የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማወቅ የሚችል አለ?
ጥቂቶቹ ቢሳኩም አብዛኞቹ መና ቀርተዋል
ስለ ወደፊት ሕይወትህ ብታውቅ ደስ ይልሃል? ብዙዎች ስለ ወደፊት ሕይወታቸው ማወቅ ይፈልጋሉ። በርካታ ሰዎች ወደፊት ስለሚፈጸሙ ክስተቶች ይተነብያሉ፤ ይሁንና ስለ ውጤቱ ምን ማለት ይችላል? እስቲ የሚከተሉትን ምሳሌዎች እንመልከት።
-
የሳይንስ ሊቃውንት የተራቀቁ መሣሪያዎችን በመጠቀምና ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በማፍሰስ ስለተለያዩ ጉዳዮች፣ ለምሳሌ የአካባቢ ብክለት ውሎ አድሮ በምድር ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ እንዲሁም በቀጣዩ ቀን በአካባቢህ ዝናብ ይጥል እንደሆነና እንዳልሆነ ይተነብያሉ።
-
ተንታኞች በንግዱና በፖለቲካው ዓለም ውስጥ ያሉ ሁኔታዎች ወዴት እያመሩ እንዳሉ ይተነብያሉ። በዓለም ላይ እጅግ ሀብታም ከሆኑት ሰዎች አንዱ የሆነው ዋረን ባፌት፣ የንግድ ሁኔታዎችን አስመልክቶ የተነበያቸው ነገሮች ትክክል በመሆናቸው አንዳንዶች “ነቢይ” ብለው ጠርተውታል። ኔት ሲልቨር የተባለ ሌላ ተንታኝ ደግሞ አኃዛዊ መረጃዎችን በመጠቀም ከዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲካ አንስቶ እስከ ሆሊውድ የፊልም ተሸላሚዎች ድረስ ስለተለያዩ ነገሮች ይተነብያል።
-
ጥንታዊ ምንጮች እንደ ትንቢት የሚታዩበት ጊዜ አለ። አንዳንድ ሰዎች በ16ኛው መቶ ዘመን የኖረው ኖስትራዳመስ (ሚሼል ዴ ኖትረዳም) የጻፋቸው ግልጽ ያልሆኑ ጽሑፎች በዘመናችን ፍጻሜ እያገኙ እንደሆነ ይሰማቸዋል። አንዳንዶች የማያዎች የዘመን መቁጠሪያ ትንቢታዊ መልእክት ያለው እንደሆነ በማመናቸው የቀን መቁጠሪያው በታኅሣሥ 21 ቀን 2012 ሲያበቃ አስፈሪ ነገር እንደሚከሰት ጠብቀው ነበር።
-
የሃይማኖት መሪዎች ሰዎችን ለማስጠንቀቅና ተከታዮችን ለመሰብሰብ ሲሉ አስፈሪ ዓለም አቀፍ ክስተቶች እንደሚደርሱ የሚተነብዩበት ጊዜ አለ። የምፅአት ቀን ነቢይ የሆነው ሃሮልድ ካምፒንግ እና ደቀ መዛሙርቱ ምድር በ2011 ትጠፋለች ብለው በሰፊው አውጀው ነበር። ዓለማችን ግን አሁንም ድረስ አለች።
-
ዘመናዊ ጠንቋዮች ስለ ወደፊቱ ጊዜ የመተንበይ ልዩ ችሎታ እንዳላቸው ይናገራሉ። ኤድጋር ካሴ እና ጄን ዲክሰን በ20ኛው መቶ ዘመን ላይ እንደሚፈጸሙ ከተናገሯቸው ነገሮች መካከል የተወሰኑት በትክክል ተፈጽመዋል። ይሁን እንጂ ሁለቱም ከተናገሯቸው ነገሮች መካከል ብዙዎቹ አልተፈጸሙም። ለምሳሌ ያህል፣ ዲክሰን ሦስተኛው የዓለም ጦርነት በ1958 ይፈነዳል ብላ ተንብያ ነበር፤ እንዲሁም ካሴ በ1970ዎቹ አጋማሽ ላይ የኒው ዮርክ ግዛት ውቅያኖስ ውስጥ እንደምትሰጥም ተንብዮ ነበር።
ለመሆኑ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማወቅ የምንችልበት አስተማማኝ የሆነ መንገድ አለ? ይህ ጥያቄ መነሳቱ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ወደፊት የሚመጡትን ነገሮች አስቀድመህ ማየት ብትችል ኖር ሕይወትህ አሁን ካለው በእጅጉ የተለየ ይሆን ነበር።