በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ነቅታችሁ ጠብቁ!

ሃይማኖትና የዩክሬን ጦርነት—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሃይማኖትና የዩክሬን ጦርነት—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ታዋቂ የሃይማኖት መሪዎች በዩክሬን እየተካሄደ ስላለው ጦርነት የሰጡትን አስተያየት በተመለከተ የወጡትን የሚከተሉትን ዘገባዎች ተመልከት፦

  •   “የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሪ የሆኑት ፓትርያርክ ኪሪል፣ ሩሲያ ያካሄደችውን ወረራ የሚያወግዝ አንዲትም ቃል አልተናገሩም። . . . ቤተ ክርስቲያናቸው ስለ ዩክሬን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ መንዛቷን ቀጥላለች፤ ፑቲንም ይህን ፕሮፖጋንዳ ጦርነት ማወጃቸው ተገቢ እንደሆነ ለማሳየት እየተጠቀሙበት ነው።”—ኢዩኦብዘርቨር፣ መጋቢት 7, 2022

  •   “ፓትርያርክ ኪሪል . . . ጦርነቱ ከኃጢአት ጋር የሚደረገው ትግል አንዱ አካል እንደሆነ በመግለጽ አገራቸው ዩክሬንን መውረሯ ተገቢ ነው በማለት ሽንጣቸውን ገትረው ተሟግተዋል።”—ኤፒ ኒውስ፣ መጋቢት 8, 2022

  •   “የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሪ የሆኑት የኪየቩ ቀዳማዊ ሜትሮፖሊታን ኢፒፋነስ፣ ሰኞ ዕለት ‘ከሩሲያ ወራሪዎች ጋር እንዲዋጋ’ ሕዝባቸውን ባርከዋል’ . . . በተጨማሪም የሩሲያን ወታደሮች መግደል ኃጢያት አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።”—ጀሩሳሌም ፖስት፣ መጋቢት 16, 2022

  •   እኛ [የዩክሬን አብያተ ክርስቲያናትና ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ምክር ቤት (ዩሲሲአርኦ)] የዩክሬንን ጦር ሠራዊትና ከጎናችን የተሰለፉትን ሁሉ እንደግፋለን፤ ዩክሬንን ከወራሪው ኃይል ለመታደግ የሚያደርጉትን ተጋድሎ በመደገፍ ቃለ ቡራኬ እናቀርባለን፤ እንዲሁም እንጸልይላቸዋለን።”—ዩሲሲአርኦ a ስቴትመንት፣ የካቲት 24, 2022

 ታዲያ ምን ትላለህ? ኢየሱስ ክርስቶስን እንከተላለን የሚሉ ሃይማኖቶች ምዕመኖቻቸው ለጦርነት እንዲዘምቱ መቀስቀስ ይኖርባቸዋል? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

በታሪክ ዘመናት ሃይማኖት በጦርነት የተጫወተው ሚና

 ታሪክ እንደሚያሳየው ሃይማኖቶች ለሰላም የቆሙ ቢመስሉም እንኳ ጦርነትን በዝምታ ሲያልፉ፣ ሲደግፉ አልፎ ተርፎም ጦርነትን ሲያራግቡ ኖረዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ለዘመናት እንዲህ ዓይነቱን ሃይማኖታዊ ግብዝነት ሲያጋልጡ ቆይተዋል። በጽሑፎቻችን ላይ የወጡትን አንዳንድ ምሳሌዎች ተመልከት።

የክርስትና ሃይማኖቶች ጦርነትን ሊደግፉ ይገባል?

 ኢየሱስ ምን አስተምሯል? “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።” (ማቴዎስ 22:39) “ጠላቶቻችሁን ውደዱ።”—ማቴዎስ 5:44-47

 ምን ትላለህ?፦ አንድ ሃይማኖት ተከታዮቹ በጦርነት ሌሎችን እንዲገድሉ እያበረታታ ኢየሱስ ስለ ፍቅር የሰጠውን ትእዛዝ እንደሚያከብር ሊናገር ይችላል? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት “እውነተኛ ክርስቲያኖችና ጦርነት” (እንግሊዝኛ) እንዲሁም “ጠላትን መውደድ ይቻላል?” የሚሉትን ርዕሶች አንብብ።

 ኢየሱስ ምን አስተምሯል? “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም። መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል ቢሆን ኖሮ በአይሁዳውያን እጅ እንዳልወድቅ አገልጋዮቼ ይዋጉልኝ ነበር።” (ዮሐንስ 18:36) “ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ።”—ማቴዎስ 26:47-52

 ምን ትላለህ?፦ ክርስቲያኖች ኢየሱስን ከጥቃት ለመጠበቅ እንኳ መዋጋት ከሌለባቸው በሌላ ምክንያት መዋጋት ይኖርባቸዋል? የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የኢየሱስን አርዓያና ትምህርቶች እንዴት በጥብቅ ይከተሉ እንደነበረ ለማየት “ክርስትና ጦርነትን ይደግፋል?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

ጦርነትን የሚደግፉ ሃይማኖቶች ምን ይጠብቃቸዋል?

 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን እንከተላለን እያሉ ትምህርቶቹን የማይታዘዙ ሃይማኖቶችን አምላክ እንደማይቀበል ይገልጻል።—ማቴዎስ 7:21-23፤ ቲቶ 1:16

  •   የራእይ መጽሐፍ፣ አምላክ ሃይማኖቶችን ‘በምድር ላይ ለታረዱ ሰዎች ሁሉ ደም’ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ይገልጻል። (ራእይ 18:21, 24) የበለጠ ማብራሪያ ለማግኘት “ታላቂቱ ባቢሎን ማን ናት?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

  •   ኢየሱስ የበሰበሰ ፍሬ የሚያፈራ የበሰበሰ ዛፍ ‘ተቆርጦ ወደ እሳት እንደሚጣል’ ሁሉ መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው ሃይማኖቶች በሙሉ እንደሚጠፉ አመልክቷል። (ማቴዎስ 7:15-20) ይህ የሚፈጸመው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ “የሐሰት ሃይማኖት የሚጠፋበት ጊዜ ቀርቧል!” የተባለውን ርዕስ አንብብ።

Photo credits, left to right: Photo by Sefa Karacan/Anadolu Agency/Getty Images; Maxym Marusenko/NurPhoto via Getty Images

a ዩሲሲአርኦ ወይም የዩክሬን አብያተ ክርስቲያናትና ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ምክር ቤት ኦርቶዶክስን፣ የግሪክና የሮም ካቶሊክን፣ ፕሮቴስታንትንና የተለያዩ የወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያኖችን የሚወክሉ 15 አብያተ ክርስቲያናትን እንዲሁም የአይሁድና የእስልምና ሃይማኖቶችን ያቀፈ ነው።