በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክሪስቶፍ ፕላንታን ለመጽሐፍ ቅዱስ ሕትመት ፈር ቀዳጅ

ክሪስቶፍ ፕላንታን ለመጽሐፍ ቅዱስ ሕትመት ፈር ቀዳጅ

ክሪስቶፍ ፕላንታን ለመጽሐፍ ቅዱስ ሕትመት ፈር ቀዳጅ

ዮሐንስ ጉተንበርግ (1397-1468 ገደማ) በተንቀሳቃሽ ማተሚያ ተጠቅሞ መጽሐፍ ቅዱስን በማተም የመጀመሪያው ሰው እንደሆነ ይታወቃል። ስለ ክሪስቶፍ ፕላንታን የሚያውቁት ግን ብዙዎች አይደሉም። ይህ ሰው በሕትመት ሥራ ፈር ቀዳጅ ሲሆን በ1500ዎቹ ዓመታት በዓለም ዙሪያ ለሚኖሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስና ሌሎች መጻሕፍት እንዲዳረሱ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

ክሪስቶፍ ፕላንታን በ1520 ገደማ በሴንት ኤቨርተን፣ ፈረንሳይ ተወለደ። ፕላንታን 28 ዓመት ገደማ ሲሆነው፣ ከፈረንሳይ ይልቅ ሃይማኖታዊ መቻቻል በሚታይባትና በኢኮኖሚው ዘርፍም ለማደግ ምቹ አጋጣሚዎች በነበሩባት በሎው ካንትሪስ በምትገኘው በአንትወርፕ መኖር ጀመረ። a

ፕላንታን ሥራውን የጀመረው መጽሐፍ በመጠረዝና የቆዳ ውጤቶችን በልዩ ልዩ ንድፍ በማዘጋጀት ነበር። የቆዳ ሥራዎቹን በረቀቀ ንድፍ ያስጌጣቸው ስለነበር በሀብታሞች ዘንድ ከፍተኛ ተፈላጊነት ነበራቸው። የሆነ ሆኖ በ1555 የደረሰበት አደጋ ፕላንታን ሥራውን እንዲቀይር አስገደደው። ፕላንታን፣ የሎው ካንትሪስ ገዥ የነበሩት የስፔኑ ንጉሥ ዳግማዊ ፊሊፕ እንዲሠራላቸው ያዘዙትን አነስተኛ የቆዳ ቦርሳ ለማድረስ በአንትወርፕ አውራ ጎዳና ላይ ሲጓዝ የሰከሩ ሰዎች ትከሻውን በሰይፍ ወጉት። ፕላንታን ከጉዳቱ ያገገመ ቢሆንም የጉልበት ሥራ መሥራት ባለመቻሉ ሙያውን መተው ግድ ሆነበት። ከዚያም ፕላንታን፣ የአናባፕቲስት ቡድን መሪ የሆነ ሄንድረክ ኒክላስ የተባለ ሰው የገንዘብ እርዳታ ስላደረገለት የሕትመት ሥራ ጀመረ።

“ተግቶ መሥራት”

ፕላንታን ለማተሚያ ቤቱ ደ ኩልደን ፓሰር (ወርቃማው ኮምፓስ) የሚል ስም ሰጠው። የንግድ ምልክቱም ለንድፍ የሚያገለግል ኮምፓስ (ማክበቢያ) ሲሆን “ላቦሬ ኤ ኮንስታንቲያ” ማለትም “ተግቶ መሥራት” የሚል ጽሑፍ ተቀርጾበት ነበር። የንግድ ምልክቱ ታታሪ የነበረውን ይህን ሰው ጥሩ አድርጎ የሚገልጸው ይመስላል።

ፕላንታን በኖረበት ዘመን በአውሮፓ ውስጥ ታላቅ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ነውጥ የነበረ ቢሆንም እርሱ ግን በተቻለው መጠን ችግር ውስጥ ላለመግባት ይጥር ነበር። ፕላንታን ከምንም ነገር በላይ ለሕትመት ሥራው ትልቅ ቦታ ይሰጥ ነበር። በጊዜው የፕሮቴስታንት ተሃድሶን ይደግፍ የነበረ ቢሆንም፣ ማዩራትስ ሳቢ የተባሉ ጸሐፊ እንደገለጹት “ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የነበረው አመለካከት አሻሚ ነበር።” በመሆኑም ፕላንታን የተወገዙ መጻሕፍትን እንደሚያትም የሚገልጽ ወሬ ይናፈስ ጀመር። በዚህም ምክንያት በ1562 ወደ ፓሪስ ሸሽቶ በመሄድ ከአንድ ዓመት በላይ መቆየት ግድ ሆኖበታል።

ፕላንታን በ1563 ወደ አንትወርፕ ሲመለስ ባለጸጋ ከሆኑ ነጋዴዎች ጋር በሽርክና መሥራት የጀመረ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ የካልቪን ተከታዮች ነበሩ። ከእነዚህ ሰዎች ጋር በሽርክና በሠራባቸው አምስት ዓመታት ውስጥ ፕላንታን 260 የሚሆኑ ልዩ ልዩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን አትሟል። ከእነዚህ መካከል የዕብራይስጥ፣ የግሪክና የላቲን መጽሐፍ ቅዱሶች እንዲሁም ደማቅ በሆኑ ቀለማት ያጌጡ የደች ካቶሊክ ሉቫን መጽሐፍ ቅዱስ እትሞች ይገኙበታል።

“ታላቅ የሕትመት ሥራ”

በ1567 የሎው ካንትሪስ ነዋሪዎች በስፔን አገዛዝ ላይ የነበራቸው ተቃውሞ እየጨመረ በመሄዱ የስፔኑ ንጉሥ ዳግማዊ ፊሊፕ የአልባውን መሥፍን በአገረ ገዥነት እንዲያገለግል ወደ አካባቢው ላከው። መሥፍኑ ከንጉሡ በተሰጠው ሙሉ ሥልጣን በመጠቀም፣ እየጨመረ የመጣውን የፕሮቴስታንቶች ተቃውሞ ለማስቆም የተቻለውን ሁሉ ይጥር ነበር። ፕላንታንም፣ መናፍቅ እንደሆነ የሚያስቡ ሰዎችን ጥርጣሬ በዚህ አጋጣሚ ለማስወገድ በማሰብ አንድ ትልቅ ሥራ ጀመረ። ቅዱሳን መጻሕፍት መጀመሪያ በተጻፉበት ቋንቋ የተዘጋጀ ለምሑራን የሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ ለማተም ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ፕላንታን ይህን አዲስ እትም ለማዘጋጀት የሚያስችለውን ድጋፍ ከዳግማዊ ፊሊፕ አግኝቶ ነበር። ንጉሡ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ከመግባቱም ባሻገር ሥራውን በበላይነት እንዲመራ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የነበረውን አርያስ ሞንታኖን ሾመው።

ሞንታኖ የቋንቋ ተሰጥኦ የነበረው ሲሆን በቀን ውስጥ ለ11 ሰዓታት ይሠራ ነበር። ይህ ሰው የስፔን፣ የቤልጂየምና የፈረንሳይ ተወላጆች በሆኑ የቋንቋ ሊቃውንት ይታገዝ ነበር። ዓላማቸውም በርካታ ቋንቋዎች የያዘውንና ታዋቂ የሆነውን የኮምፕሉቴንስ መጽሐፍ ቅዱስ በአዲስ መልክ ማዘጋጀት ነበር። b ፕላንታን ያተመው ይህ በብዙ ቋንቋዎች የተዘጋጀ አዲስ መጽሐፍ ቅዱስ ከላቲኑ ቩልጌት፣ ከግሪክኛው ሰብዓ ሊቃናት እንዲሁም ከዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ በተጨማሪ የአረማይኩን ታርገምና በሶርያ ቋንቋ የተዘጋጀውን ፐሺታ ከላቲን ቀጥተኛ ትርጉማቸው ጋር አጣምሮ የያዘ ነው።

የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ሕትመት የተጀመረው በ1568 ሲሆን ይህ ታላቅ ሥራ በ1572 ተጠናቀቀ። በዘመኑ ከነበረው የሕትመት ሥራ አንጻር ሲታይ የወሰደው ጊዜ አጭር ነበር። ሞንታኖ ለንጉሥ ዳግማዊ ፊሊፕ በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ሮም ውስጥ በአንድ ዓመት ከሚሠራው ሥራ ይልቅ እዚህ በአንድ ወር የተከናወነው ይበልጣል” ብሏል። ፕላንታን በስምንት ትላልቅ ጥራዞች የተዘጋጀውንና ብዙ ቋንቋዎችን የያዘውን የዚህን መጽሐፍ ቅዱስ 1,213 ቅጂዎች አትሟል። በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ገጽ ላይ ኢሳይያስ 65:25 በሥዕላዊ መንገድ ተገልጿል፤ ይህ ሥዕል አንበሳ፣ በሬ፣ ተኩላና በግ ከአንድ ገንዳ በሰላም አብረው ሲመገቡ ያሳያል። የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ስምንት ጥራዞች አጠቃላይ ዋጋ 70 ጊልደር ነበር፤ በዘመኑ የአንድ ቤተሰብ አማካይ ዓመታዊ ገቢ 50 ጊልደር ስለነበር ከዚህ አንጻር ሲታይ መጽሐፉ ውድ ነበር። ከጊዜ በኋላ ሁሉም ጥራዞች በአንድ ላይ አንትወርፕ ፖሊግሎት የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሱ በንጉሥ ዳግማዊ ፊሊፕ ድጋፍ የተዘጋጀ በመሆኑ ቢብልያ ሬጊያ (ሮያል ባይብል) እየተባለም ይጠራል።

ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በሊቀ ጳጳስ ግሪጎሪ 13ኛ ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም በአሪያስ ሞንታኖ ላይ ከፍተኛ ነቀፋ አስከትሎበታል። ይህ የሆነበት አንደኛው ምክንያት ሞንታኖ የዕብራይስጡን በኩረ ጽሑፍ ከላቲኑ ቩልጌት የላቀ እንደሆነ አድርጎ መመልከቱ ነው። የእርሱ ዋና ተቀናቃኝ የሆነው ስፔናዊው የሃይማኖት ምሑር ሌዎን ደ ካስትሮ፣ የላቲኑ ቩልጌት ከሁሉም በላይ ትክክለኛ እንደሆነ ያምን ነበር። ደ ካስትሮ፣ ሥላሴን የሚጻረር ፍልስፍና በማስገባት መጽሐፍ ቅዱስን እንደበከለው በመግለጽ ሞንታኖን ወንጅሎታል። ለዚህም 1 ዮሐንስ 5:7 ላይ ያለው “በሰማይ የሚመሰክሩ ሶስት ናቸውና እርሳቸውም አብ ቃልም መንፈስ ቅዱስም። እሌህ ሶስትም አንድም ናቸው” (የ1879 ትርጉም) የሚለው ትክክለኛ ያልሆነ ጭማሪ በሶርያ ቋንቋ ከተዘጋጀው ፐሺታ ላይ እንዲወጣ መደረጉን እንደ ምሳሌ አድርጎ ይጠቅሳል። ያም ሆኖ የስፓኒሽ ኢንኩዊዚሽን ሞንታኖ መናፍቅ እንደሆነ የሚገልጸው ጥርጣሬ መሠረተ ቢስ መሆኑን አረጋግጧል። አንዳንዶች አንትወርፕ ፖሊግሎትን “በ16ኛው መቶ ዘመን የኖረ አታሚ ብቻውን ያከናወነው ታላቅ የሕትመት ሥራ” እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።

ዘላቂ ጠቀሜታ ያለው ሥራ

በወቅቱ የነበሩት ብዙዎቹ አታሚዎች ሁለት ወይም ሦስት ማተሚያዎች ብቻ ነበሯቸው። ሆኖም ፕላንታን ሥራው ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ጊዜ 22 የሚያህሉ ማተሚያዎችና 160 ሠራተኞች ነበሩት። በስፓንኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዘንድም ስኬታማ አታሚ በመሆን ጥሩ ዝና አትርፏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሎው ካንትሪስ ውስጥ በስፔን አገዛዝ ላይ የተነሳው ተቃውሞ እያየለ ሄደ። አንትወርፕ በግጭቱ ምክንያት ታመሰች። በ1576 ደሞዝ ያልተከፈላቸው የስፔን ቅጥረኛ ወታደሮች በማመጽ ከተማዋን መዝረፍ ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ከ600 የሚበልጡ ቤቶች በእሳት የጋዩ ሲሆን በሺህ የሚቆጠሩ የአንትወርፕ ነዋሪዎችም ተገደሉ። ነጋዴዎች ከተማዋን ለቅቀው ሸሹ። ይህ ደግሞ ለፕላንታን ትልቅ ኪሳራ አስከተለበት። ከዚህም በላይ ቅጥረኛ ወታደሮቹ ከሚገባው በላይ ግብር እንዲከፍል አስገደዱት።

በ1583 ፕላንታን ከአንትወርፕ በስተ ሰሜን 100 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኘው ወደ ላይድን ተዛወረ። በዚያም ማተሚያ ቤት ካቋቋመ በኋላ የካልቪን ተከታዮች ላቋቋሙት ለላይደን ዩኒቨርሲቲ አታሚ ሆኖ መሥራት ጀመረ። ይሁንና ለካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ታማኝ እንዳልሆነ የሚገልጸው የቀድሞው ክስ እንደገና ተነሳ። በመሆኑም ፕላንታን፣ አንትወርፕ እንደገና በስፔን ቁጥጥር ሥር ከሆነች ብዙም ሳይቆይ ማለትም በ1585 መጨረሻ አካባቢ ወደ ከተማዋ ተመለሰ። በዚህ ወቅት ፕላንታን በ60ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ነበር፤ ወርቃማው ኮምፓስ በመባል በሚታወቀው ማተሚያ ቤቱ ውስጥም በአንድ ማተሚያ ማሽን ላይ የሚሠሩ አራት ሠራተኞች ብቻ ነበሩት። ፕላንታን ማተሚያውን በድጋሚ ለመሥራት የሞከረ ቢሆንም የቀድሞ ዝናውን ማደስ ሳይችል ቀርቷል፤ በኋላም ፕላንታን ሐምሌ 1, 1589 አረፈ።

ክሪስቶፍ ፕላንታን በ34 ዓመታት ውስጥ 1,863 የተለያዩ መጻሕፍትን በበርካታ ቅጂዎች ያተመ ሲሆን ይህም በየዓመቱ በአማካይ 55 ዓይነት መጻሕፍትን አትሟል ማለት ነው። ዛሬም ቢሆን ለአንድ የግል አታሚ ይህ ታላቅ ስኬት ነው! ፕላንታን ጥብቅ የሆነ ሃይማኖታዊ አቋም ያልነበረው ቢሆንም ሥራው ለሕትመት ሙያ ብቻ ሳይሆን በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ለሚደረገው ጥናትም እርዳታ አበርክቷል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በእርግጥም ፕላንታን እና በዘመኑ የነበሩት አታሚዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለተራው ሕዝብ እንዲዳረስ ከፍተኛ ድርሻ አበርክተዋል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a “ሎው ካንትሪስ” (Low Countries) የሚለው ስያሜ በአሁኑ ጊዜ ቤልጅየም፣ ኔዘርላንድና ሉክሰምበርግ የሚገኙበትን በጀርመንና በፈረንሳይ መካከል ያለውን በባሕር ዳርቻ ላይ የሚገኝ አካባቢ ያመለክታል።

b የተለያዩ ቋንቋዎችን የያዘው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የታተመው በ1517 ሲሆን በአረማይክ የተጻፉ የተወሰኑ ክፍሎችን ጨምሮ በዕብራይስጥ፣ በግሪክና በላቲን ቋንቋዎች የተዘጋጀ ነው። በሚያዝያ 15, 2004 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 28-31 ላይ ያለውን “በርካታ ቋንቋዎችን የያዘው የኮምፕሉቴንስ መጽሐፍ ቅዱስ—ታሪካዊ የትርጉም መሣሪያ” የሚል ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የፕላንታን-ሞሬተስ ሙዚየም

ፕላንታንና ልጆቹ ለመኖሪያና ለሕትመት ሥራ ይገለገሉበት የነበረው በአንትወርፕ የሚገኝ ሕንጻ በ1877 በሙዚየምነት ለሕዝብ እይታ ክፍት ሆነ። በዚያ ዘመን ከነበሩት ማተሚያ ቤቶች መካከል ምንም ሳይሆን ተጠብቆ የቆየ ሌላ ማተሚያ ቤት የለም። በ17ኛውና በ18ኛው መቶ ዘመን የነበሩ አምስት ማተሚያዎችም ለእይታ ቀርበዋል። ከዚህ በተጨማሪ ፕላንታን በኖረበት ዘመን አካባቢ የተሠሩ በዓለማችን ላይ ካሉት ማተሚያዎች ሁሉ እጅግ ጥንታዊ የሆኑ ሌሎች ሁለት ማተሚያዎችም ነበሩ። ሙዚየሙ ፊደላትን ለመቅረጽ የሚያገለግሉ 15,000 ቅርጽ ማውጫዎችን፣ ጽሑፍ የተቀረጸባቸው 15,000 ማተሚያ እንጨቶችን እንዲሁም ፊደል የተቀረጸባቸውን 3,000 የመዳብ ማተሚያዎች ይዟል። በሙዚየሙ ውስጥ የሚገኘው ቤተ መጻሕፍትም ከ9ኛው እስከ 16ኛው መቶ ዘመን ባለው ጊዜ ውስጥ የተጻፉ 638 ጥንታዊ ቅጂዎችን እንዲሁም ከ1501 በፊት የታተሙ 154 መጻሕፍትን ይዟል። ከእነዚህም መካከል ከ1461 በፊት እንደተጻፈ የሚነገርለት የጉተንበርግ መጽሐፍ ቅዱስና ዝነኛ የሆነው የፕላንታን አንትወርፕ ፖሊግሎት ይገኙበታል።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አርያስ ሞንታኖ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንትወርፕ ፖሊግሎት የላቲኑን “ቩልጌት፣” የግሪክኛውን “ሰብዓ ሊቃናትና” የዕብራይስጡን በኩረ ጽሑፍ እንዲሁም የአረማይኩን ታርገምና በሶርያ ቋንቋ የተዘጋጀውን “ፐሺታ” ከላቲን ቀጥተኛ ትርጉማቸው ጋር አጣምሮ የያዘ ነው

[ምንጭ]

By courtesy of Museum Plantin-Moretus/Stedelijk Prentenkabinet Antwerpen

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሁለቱም ምስሎች:- By courtesy of Museum Plantin-Moretus/Stedelijk Prentenkabinet Antwerpen