጋችሁ አስፈላጊም ተገቢም ነበር። አራስ ሕፃን የወላጆቹ ትኩረትና ጥበቃ እንደሚያስፈልገው እሙን ነው።

ለበርካታ ወራት እንዲህ ዓይነት እንክብካቤ ሲደረግለት ከቆየ በኋላ ልጁ እሱ የቤቱ ጌታ፣ ወላጆቹ ደግሞ እሱ የጠየቀውን ሁሉ ማድረግ የሚጠበቅባቸው አገልጋዮች እንደሆኑ አድርጎ ቢያስብ የሚያስገርም አይሆንም። ከዚያም ሁለት ዓመት ገደማ ሲሆነው እውነታውን መቀበሉ ይኸውም ቤት ውስጥ የነበረው “ሥልጣን” እንዳበቃ መገንዘቡ አይቀርም። አሁን ወላጆቹ የእሱን ፍላጎት አያስተናግዱም፤ ይልቁንም ልጁ ወላጆቹ የሚጠብቁበትን ነገር ያደርጋል። ይህ ለልጆች ያልጠበቁት ክስተት ነው! በዚህ ምክንያት አንዳንዶች ሽብር ይፈጥራሉ። ሌሎች ደግሞ የወላጆቻቸውን ሥልጣን መቀበል ስለሚከብዳቸው ለመታዘዝ እንቢተኛ ይሆናሉ።

እንዲህ ባለው ወሳኝ ጊዜ ወላጅ ከቀድሞው ለየት ያለ ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፤ ከልጁ ምን እንደሚፈለግ መመሪያ የመስጠት ሥልጣን እንዳለው ማሳወቅ ይኖርበታል። ይሁን እንጂ በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ልጅ እንዳደረገው ልጁ የሚሰጠውን መመሪያ አልቀበልም ቢልስ?

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

አመራር ስጡ። ልጃችሁ አመራር ስትሰጡ እስካላየ ድረስ የመሪነት ቦታችሁን አይቀበልም። ስለዚህ ሥልጣናችሁን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መጠቀም ይኖርባችኋል። ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ምሁራን ነን የሚሉ አንዳንድ ሰዎች “ሥልጣን” የሚለው ቃል ራሱ ጭካኔ የሚንጸባረቅበት እንደሆነ መናገር ጀምረዋል። እንዲያውም አንድ ምሁር የወላጆች ሥልጣን “ሥነ ምግባርም ሆነ ግብረ ገብነት የጎደለው ነው” ብለዋል። ይሁን እንጂ ልጆችን ስድ መልቀቅም ግራ እንዲጋቡ፣ እንዲሞላቀቁና ለሥልጣን አክብሮት የሌላቸው እንዲሆኑ ያደርጋል። ካደጉ በኋላ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች እንዲሆኑ አያደርጋቸውም።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 29:15

ተግሣጽ ስጡ። አንድ መዝገበ ቃላት ተግሣጽ የሚለው ቃል “አንድ ሰው ታዛዥ እንዲሆን ወይም ራሱን እንዲገዛ የሚረዳ ሥልጠና እንደሆነና ይህም መመሪያ በመስጠት፣ መመሪያው ሲጣስ ደግሞ ቅጣት በማስፈጸም እንደሚከናወን” ገልጿል። እርግጥ ተግሣጽ ምክንያታዊ ባልሆነ ወይም ልጁን በሚጎዳ መንገድ መሰጠት የለበትም። በሌላ በኩል ደግሞ ተግሣጹ ግልጽ እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ የሚሰጥ መሆን አለበት፤ እንዲህ ካልሆነ ግን ልጁ ለውጥ ለማድረግ አይገፋፋም።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 23:13

ቀጥተኛ ትእዛዝ ስጡ። አንዳንድ ወላጆች ለልጆቻቸው ትእዛዝ የሚሰጡት ያንን ነገር ማድረግ ይችሉ እንደሆነ በመጠየቅ ነው። (“ክፍልህን እንድታጸዳ እፈልጋለሁ፤ እሺ?”) ምናልባት ወላጆች እንዲህ የሚያደርጉት ጥሩ ምግባር እንዳላቸው ለማሳየት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ዘዴ አንድ ወላጅ በልጁ ላይ ያለውን የማዘዝ ሥልጣን ያሳጣዋል፤ ይህ ደግሞ ልጁ፣ የተሰጠው ትእዛዝ ምን ጉዳትና ጥቅም እንዳለው አመዛዝኖ ትእዛዙን ለመፈጸም ወይም ላለመፈጸም እንዲመርጥ ነፃነት ይሰጠዋል። ሥልጣናችሁን አሳልፋችሁ ከመስጠት ይልቅ ቀጥተኛ የሆነ ትእዛዝ ስጧቸው።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ 1 ቆሮንቶስ 14:9

አቋማችሁን አታላሉ። አይሆንም ካላችሁ በአቋማችሁ ጽኑ፤ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር አንድ ዓይነት አቋም ይኑራችሁ። አለመታዘዙ ምን ቅጣት እንደሚያስከትልበት ከነገራችሁት ያንን ከማድረግ ወደኋላ አትበሉ። እሱን ለመቅጣት የወሰናችሁት ለምን እንደሆነ ለማስረዳት አላስፈላጊ ጭቅጭቅ ውስጥ አትግቡ። “‘አዎ’ ካላችሁ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ካላችሁ አይደለም ይሁን” የሚለውን ጥቅስ ተግባራዊ ማድረጋችሁ ለልጃችሁም ሆነ ለራሳችሁ ይበጃችኋል።—ያዕቆብ 5:12

አፍቃሪ ሁኑ። የቤተሰብ ተቋም የሥልጣን ተዋረድ የሌለበት ወይም አምባገነናዊነት የሰፈነበት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ልጆቹ አድገው ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች እስከሚሆኑ ድረስ ፍቅራዊ መመሪያ የሚያገኙበት ከአምላክ የተሰጠ ዝግጅት ነው። ልጆች እንዲህ ያለውን መመሪያ ከሚያገኙበት መንገድ አንዱ ተግሣጽ ነው፤ ይህም ልጃችሁ ታዛዥ እንዲሆንና በፍቅራችሁ ተማምኖ እንዲኖር ይረዳዋል።

^ አን.5 በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለ ልጆች ስንናገር በወንድ ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሴቶችም ይሠራሉ።