በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የታሪክ መስኮት

ጋሊልዮ

ጋሊልዮ

በ14ኛውና በ16ኛው መቶ ዘመን መካከል የነበሩ አውሮፓውያን የሳይንስ ሊቃውንትና ፈላስፎች የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስለ ጽንፈ ዓለም ከምታስተምረው ትምህርት ጋር የሚጋጭ አመለካከት ማስፋፋት ጀመሩ። ጽንፈ ዓለምን በተመለከተ የተለየ አመለካከት ይዘው ብቅ ካሉት ሰዎች አንዱ ጋሊልዮ ጋሊሌ ነበር።

ከጋሊልዮ ዘመን በፊት ብዙ ሰዎች ፀሐይ፣ ፕላኔቶችና ከዋክብት በምድር ዙሪያ ይዞራሉ ብለው ያምኑ ነበር። ይህ አመለካከት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከምታስተምራቸው ነገሮች አንዱ ነበር።

ይሁን እንጂ ጋሊልዮ በቴሌስኮፕ አማካኝነት ሰፊ ተቀባይነት ከነበረው ሳይንሳዊ ትምህርት ጋር የሚቃረን ነገር ተመለከተ። ለምሳሌ ያህል፣ ነቁጠ ፀሐይ (ሰንስፖትስ) በመባል የሚታወቁት በፀሐይ አካል ላይ የሚገኙት ነጠብጣቦች ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ተመለከተ፤ ይህም ፀሐይ በራሷ ዛቢያ ላይ እንደምትዞር እንዲያስተውል አስቻለው። እንደነዚህ ያሉ ግኝቶች የሰው ልጆች ስለ ጽንፈ ዓለም ያላቸው ግንዛቤ በእጅጉ እንዲሰፋ አስችለዋል፤ ሆኖም ጋሊልዮ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ፊት ለፊት እንዲጋጭ አድርገውታል።

ሳይንስና ሃይማኖት

ከተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በፊት ፖላንዳዊው የሥነ ፈለክ ተመራማሪ ኒኮላውስ ኮፐርኒከስ ምድር በፀሐይ ዙሪያ ትዞራለች የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ማስፋፋት ጀምሮ ነበር። ጋሊልዮ፣ ኮፐርኒከስ ስለ ጠፈር አካላት እንቅስቃሴ ያደረገውን የምርምር ሥራ ካጠና በኋላ ከዚህ ጽንሰ ሐሳብ ጋር የሚስማማ መረጃ ሰበሰበ። መጀመሪያ ላይ ጋሊልዮ ስድብና ፌዝ እንዳይደርስበት በመፍራት ያስተዋላቸውን ነገሮች ይፋ አላወጣም ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን በቴሌስኮፕ አማካኝነት የተመለከታቸውን ነገሮች ለራሱ ብቻ ይዞ መቀመጥ ስላልቻለ ግኝቶቹን ለሕዝብ አሳወቀ። አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት ጋሊልዮ ያቀረባቸውን የመከራከሪያ ነጥቦች የተቃወሙ ከመሆኑም ሌላ ቀሳውስት በየመድረኮቻቸው ጋሊልዮን መንቀፍ ጀመሩ።

በ1616 “የዘመኑ ግንባር ቀደም ሃይማኖታዊ ሊቅ” የሚባሉት ካርዲናል ቤላርመን፣ በኮፐርኒከስ አመለካከት ላይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አዲስ ድንጋጌ እንዳወጣች ለጋሊልዮ ነገሩት። ጋሊልዮ ይህን ድንጋጌ እንዲቀበል አጥብቀው አሳሰቡት፤ ከዚያ በኋላ ጋሊልዮ ለዓመታት ምድር በፀሐይ ዙሪያ ትዞራለች ብሎ በአደባባይ መከራከሩን አቆመ።

በ1623 የጋሊልዮ ወዳጅ የነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ኧርበን ስምንተኛ ሥልጣን ያዙ። በመሆኑም በ1624 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በ1616 የወጣውን ድንጋጌ እንዲሽሩ ጋሊልዮ ጠየቃቸው። ኧርበን ግን ጋሊልዮ እርስ በርሳቸው ይጋጩ የነበሩትን የኮፐርኒከስንና የአርስቶትልን ጽንሰ ሐሳቦች ከወገናዊነት ነፃ በሆነ ሁኔታ እንዲያብራራ ጠየቁት።

ከዚያም ጋሊልዮ ዳያሎግ ኦን ዘ ግሬት ወርልድ ሲስተምስ የተባለ መጽሐፍ ጻፈ። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጋሊልዮን ገለልተኛ እንዲሆን ቢያዙትም መጽሐፉ የኮፐርኒከስን ድምዳሜ የሚደግፍ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ጋሊልዮን ይቃወሙ የነበሩ ሰዎች መጽሐፉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን እንደሚሳደብ መናገር ጀመሩ። ጋሊልዮም በመናፍቅነት ስለተከሰሰና ብዙ ሥቃይ እንደሚደርስበት ስለተዛተበት የኮፐርኒከስን ትምህርቶች ለመካድ ተገደደ። በ1633 የሮም ኢንኩዊዚሽን ይባል የነበረው ፍርድ ቤት ዕድሜ ልክ የቁም እስር ፈረደበት፤ ጽሑፎቹም እንዲታገዱ ወሰነ። ጋሊልዮ ጥር 8 ቀን 1642 በፍሎረንስ አቅራቢያ በአርቼትሪ በሚገኘው ቤቱ ሞተ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋሊልዮን ያወገዘችው በስህተት እንደነበረ አምነዋል

በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት ከጋሊልዮ ሥራዎች አንዳንዶቹ ካቶሊኮች እንዳያነቧቸው በተከለከሉ መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ ተካትተው ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያኗ በ1979 የሮም ኢንኩዊዚሽን ከ300 ዓመታት በፊት ወስዶት የነበረውን እርምጃ ዳግመኛ ለማየት ወሰነች። በመጨረሻም በ1992 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋሊልዮን ያወገዘችው በስህተት እንደነበረ አመኑ።