በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ የአምላክ አገልጋይ እና ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

እውነተኛ የአምላክ አገልጋይ እና ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

እውነተኛ የአምላክ አገልጋይ እና ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

የኢየሱስ አገልግሎት ተለይቶ የሚታወቅባቸው ሁለት ነገሮች የትኞቹ ናቸው? አንደኛ፣ ኢየሱስ ለመለወጥ የሞከረው ፖለቲካዊ ተቋማትን ሳይሆን የሰዎችን ልብ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ትኩረት ያደረገባቸውን ነጥቦች እንመልከት። ተከታዮቹ እንደ ጨውና እንደ ብርሃን መሆን እንዳለባቸው ከመናገሩ በፊት፣ እውነተኛ ደስታ የሚያገኙት “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ” ሰዎች እንደሆኑ ተናግሯል። አክሎም ‘ገሮች፣ ልባቸው ንጹሕ የሆነ እንዲሁም ሰላም ፈጣሪዎች ደስተኞች’ እንደሆኑ ገልጿል። (ማቴዎስ 5:1-11) ከዚህም ሌላ ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ አስተሳሰባቸውና ዝንባሌያቸው አምላክ ትክክል ወይም ስህተት ስለሆኑት ነገሮች ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ እንዲሆን ማድረጋቸውና አምላክን በሙሉ ልባቸው ማገልገላቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል።

ሁለተኛ፣ ኢየሱስ የሰው ልጆች መከራ ሲደርስባቸው ሲመለከት በርኅራኄ ተነሳስቶ ችግራቸውን ለማቃለል አንዳንድ እርምጃዎችን ወስዷል። ይህ ሲባል ግን መከራን ጨርሶ ለማስወገድ ይጥር ነበር ማለት አይደለም። (ማቴዎስ 20:30-34) የታመሙትን ቢፈውስም በሽታ አልጠፋም። (ሉቃስ 6:17-19) ለተጨቆኑ ሰዎች እፎይታ ያስገኘላቸው ቢሆንም ሕዝቡ በፍትሕ መጓደል ምክንያት የሚደርስባቸው ችግር ጨርሶ አልተወገደም። የተራቡ ሰዎችን የመገበ ቢሆንም የሰው ልጆች በረሃብ አለንጋ መገረፋቸው አልቀረም።—ማርቆስ 6:41-44

ልባቸውን መለወጥና መከራቸውን ማቅለል

ኢየሱስ ሥርዓቱን ለመለወጥ ወይም ችግሮችን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ከመሞከር ይልቅ የሰዎችን ልብ በመለወጥና መከራቸውን በማቅለል ላይ ያተኮረው ለምንድን ነው? አምላክ ወደፊት በመንግሥቱ አማካኝነት ሰብዓዊ መንግሥታትን ጠራርጎ የማጥፋትና ለመከራ መንስኤ የሚሆኑ ነገሮችን በሙሉ የማስወገድ ዓላማ እንዳለው ኢየሱስ ያውቅ ነበር። (ሉቃስ 4:43፤ 8:1) በመሆኑም በአንድ ወቅት ደቀ መዛሙርቱ የታመሙትን መፈወሱን እንዲቀጥል በገፋፉት ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በዚያም እንድሰብክ በአቅራቢያ ወዳሉት ትንንሽ ከተሞች እንሂድ፤ የመጣሁትም ለዚሁ ዓላማ ነው።” (ማርቆስ 1:32-38) ኢየሱስ የብዙዎችን መከራ ያቃለለ ቢሆንም ይበልጥ ትኩረት ያደረገው የአምላክን ቃል በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ ላይ ነበር።

በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም በስብከቱ ሥራቸው የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል ጥረት ያደርጋሉ። ለተቸገሩ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ በመስጠት መከራቸውን ለማቅለል ይጥራሉ። ያም ሆኖ በዓለም ላይ የሚታየውን የፍትሕ መጓደል ከሥረ መሠረቱ ለማስወገድ አይሞክሩም። ምክንያቱም የማንኛውንም ዓይነት መከራ መንስኤ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ያምናሉ። (ማቴዎስ 6:10) እንደ ኢየሱስ ሁሉ እነሱም የፖለቲካ ተቋማትን ሳይሆን የሰዎችን ልብ ለመለወጥ ይጥራሉ። እንዲህ ያለ አካሄድ መከተላቸው ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም የሰው ልጆች ዋና ዋና ችግሮች መንስኤ ከፖለቲካ ሳይሆን ከሥነ ምግባር ጋር የተያያዘ ነው።

ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች

በሌላ በኩል ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ጥሩ ዜጎች የመሆን ክርስቲያናዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። በመሆኑም የመንግሥት ባለሥልጣናትን ያከብራሉ። በጽሑፎቻቸውና በስብከቱ ሥራቸው አማካኝነት ሌሎች ሰዎችም ሕግ አክባሪዎች እንዲሆኑ ያበረታታሉ። ይሁንና አንድ መንግሥት ከአምላክ ሕግ ጋር በቀጥታ የሚጋጭ ነገር እንዲፈጽሙ በሚጠይቃቸው ጊዜ ይህን ለማድረግ ፈቃደኞች አይሆኑም። “ከሰው ይልቅ አምላክን” እንደ ገዢያቸው አድርገው ይታዘዛሉ።—የሐዋርያት ሥራ 5:29፤ ሮም 13:1-7

የይሖዋ ምሥክሮች በአካባቢያቸው ወደሚገኙ ሰዎች ሁሉ በመሄድ መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ እንዲማሩ ግብዣ ያቀርቡላቸዋል። ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ልብ ለመለወጥ አስችሏል። የይሖዋ ምሥክሮች፣ በየዓመቱ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንደ ማጨስ፣ ስካር፣ ዕፅ መውሰድ፣ ቁማርና ልቅ የፆታ ብልግና ካሉ ጎጂ ልማዶች መላቀቅ እንዲችሉ ይረዳሉ። እነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሕይወታቸው እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችሉ ስለተማሩ ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸውና ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች መሆን ችለዋል።—“መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” የሚለውን በዚህ መጽሔት ገጽ 18 ላይ የሚገኘውን ርዕስ ተመልከት።

በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የቤተሰብ አባላት አንዳቸው ለሌላው ያላቸው አክብሮት እንዲጨምር ያደርጋል፤ ከዚህም ሌላ ባልና ሚስት፣ ወላጆችና ልጆች እንዲሁም ልጆች እርስ በርሳቸው ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። በቤተሰብ አባላት መካከል አክብሮትና ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ መኖሩ ግንኙነታቸው ጠንካራ እንዲሆን ያደርጋል። ጠንካራ ቤተሰቦች ደግሞ ጠንካራ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ የቀረቡትን ነጥቦች ከመረመርክ በኋላ ምን መደምደሚያ ላይ ደረስክ? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሃይማኖት በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ መግባቱን የሚደግፍ ይመስልሃል? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለውን ጥምረት የማይደግፍ መሆኑ አሌ የማይባል ሐቅ ነው። ይህ ሲባል ታዲያ እውነተኛ ክርስቲያኖች ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች አይሆኑም ማለት ነው? በፍጹም! እንዲያውም፣ ኢየሱስ የምድር ጨው እና የዓለም ብርሃን እንዲሆኑ የሰጠውን ትእዛዝ በመከተል ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች መሆናቸውን ማሳየት አለባቸው።

ክርስቶስ የሰጣቸውን መመሪያዎች በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ የሚጥሩ ሁሉ ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን አልፎ ተርፎም የሚኖሩበትን ማኅበረሰብ ይጠቅማሉ። በአካባቢህ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በማኅበረሰቡ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር ስለሚያካሂዱት እንቅስቃሴ ተጨማሪ መረጃ ሊሰጡህ ፈቃደኞች ናቸው። *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የበለጠ ለማወቅ www.watchtower.org የተባለውን ድረ ገጽም መጎብኘት ትችላለህ።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ኢየሱስ ለመለወጥ የሞከረው ፖለቲካዊ ተቋማትን ሳይሆን የሰዎችን ልብ ነበር

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ ዜጎች የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ