በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የአምላክ መንግሥት ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?

የአምላክ መንግሥት ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?

የአምላክ መንግሥት ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተስፋቸውን በአምላክ መንግሥት ላይ አድርገዋል። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ ይከተላሉ፤ ኢየሱስ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ . . . በምድር ትሁን” በማለት እንዲጸልዩ ተከታዮቹን አስተምሯል።—ማቴዎስ 6:10 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የሚገርመው ነገር፣ የአምላክ መንግሥት የብዙ ሰዎችን ትኩረት የሳበ ነገር ቢሆንም በአብዛኞቹ ሃይማኖቶች ውስጥ ትኩረት የተሰጠው አይመስልም። የታሪክ ምሁር የሆኑት ኸርበርት ጆርጅ ዌልስ እንዲህ ብለዋል፦ “ኢየሱስ መንግሥተ ሰማያት በማለት ስለጠራው ነገር ለማስተማር ከፍተኛ ቦታ ይሰጥ የነበረ ቢሆንም አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ስለዚህ ጉዳይ ያን ያህል አለማስተማራቸው . . . ይገርማል።”

ከእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት በተቃራኒ የይሖዋ ምሥክሮች ለአምላክ መንግሥት ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። ለምሳሌ ያህል አሁን እያነበብከው ያለው ዋነኛው መጽሔታችን በ220 ቋንቋዎች ይታተማል። እንዲሁም እያንዳንዱ እትም ወደ 46 ሚሊዮን በሚጠጉ ቅጂዎች ይታተማል፤ ይህም በዓለም ላይ በብዛት በመሰራጨት ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው መጽሔት እንዲሆን አድርጎታል። ታዲያ የዚህ መጽሔት ዋና መልእክት ምንድን ነው? የመጽሔቱ ሙሉ ርዕስ “የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ” እንደሚል ልብ በል። *

የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት ለማወጅ ወይም ለማስታወቅ ይህን ያህል ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉት ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት በዓለም ላይ ካሉት መጻሕፍት ሁሉ የላቀ የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ መልእክት የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ስለምናምን ነው። ከዚህም ሌላ በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሱት ችግሮች ብቸኛው እውነተኛ መፍትሔ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ እናምናለን።

የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ሰዎች ትኩረታቸውን በአምላክ መንግሥት ላይ እንዲያደርጉ ይረዳሉ። ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ በሕይወቱና በአገልግሎቱ ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው የአምላክ መንግሥት ነበር። (ሉቃስ 4:43) ኢየሱስ ለዚህ መንግሥት ትልቅ ቦታ የሰጠው ለምንድን ነው? የአምላክ መንግሥት ለአንተስ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ በሚቀጥሉት ርዕሶች ውስጥ እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።

^ አን.5 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።