በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአነስተኛ ገቢ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?

በአነስተኛ ገቢ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?

 በኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት በአነስተኛ ገቢ ለመኖር ተገደሃል? ወረርሽኞች፣ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የእርስ በርስ ግጭቶች በድንገት የኢኮኖሚ ቀውስ ሊፈጥሩ ይችላሉ። ሳይታሰብ መተዳደሪያህን ማጣትህ ውጥረት ሊፈጥርብህ ቢችልም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር በአነስተኛ ገቢ መኖር እንድትችል ይረዳሃል።

1. ሁኔታህ መቀየሩን አምነህ ተቀበል።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ብዙ አግኝቶም ሆነ አጥቶ መኖር የሚቻልበትን ሚስጥር ተምሬአለሁ።”—ፊልጵስዩስ 4:12

 የቀድሞውን ያህል ገንዘብ ባይኖርህም ከአዲሱ ሁኔታህ ጋር መላመድ ትችላለህ። ያለህበትን ሁኔታ ቶሎ አምነህ በመቀበል ማስተካከያ ማድረግህ አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ችግሩን በተሻለ ሁኔታ እንድትቋቋሙ ይረዳችኋል።

 መንግሥት ወይም የእርዳታ ድርጅቶች ያደረጉት የድጎማ ዝግጅት ካለ ለማጣራት ሞክር። አፋጣኝ እርምጃ ውሰድ፤ ምክንያቱም እንዲህ ያሉ የእርዳታ ዝግጅቶችን ለማግኘት ማመልከቻ ማስገባት የሚቻልበት ጊዜ የተገደበ ሊሆን ይችላል።

2. በቤተሰብ ደረጃ ተባብራችሁ ሥሩ።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “መመካከር ከሌለ የታቀደው ነገር ሳይሳካ ይቀራል፤ በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል።”—ምሳሌ 15:22

 ከባለቤትህና ከልጆችህ ጋር ስለ ሁኔታው ተነጋገር። በቤተሰብ ደረጃ መነጋገራችሁ እያንዳንዱ የቤተሰቡ አባል ስላላችሁበት ሁኔታ ጥሩ ግንዛቤ እንዲኖረውና አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችን ማድረግ እንዲችል ያደርጋል። ሁሉም ሰው ገንዘብ ለመቆጠብና ብክነት ለመቀነስ ተባብሮ የሚሠራ ከሆነ ገንዘባችሁ ይበረክታል።

3. ገቢና ወጪህን አስላ።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ‘ተቀምጣችሁ ወጪያችሁን አስሉ።’—ሉቃስ 14:28

 በአነስተኛ ገቢ ለመኖር ከተገደድክ እያንዳንዷ ሳንቲም በምን ላይ እያዋለች እንዳለ ማወቅህ በጣም አስፈላጊ ነው። ገቢና ወጪህን ለማስላት በመጀመሪያ አዲሱን ወርሃዊ ገቢህን አስፍር። ቀጥሎም እስካሁን ያለብህን ወርሃዊ ወጪ በዝርዝር ጻፍ፤ እርግጥ ከዚህ በኋላ በወጪዎችህ ረገድ ማስተካከያ ማድረግ ሊኖርብህ ይችላል። ለድንገተኛ ሁኔታ ብለህ የምትመድበውን ገንዘብም በወርሃዊ የወጪ ዝርዝርህ ውስጥ ለማካተት ሞክር።

 ጠቃሚ ምክር፦ ወጪህን ስታሰፍር ጥቃቅን ወጪዎችንም ማካተት እንዳለብህ አትዘንጋ። እነዚህ ወጪዎች ሲደመሩ ምን ያህል እንደሚሆኑ ስታውቅ ትገረም ይሆናል። ለምሳሌ አንድ ሰው ወጪውን በዝርዝር ከጻፈ በኋላ በየዓመቱ ለማስቲካ በመቶዎች የሚቆጠር ዶላር እንደሚያወጣ ተገንዝቧል።

4. እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ ወጪዎችን በመለየት ማስተካከያ አድርግ።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”—ፊልጵስዩስ 1:10

 ገቢህንና ወጪህን በማወዳደር አሁን ባለህ አነስተኛ ገቢ ለመኖር የትኞቹን ወጪዎች መቀነስ ወይም ማስቀረት እንደምትችል ለይ። የሚከተሉትን ዘርፎች ገምግም፦

  •   መጓጓዣ። ከአንድ በላይ መኪና ካለህ አንዱን መሸጥ ትችል ይሆን? የምትነዳው የቅንጦት መኪና ከሆነ እሱን ሸጠህ ወጪ ቆጣቢ የሆነ መኪና መግዛት ትችል ይሆን? አሊያም ደግሞ ከናካቴው መኪና ትተህ የሕዝብ መጓጓዣ ወይም ብስክሌት መጠቀም ትችል ይሆን?

  •   መዝናኛ። ገንዘብ የሚያስከፍሉ የኢንተርኔት፣ የሳተላይት ወይም የቴሌቪዥን አገልግሎቶችን ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ ማቋረጥ ትችል ይሆን? ብዙ ወጪ የማያስወጡ አማራጮችን ማግኘት ትችል ይሆን? ለምሳሌ አንዳንድ ቤተ መጻሕፍቶች ፊልሞችን፣ ኤሌክትሮኒክ መጽሐፎችን ወይም በድምፅ የተቀዱ መጽሐፎችን በነፃ ያውሱ ይሆናል።

  •   የኃይልና የውኃ ወጪዎች። የውኃ፣ የኤሌክትሪክና የነዳጅ ወጪያችሁን መቀነስ ስለምትችሉበት መንገድ በቤተሰብ ደረጃ ተነጋገሩ። አምፖል ማጥፋትና አጠር ያለ ሻወር መውሰድ ያን ያህል ለውጥ የሚያመጣ ባይመስልም እንዲህ ያሉት ልማዶች ገንዘብ ሊቆጥቡ ይችላሉ።

  •   ምግብ። ምግብ ቤት ከመመገብ ተቆጠብ። ከዚህ ይልቅ ቤት ውስጥ ማብሰል የተሻለ ነው። ምን ዓይነት ምግብ እንደምትመገብ አስቀድመህ ወስን፤ የሚቻል ከሆነ ምግብ ለማብሰል የሚያስፈልጉ ነገሮችን በብዛት በመግዛት ለብዙ ቀን የሚሆን ምግብ አብስል፤ የተረፈ ምግብ ላለመድፋት ጥረት አድርግ። አስቤዛ ለመግዛት ከመውጣትህ በፊት የምትገዛውን ነገር ዝርዝር አዘጋጅ፤ ይህም ያለዕቅድ ከመግዛት እንድትቆጠብ ይረዳሃል። በአካባቢው የሚበቅሉ ነገሮች አብዛኛውን ጊዜ ረከስ ስለሚሉ እንደዚህ ያሉ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን ግዛ። ለጤና ጠቃሚ ያልሆኑ ምግቦችን ከመግዛት ተቆጠብ። የሚቻል ከሆነ የጓሮ አትክልቶችን ትከል።

  •   አልባሳት። ፋሽን ለመከተል ብለህ ሳይሆን ልብስ ሲያረጅብህ ብቻ ግዛ። ቅናሽ የተደረገባቸውን አልባሳት ወይም በጥሩ ይዞታ ላይ የሚገኙ ሳልባጅ ልብሶችን ለማግኘት ሞክር። የአየሩ ሁኔታና የመኖሪያ አካባቢህ አመቺ ከሆነ ልብሶችን አስጥተህ አድርቅ፤ ይህም የልብስ ማድረቂያ ማሽን ለመጠቀም የሚውለውን የኤሌክትሪክ ወጪ ይቆጥብልሃል።

  •   ግዢ። አንድ ነገር ከመግዛትህ በፊት ‘አቅሜ ይፈቅዳል? በእርግጥ ዕቃው ያስፈልገኛል?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን፣ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን ወይም መኪናዎችን ሳትቀይር የበፊቱን እየተጠቀምክ መቆየት ትችል ይሆን? በሌላ በኩል ደግሞ የማትጠቀምበት ዕቃ ካለ ብትሸጠውስ? እንዲህ ማድረግህ ኮተት የሚቀንስልህ ከመሆኑም ሌላ ተጨማሪ ገቢ ሊያስገኝልህ ይችላል።

 ጠቃሚ ምክር፦ ገቢህ በድንገት መቀነሱ ገንዘብ የሚያባክኑ ጎጂ ሱሶችን ለማቆም ሊያነሳሳህ ይችላል፤ ከእነዚህ መካከል ሲጋራ ማጨስ፣ ቁማር መጫወት ወይም የአልኮል ሱስ ይገኙበታል። እነዚህን ሱሶች ማስወገድህ ገንዘብ የሚቆጥብልህ ከመሆኑም ሌላ ይበልጥ ደስተኛ እንድትሆን ይረዳሃል።

5. ለመንፈሳዊ ነገሮች ትኩረት ስጥ።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው።”—ማቴዎስ 5:3

 መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብ ጥበቃ እንደሚያስገኝ ሁሉ ጥበብም ጥበቃ ታስገኛለችና፤ የእውቀት ብልጫ ግን፣ ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት ጠብቃ ማቆየት መቻሏ ነው” የሚል ሚዛናዊ ምክር ይሰጣል። (መክብብ 7:12) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህ ያለው ጥበብ ይገኛል፤ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ በሥራ ላይ ማዋላቸው ስለ ገንዘብ ከልክ በላይ እንዳይጨነቁ ረድቷቸዋል።—ማቴዎስ 6:31, 32