በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆቻችሁን አስተምሩ

ኢዮስያስ ትክክል የሆነውን ለማድረግ መርጧል

ኢዮስያስ ትክክል የሆነውን ለማድረግ መርጧል

ትክክል የሆነውን ማድረግ ከባድ እንደሆነ ይሰማሃል? *— አዎ ብለህ የምትመልስ ከሆነ ብዙ ሰዎችም በአንተ ሐሳብ ይስማማሉ። ትልልቅ ሰዎችም እንኳ ትክክል እንደሆነ የሚያውቁትን ነገር ማድረግ ይከብዳቸዋል። ኢዮስያስ ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ ከባድ እንዲሆንበት ያደረገው ምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት። ለመሆኑ ኢዮስያስ ማን እንደነበር ታውቃለህ?—

ኢዮስያስ የይሁዳ ንጉሥ የሆነው የአሞን ልጅ ነው። አሞን ኢዮስያስን የወለደው ገና በ16 ዓመቱ ነበር። አሞን ልክ እንደ አባቱ እንደ ንጉሥ ምናሴ በጣም መጥፎ ሰው ነበር። ምናሴ ለብዙ ዓመታት የገዛ በጣም ክፉ ሰው ነበር። ይሁንና አሦራውያን ምናሴን ከማረኩት በኋላ አስረው ርቃ ወደምትገኘው ባቢሎን ወሰዱት። ምናሴ በእስር ላይ እያለ ይሖዋ ይቅር እንዲለው ለመነ፤ ይሖዋም ይቅር አለው።

ምናሴ ከእስር ሲፈታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ እንደገና ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀመረ። የሠራቸውን መጥፎ ነገሮች ወዲያውኑ ያስተካከለ ሲሆን ሕዝቡም ይሖዋን እንዲያገለግል ያበረታታ ጀመር። ልጁ አሞን የእሱን ጥሩ ምሳሌ ባለመከተሉ ሳያዝን አልቀረም። ኢዮስያስ የተወለደው በዚህ ወቅት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ምናሴ ከልጅ ልጁ ከኢዮስያስ ጋር ምን ያህል ጊዜ እንዳሳለፈ አይገልጽም። ምናሴ፣ ኢዮስያስ ይሖዋን እንዲያገለግል ረድቶት ሊሆን ይችላል ብለህ ታስባለህ?—

ኢዮስያስ ገና የስድስት ዓመት ልጅ ሳለ ምናሴ ሞተ፤ በዚህ ጊዜ የኢዮስያስ አባት አሞን ንጉሥ ሆነ። አሞን ለሁለት ዓመት ብቻ ከገዛ በኋላ የራሱ አገልጋዮች ገደሉት። በመሆኑም ኢዮስያስ በስምንት ዓመቱ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ። (2 ዜና መዋዕል ምዕራፍ 33) ከዚያ በኋላ ምን የሆነ ይመስልሃል? ኢዮስያስ የአባቱን የአሞንን መጥፎ ምሳሌ ለመከተል ይመርጥ ይሆን ወይስ ንስሐ የገባው አያቱ ምናሴ የተወውን ጥሩ ምሳሌ?—

ኢዮስያስ ልጅ የነበረ ቢሆንም እንኳ ይሖዋን የማገልገል ፍላጎት ነበረው። በመሆኑም ከአባቱ ጓደኞች ይልቅ ለይሖዋ ፍቅር የነበራቸው ሰዎች የሚነግሩትን ይሰማ ነበር። ኢዮስያስ ገና የስምንት ዓመት ልጅ ቢሆንም ለአምላክ ፍቅር የነበራቸው ሰዎች የሚናገሩትን መስማቱ ትክክል እንደሆነ ተረድቶ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 34:1, 2) ኢዮስያስን ይመክሩት ስለነበሩትና ለእሱ ጥሩ ምሳሌ ስለሆኑት ሰዎች ማወቅ ትፈልጋለህ?—

ለኢዮስያስ ጥሩ ምሳሌ ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዱ ነቢዩ ሶፎንያስ ነው። ሶፎንያስ፣ የምናሴ አባት ይኸውም ጥሩ ንጉሥ የነበረው የሕዝቅያስ ዝርያ እንደሆነ ስለሚታሰብ ከኢዮስያስ ጋር የሥጋ ዝምድና ነበረው። በኢዮስያስ የንግሥና ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ሶፎንያስ በስሙ የሚጠራውን የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ጽፎ አጠናቅቆ ነበር። ሶፎንያስ ትክክል የሆነውን ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች ስለሚደርስባቸው መጥፎ ነገር አስጠንቅቆ ነበር፤ ኢዮስያስ ማስጠንቀቂያውን ሰምቶ እንደሚሆን ግልጽ ነው።

ምሳሌ የሆነው ሌላው ሰው ደግሞ ኤርምያስ ሲሆን ስለ እሱ ከዚህ በፊት ሰምተህ ይሆናል። ኤርምያስና ኢዮስያስ ሁለቱም በወጣትነት ዕድሜ ላይ የነበሩ ሲሆን ያደጉትም በአንድ አካባቢ ነው። ኤርምያስ በስሙ የሚጠራውን የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ እንዲጽፍ ይሖዋ በመንፈስ መርቶት ነበር። ኢዮስያስ ጦርነት ላይ በሞተበት ወቅት ኤርምያስ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ለመግለጽ የልቅሶ ግጥም ጽፎ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 35:25) ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ለመቀጠል አንዳቸው ሌላውን እንዴት ያበረታቱ እንደነበር መገመት አያዳግትም!

ሶፎንያስና ኤርምያስ ትክክል የሆነውን ነገር እንዲያደርግ ኢዮስያስን የረዱት እንዴት ነበር?

የኢዮስያስን ታሪክ በማጥናት ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?— አንተም እንደ ኢዮስያስ አባትህ ይሖዋን የማያገለግል ከሆነ ስለ አምላክ እንድታውቅ የሚረዳህ ሌላ ሰው ይኖር ይሆን? ምናልባትም እናትህ፣ አያትህ ወይም ሌላ ዘመድህ ሊረዱህ ይችሉ ይሆናል። ወይም ደግሞ እናትህ ይሖዋን የሚያገለግል ሌላ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠናህ ትፈቅድ ይሆናል።

ሁኔታህ ምንም ይሁን ምን ኢዮስያስ ገና ትንሽ ልጅ የነበረ ቢሆንም እንኳ ይሖዋን ከሚያገለግሉ ሰዎች ጋር ብቻ ጓደኛ መሆን እንዳለበት ለማወቅ የሚያስችል ብስለት እንደነበረው ልብ በል። አንተም እንደ ኢዮስያስ እንድታደርግና ትክክል የሆነውን ለማድረግ እንድትመርጥ እንመኛለን!

^ አን.3 ይህን ርዕስ የምታነበው ከትንሽ ልጅ ጋር ከሆነ ይህ ሰረዝ ቆም ብለህ ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ እንድታበረታታው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።