በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ቀና በሆነው መንገድ’ ሂድ

‘ቀና በሆነው መንገድ’ ሂድ

‘ቀና በሆነው መንገድ’ ሂድ

ነቢዩ ኢሳይያስ “የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉና ጻድቁን:- መልካም ይሆንልሃል በሉት” በማለት ተናግሯል። በተጨማሪም “የጻድቃን መንገድ ቅን ናት” ብሏል። (ኢሳይያስ 3:​10፤ 26:​7) ሥራችን ጥሩ ፍሬ እንዲያስገኝልን የምንፈልግ ከሆነ በአምላክ ፊት ቀና የሆነውን ማድረግ እንደሚገባን ግልጽ ነው።

ታዲያ ቀና በሆነው መንገድ መጓዝ የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ካደረግን ምን በረከቶች እናገኛለን? አምላክ ካወጣቸው የጽድቅ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምተን በመኖራችን ሌሎች ሊጠቀሙ የሚችሉት እንዴት ነው? የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በምሳሌ መጽሐፍ 10ኛ ምዕራፍ ውስጥ ጻድቅን ከኀጥእ ጋር በማነጻጸር የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል። ይህን ሲያደርግ ‘ጻድቅ’ እና ‘ጻድቃን’ የሚሉትን ቃላት 13 ጊዜ ተጠቅሟል። ከእነዚህ መካከል ዘጠኙ የሚገኙት ከ15 እስከ 32 ባሉት ቁጥሮች ውስጥ ነው። እንግዲያው ምሳሌ 10:​15-32ን መመርመሩ አበረታች ይሆንልናል። a

ተግሣጽን አጥብቀህ ያዝ

ሰሎሞን “የባለጠጋ ሀብት ለእርሱ የጸናች ከተማ ናት፤ የድሆች ጥፋት ድህነታቸው ነው። የጻድቅ ደመወዝ ለሕይወት ነው፤ የኀጥእ ፍሬ ግን ለኃጢአት ነው” በማለት የጽድቅን አስፈላጊነት ተናግሯል።​—⁠ምሳሌ 10:​15, 16

በቅጥር የተከበበች ከተማ በውስጧ የሚኖሩ ሰዎች በተወሰነ መጠን ደኅንነት እንዲሰማቸው እንደምታደርግ ሁሉ ሃብትም በሕይወት ውስጥ ከሚያጋጥሙ አንዳንድ ስጋቶች ሊያሳርፍ ይችላል። ድህነት ያልተጠበቁ ሁኔታዎች በሚከሰቱበት ጊዜ ከባድ ችግር ላይ ሊጥል ይችላል። (መክብብ 7:​12) ይሁን እንጂ ጠቢቡ ንጉሥ ከሃብትም ከድህነትም ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችል አደጋ እንዳለ እየጠቆመም ሊሆን ይችላል። ባለጠጋ ሀብቱን “እንደ ጸናች ከተማ” አድርጎ በማሰብ ትምክህቱን ሙሉ በሙሉ በሀብቱ ላይ ወደ ማድረግ ያዘነብል ይሆናል። (ምሳሌ 18:​11) እንዲሁም ድሃ በድህነቱ የተነሳ ምንም የወደፊት ተስፋ እንደሌለው አድርጎ ሊያስብ ይችላል። በዚህ ምክንያት ሁለቱም በአምላክ ዘንድ መልካም ስም ሳያተርፉ ይቀራሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ጻድቅ ሰው ብዙ ሀብት ኖረውም አልኖረው ቀና የሆነ ተግባሩ ሕይወት ያስገኝለታል። እንዴት? ባለው ነገር ረክቶ ይኖራል። ያለበት ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በአምላክ ፊት ያለውን ጥሩ አቋም እንዲያበላሽበት አይፈቅድም። ጻድቅ ሰው ሃብታምም ይሁን ድሃ የሚከተለው የሕይወት መንገድ አሁንም እንኳ ደስታ የሚያስገኝለት ሲሆን ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲኖረው ያደርጋል። (ኢዮብ 42:​10-13) ክፉ ሰው ሃብት ቢያገኝ እንኳ አይጠቀምም። ሀብት ለሚያስገኘው ጥበቃ አመስጋኝ በመሆን ከአምላክ ፈቃድ ጋር ተስማምቶ ከመኖር ይልቅ ሀብቱን በኃጢአት ለተጨማለቀ አኗኗር ይጠቀምበታል።

የእስራኤል ንጉሥ ቀጥሎ “ተግሣጽን የሚጠብቅ በሕይወት መንገድ ይሄዳል፤ ዘለፋን የሚተው ግን ይስታል” ይላል። (ምሳሌ 10:​17) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ይህንን ጥቅስ በሁለት መንገድ መረዳት እንደሚቻል ተናግረዋል። አንደኛው አማራጭ ተግሣጽ ሲሰጠው ተቀብሎ ጽድቅን የሚከታተል ሰው በሕይወት መንገድ ላይ ሲሄድ ተግሣጽን የማይቀበል ግን ከሕይወት መንገድ ወጥቶ ይባዝናል ማለት ሊሆን ይችላል። ጥቅሱ “ተግሣጽን ነቅቶ የሚጠብቅ የሕይወትን መንገድ ያሳያል፤ እርምትን የማይቀበል ግን ሌሎችን ወደ ስሕተት ይመራል” ማለት ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 10:​17 አ.መ.ት) ያም ሆነ ይህ ተግሣጽን አጥብቀን መያዛችንና የሚሰጠንን እርማት ቸል አለማለታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

በጥላቻ ፈንታ ፍቅር

ሰሎሞን በመቀጠል ተመሳሳይ ሐሳብ የሚያስተላልፉ ሁለት ክፍሎች ያሉት ምሳሌ የተናገረ ሲሆን ሁለተኛው የመጀመሪያውን የሚያጠናክር ነው። “ጥልን የሚከድን ሐሰተኛ ከንፈር አለው” ይላል። አንድ ሰው ሌላውን በልቡ እየጠላው በአፉ ቢሸነግለው አታላይ ነው ወይም “ሐሰተኛ ከንፈር አለው” ማለት ነው። ጠቢቡ ንጉሥ “ሐሜትንም የሚገልጥ ሰነፍ ነው” በማለት ጨምሮ ተናግሯል። (ምሳሌ 10:​18) አንዳንዶች ደግሞ ጥላቻቸውን በልባቸው ከመሰወር ይልቅ የሚጠሉትን ሰው በሐሰት መወንጀል ወይም እሱን የሚያጥላላ ወሬ መንዛት ይቀናቸዋል። ይህ የሞኝነት ሥራ ነው፤ ምክንያቱም ስም አጥፊው የሚያናፍሰው ወሬ የሰውዬውን ማንነት አይለውጠውም። እንዲሁም አስተዋይ ሰው የተነገረውን አዳምጦ ሐሰት መሆኑን ሊደርስበትና ሐሜተኛውን ሊታዘበው ይችላል። ስለዚህ የሐሰት ወሬ የሚያናፍስ ሰው ዞሮ ዞሮ የሚጎዳው ራሱን ነው።

የጽድቅ መንገድ ለሽንገላም ሆነ የሌሎችን ስም ለማጥፋት ቦታ የለውም። አምላክ ለእስራኤላውያን “ወንድምህን በልብህ አትጥላው” ብሏቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 19:​17) ኢየሱስም አድማጮቹን “በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፣ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፣ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ” በማለት መክሯል። (ማቴዎስ 5:​44, 45) ልባችንን ከጥላቻ ይልቅ በፍቅር መሙላት ምንኛ የተሻለ ነው!

‘ከንፈርህን ግታ’

ጠቢቡ ንጉሥ አንደበትን የመግታትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ሲናገር “በቃል ብዛት ውስጥ ኃጢአት ሳይኖር አይቀርም፤ ከንፈሩን የሚገታ ግን አስተዋይ ነው” ብሏል።​—⁠ምሳሌ 10:​19

“ሰነፍ ቃሉን ያበዛል።” (መክብብ 10:​14) አንደበቱ “ስንፍናን ያፈልቃል።” (ምሳሌ 15:​2) እንዲህ ሲባል ግን ብዙ የሚናገር ሁሉ ሰነፍ ነው ማለት አይደለም። ሆኖም ዝም ብሎ የሚለፈልፍ ሰው በቀላሉ የጎጂ ሐሜት ወይም ያልተጣራ ወሬ የማሰራጨት አጋጣሚው ምንኛ ሰፊ ነው! የስንፍና አነጋገር ስምን ሊያጎድፍ፣ ስሜትን ሊጎዳ፣ ወዳጅነትን ሊያሻክር አልፎ ተርፎም አካላዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። “ከቃላት ብዛት ኃጢአት አይታጣም።” (ምሳሌ 10:​19 አ.መ.ት) በተጨማሪም አንድ ርዕስ በተነሳ ቁጥር ጣልቃ ከሚገባ ሰው ጋር መሆን አያስደስትም። እንግዲያው ብዙ ከመለፍለፍ እንቆጠብ።

ከንፈሩን የሚገታ ሰው ሐሰት ከመናገር መታቀብ ብቻ ሳይሆን አስተዋይም ነው። ከመናገሩ በፊት ያስባል። ይሖዋ ላወጣቸው የአቋም ደረጃዎች ያለው ፍቅርና ለሰዎች ያለው ልባዊ አሳቢነት የሚናገረው ነገር በሌሎች ላይ ስለሚያሳድረው ተጽእኖ እንዲያጤን ያደርገዋል። ንግግሩ ፍቅርና ደግነት የሚንጸባረቅበት ነው። የሚናገረውን ነገር ማራኪና ጠቃሚ ማድረግ ስለሚችልበት መንገድ ያሰላስላል። የሚናገራቸው ቃላት ‘በብር ፃሕል ላይ እንዳለ የወርቅ እንኮይ’ ያማሩና ምንጊዜም ክብር ያላቸው ናቸው።​—⁠ምሳሌ 25:​11

“ብዙ ሰዎችን ይመግባሉ”

ሰሎሞን በመቀጠል “የጻድቅ ምላስ የተፈተነ ብር ነው፤ የኀጥአን ልብ ግን ምናምን ነው” ይላል። (ምሳሌ 10:​20) የጻድቅ ቃል እንደ ተፈተነ ማለትም እንደ ነጠረ ብር ንጹሕና እንከን የማይወጣለት ነው። የይሖዋ አገልጋዮች ሕይወት አድን የሆነውን የአምላክ ቃል እውቀት ለሌሎች በማካፈል የሚያከናውኑት ተግባር ይህን የሚያረጋግጥ ነው። ታላቁ አስተማሪያቸው ይሖዋ አምላክ ያስተማራቸው ሲሆን ‘የደከሙትን በቃል እንዴት እንደሚደግፉ ያውቁ ዘንድ የተማሩትን ምላስ ሰጥቷቸዋል።’ (ኢሳይያስ 30:​20፤ 50:​4) በእርግጥም ምላሳቸው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ስለሚናገር እንደተፈተነ ብር ነው። ቃላቸው ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች ከኃጥአን ሐሳብ ይልቅ እጅግ የላቀ ዋጋ ያለው ነው! ስለ አምላክ መንግሥትና ድንቅ ስለሆኑት ሥራዎቹ ለመናገር ንቁዎች እንሁን።

ጻድቅ ሰው አብረውት ላሉ ሰዎች በረከት ነው። ሰሎሞን “የጻድቅ ከንፈሮች ብዙ ሰዎችን ይመግባሉ፤ ሰነፎች ግን ከልባቸው ጉድለት የተነሣ ይሞታሉ” በማለት ይናገራል።​—⁠ምሳሌ 10:​21

‘ጻድቅ ብዙ ሰዎችን የሚመግበው’ እንዴት ነው? እዚህ ጥቅስ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል ከእረኝነት ጋር ግንኙነት ያለውን ሐሳብ ያስተላልፋል። በአብዛኛው ጥንት አንድ እረኛ በጎቹን ያሰማራና ይጠብቅ እንደነበረው ሁሉ የመምራትንና የመመገብን ሐሳብ ያስተላልፋል። (1 ሳሙኤል 16:​11፤ መዝሙር 23:​1-3፤ መኃልየ መኃልይ 1:​7) ጻድቅ ሰው ሌሎችን በጽድቅ መንገድ ላይ ይመራል። እንዲሁም ንግግሩ አድማጮቹን ያጠግባል። በዚህም ምክንያት ሕይወታቸው ደስታ የሰፈነበትና ይበልጥ አርኪ ይሆንላቸዋል፤ እንዲያውም የዘላለም ሕይወት ሊያገኙ ይችላሉ።

ሰነፍን በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል? ልብ ስለሚጎድለው የሚከተለው መንገድ የሚያስከትለው መዘዝ የሚያሳስበው ወይም የሚያስጨንቀው አይመስልም። እንደዚህ ያለ ሰው ምንም ያስከትልበት ምን የፈለገውን ያደርጋል። ስለዚህ የእጁን ማግኘቱ አይቀርም። ጻድቅ ሌሎች በሕይወት መኖራቸውን እንዲቀጥሉ መርዳት ሲችል ልቦና የጎደለው ሰው ግን ራሱን እንኳ በሕይወት ማቆየት አይችልም።

ከብልግና ራቅ

የአንድ ግለሰብ ባሕርይ በሚጠላቸውና በሚወዳቸው ነገሮች ተለይቶ ይታወቃል። የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን ይህን እውነት በመጥቀስ “ክፉ ነገር ማድረግ [“ብልግና፣” NW ] ለሰነፍ ሰው ጨዋታ ነው፤ እንዲሁም ጥበብ ለአስተዋይ ነው” በማለት ጠቅሷል።​—⁠ምሳሌ 10:​23

አንዳንዶች ብልግናን እንደ ስፖርት ወይም እንደ ጨዋታ በማየት “ለመዝናናት” በማሰብ በዚህ ድርጊት ይካፈላሉ። እንደዚህ ያሉ ሰዎች ሁሉ ለሚያደርጉት ነገር በአምላክ ፊት ተጠያቂ መሆናቸውን አቅልለው ስለሚመለከቱ የተሳሳተ አካሄድ እየተከተሉ እንዳሉ ፈጽሞ አይታያቸውም። (ሮሜ 14:​12) አስተሳሰባቸው የተዛባ በመሆኑ አምላክ የሚያደርጉትን መጥፎ ነገር የሚያይ አይመስላቸውም። ድርጊታቸው “አምላክ የለም” ብለው እንደሚያምኑ የሚያሳይ ነው። (መዝሙር 14:​1-3፤ ኢሳይያስ 29:​15, 16) ይህ እንዴት ያለ ሞኝነት ነው!

በሌላ በኩል ደግሞ አስተዋይ ሰው ብልግናን እንደ ጨዋታ አይመለከትም። አምላክን እንደሚያሳዝንና ከእርሱ ጋር ያለውን ግንኙነት ሊያበላሽ እንደሚችል ያውቃል። የሰዎችን ክብር የሚነካ፣ ትዳር የሚያፈርስ፣ አእምሮንም ሆነ አካልን የሚጎዳ ስለሆነ እንዲሁም መንፈሳዊ ኪሳራ ስለሚያስከትል እንዲህ ያለው ድርጊት ሞኝነት ነው። እንግዲያው ከማንኛውም ዓይነት የብልግና ድርጊት በመራቅ ጥበብን እጅግ እንደምትወደድ እህት ማፍቀር ብልህነት ነው።​—⁠ምሳሌ 7:​4

በትክክለኛ መሠረት ላይ መገንባት

ሰሎሞን ሕይወትን በጠንካራ መሠረት ላይ መገንባት ያለውን ጥቅም ሲናገር “የኀጥእ ሰው ፍርሃት በላዩ ይመጣበታል፣ ለጻድቃንም ምኞታቸው ትሰጣቸዋለች። ዐውሎ ነፋስ ሲያልፍ ኀጥእ አይገኝም፤ ጻድቅ ግን የዘላለም መሠረት ነው” ብሏል።​—⁠ምሳሌ 10:​24, 25

ኀጥእ በሌሎች ላይ ፍርሃት ሊለቅ ይችላል። ይሁን እንጂ በመጨረሻ የፈራው ነገር በራሱ ላይ ይመጣበታል። በጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ስላልተመሠረተ ከባድ አውሎ ነፋስ ሲመጣ እንደሚደረመስ ጥሩ መሠረት እንደሌለው ሕንፃ ይሆናል። ተጽእኖ ሲያጋጥመው መቋቋም ያቅተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ጻድቅ ኢየሱስ የተናገረውን ተግባራዊ ከሚያደርግ ሰው ጋር ይመሳሰላል። ኢየሱስ “ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም” ሰው እንደሆነ ከተናገረ በኋላ “ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፣ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም” ብሏል። (ማቴዎስ 7:​24, 25) እንደዚህ ያለው ሰው አስተሳሰቡና ድርጊቱ በአምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ጽኑ ሆኖ ስለተመሠረተ ንቅንቅ አይልም።

ጠቢቡ ንጉሥ ኀጥእንና ጻድቅን አስመልክቶ ተጨማሪ ማነጻጸሪያዎችን ከማቅረቡ በፊት “ሆምጣጤ ጥርስን፣ ጢስም ዓይንን እንደሚጐዳ፣ እንዲሁም ታካች ለላኩት” በማለት ያልተንዛዛ ግን አስፈላጊ ማስጠንቀቂያ ተናግሯል። (ምሳሌ 10:​26) ሆምጣጤ ጥርስን ውኃ ያደርጋል። በውስጡ ያለው አሴቲክ አሲድ በጣም ጎምዛዛ ጣዕም እንዲኖረው ያደረገው ሲሆን ጥርስንም ሊያጠርስ ይችላል። ጭስ ዓይን ይቆጠቁጣል እንዲሁም ያቃጥላል። በተመሳሳይም ሰነፍ ሰው ቀጥሮ የሚያሠራ ወይም ወኪል አድርጎ የሚጠቀም ሰው ለብስጭትና ለኪሳራ መዳረጉ የማይቀር ነው።

‘የይሖዋ መንገድ አምባ ነው’

የእስራኤል ንጉሥ “እግዚአብሔርን መፍራት ዘመንን ታረዝማለች፤ የኀጥአን ዕድሜ ግን ታጥራለች። የጻድቃን አለኝታ ደስታ ነው፤ የኀጥኣን ተስፋ ግን ይጠፋል” በማለት ይቀጥላል።​—⁠ምሳሌ 10:​27, 28

ጻድቅ በአምላካዊ ፍርሃት የሚመራ ሲሆን በአስተሳሰቡ፣ በሚናገራቸው ቃላትና በድርጊቱ ይሖዋን ለማስደሰት ይጥራል። አምላክ ያስብለታል እንዲሁም በጽድቅ ላይ የተመሠረቱ ፍላጎቶቹን ያሟላለታል። ይሁን እንጂ ኀጥእ ሰው ከአምላክ የራቀ ሕይወት ይመራል። አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ያደረገው ነገር የተፈጸመለት ይመስል ይሆናል። ሆኖም በአምባጓሮ ወይም አኗኗሩ በሚያስከትልበት ችግር ምክንያት ዕድሜው ስለሚያጥር ስኬቱ ለአጭር ጊዜ ቢቆይ ነው። በሚሞትበት ዕለት ተስፋው ሁሉ ይዳፈናል።​—⁠ምሳሌ 11:​7

ሰሎሞን “የእግዚአብሔር መንገድ ያለ ነውር ለሚሄድ አምባ ነው፣ ጥፋት ግን ክፋትን ለሚያደርጉ” ይላል። (ምሳሌ 10:​29) እዚህ ላይ የይሖዋ መንገድ የሚለው አባባል የሚያመለክተው የምንከተለውን የሕይወት መንገድ ሳይሆን አምላክ ሰዎችን የሚይዝበትን መንገድ ነው። ሙሴ “ሥራው ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና [“ፍትሐዊ፣” NW ] ነው” ብሏል። (ዘዳግም 32:​4) የአምላክ የጽድቅ መንገድ ለጻድቅ ደኅንነት ማለት ሲሆን ለኃጥእ ግን ጥፋት ነው።

ይሖዋ ለሕዝቦቹ አምባ ነው! “ጻድቃን ለዘላለም አይናወጡም፤ ኀጥአን ግን በምድር ላይ አይቀመጡም። የጻድቅ አፍ ጥበብን ይናገራል፤ ጠማማ ምላስ ግን ትቈረጣለች። የጻድቅ ከንፈሮች ደስ የሚያሰኝ ነገርን ያውቃሉ፤ የኀጥአን አፍ ግን ጠማማ ነው።”​—⁠ምሳሌ 10:​30-32

ጻድቃን ክፉ የማያገኛቸው ከመሆኑም በላይ ቀና በሆነ መንገድ ላይ ስለሚሄዱ ይባረካሉ። በእርግጥም “የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፣ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም።” (ምሳሌ 10:​22) እንግዲያው ምንጊዜም ከአምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ከፍተኛ ጥረት እናድርግ። በተጨማሪም ከንፈራችንን በመግታት አንደበታችንን ሕይወት አድን የሆነውን የአምላክ ቃል ለሌሎች ለመናገርና በጽድቅ መንገድ እንዲጓዙ ለመርዳት እንጠቀምበት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ምሳሌ 10:​1-14ን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት የሐምሌ 15, 2001 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 24-7⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንደበት እንደ ‘ተፈተነ ብር’ ሊሆን ይችላል