በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጋቢት 2, 2022
ሜክሲኮ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በትላፓኔክ ቋንቋ ወጣ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በትላፓኔክ ቋንቋ ወጣ

የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ካርሎስ ካሳሬስ የካቲት 27, 2022 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በትላፓኔክ ቋንቋ በዲጂታል ፎርማት መውጣቱን አበሰረ። በዚሁ ዓመት ከተወሰኑ ወራት በኋላ የታተመውን ቅጂ ማግኘት ይቻላል። አስቀድሞ የተቀረጸው ፕሮግራም 820 ገደማ ለሚሆኑ ሰዎች ተላልፏል።

የትርጉም ሥራው የተጀመረው ሐምሌ 2020 ማለትም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ነው። አንዱ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “የተለያዩ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም ሥራውን በአንድ ዓመት ተኩል ማጠናቀቅ መቻላችን በጣም አስደናቂ ነው። ይሖዋ ሥራውን አፋጥኖታል።”

የትላፓኔክ የርቀት የትርጉም ቢሮ የሚገኘው በትላፓ፣ ጉዌሬሮ፣ ሜክሲኮ ነው። የትርጉም ቡድኑ የሕንፃውን የላይኞቹን ሦስት ፎቆች ይጠቀማል

አዲሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይበልጥ ግልጽ የሆኑ አገላለጾችን ይጠቀማል። ማቴዎስ 5:3⁠ን እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል። የቀድሞዎቹ ትርጉሞች ይህን ጥቅስ “መንፈስ ቅዱስ ካልረዳቸው በቀር ምንም ነገር ማድረግ እንደማይችሉ የሚያውቁ ደስተኞች ይሆናሉ” ወይም “ደካማ መንፈስ ያላቸው ደስተኞች ናቸው” ብለው ተርጉመውታል። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ግን “አምላክን መፈለግ እንዳለባቸው የሚገነዘቡ ደስተኞች ናቸው” በማለት አስቀምጦታል።

ይህ አዲስ ትርጉም አስፋፊዎች በአገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። ወንድም ካሳሬስ በንግግሩ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉን ቻዩ አምላክ ሰዎች ምሥራቹን ለመረዳት በሚከብዳቸው ቋንቋ ሳይሆን በራሳቸው ቋንቋ፣ በየዕለቱ በሚጠቀሙበት ቋንቋ እንዲሰሙ ይፈልጋል።”

ይሖዋን “በአንድነት” አብረውን የሚያገለግሉት የትላፓኔክ ቋንቋ ተናጋሪ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይህን አዲስ መጽሐፍ ቅዱስ በማግኘታቸው በጣም ተደስተናል።—ሶፎንያስ 3:9 የግርጌ ማስታወሻ