በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሐምሌ 14, 2023
ሜክሲኮ

ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የመጀመሪያዎቹ አራት መጻሕፍት በናዋትል (ሁዋስቴካ) ቋንቋ ወጡ

ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የመጀመሪያዎቹ አራት መጻሕፍት በናዋትል (ሁዋስቴካ) ቋንቋ ወጡ

ሐምሌ 7, 2023 ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ የመጀመሪያዎቹ አራት መጻሕፍት በናዋትል (ሁዋስቴካ) ቋንቋ መውጣታቸውን የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ዃን አንኪል ኸርናንዴዝ አበሰረ። የመጻሕፍቱ መውጣት የተነገረው “በትዕግሥት ጠብቁ”! በተባለው የክልል ስብሰባ የመጀመሪያ ዕለት ነበር፤ ስብሰባው የተካሄደው በኢዳልሆ፣ ሜክሲኮ ሲሆን ትምህርቱ የቀረበው በናዋትል (ሁዋስቴካ) ቋንቋ ነው። በሜክሲኮ ግዛት እንዲሁም በኑዌቮ ልዮን፣ ሜክሲኮ በተካሄዱት የክልል ስብሰባዎች ላይ የተገኙት ሰዎች የእነዚህን መጻሕፍት መውጣት በቀጥታ ስርጭት መከታተል ችለዋል። በአጠቃላይ 2,401 ሰዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል። ንግግሩ እንዳበቃም የእነዚህን መጻሕፍት የኤሌክትሮኒክና የድምፅ ቅጂዎች ከኢንተርኔት ላይ ማውረድ ተችሏል።

በናዋትል (ሁዋስቴካ) ቋንቋ የተዘጋጁ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ቢኖሩም የይሖዋን ስም አልያዙም። በተጨማሪም የሚጠቀሙበት ቋንቋ ብዙውን ጊዜ ለመረዳት አስቸጋሪ ነው። ከተርጓሚዎቹ አንዱ እንዲህ ብሏል፦ “ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ማንበብ በጉም በተሸፈነ መስታወት እንደመጠቀም ነው። ይህ አዲስ ትርጉም ግን ጥርት ባለ መስታወት እንደማየት ሆኖልናል። አሁን አንባቢዎች ቃላቱ ምን ትርጉም እንዳላቸው ለመረዳት ከመታገል ይልቅ የአምላክ ቃል የሚያስተላልፈው ትምህርት ላይ ማሰላሰል ይችላሉ። ይሖዋ ግሩም ስጦታ ነው የሰጠን!”

የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሐንስ ወንጌሎችን የያዘው ይህ አዲስ ትርጉም ብዙ የናዋትል (ሁዋስቴካ) ተናጋሪዎች ‘ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋንና የላከውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያውቁ’ እንደሚረዳቸው እርግጠኞች ነን።—ዮሐንስ 17:3