በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

አንድሬና ባለቤቱ ስቬትላና፣ አንድሬ ከቁም እስር እንዲለቀቅ ከተወሰነ በኋላ ከፍርድ ቤቱ ውጭ ሆነው

ነሐሴ 22, 2019
ሩሲያ

ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ወንድም አንድሬ ሱቮርኮቭ ከቁም እስር እንዲለቀቅ ወሰነ

ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ወንድም አንድሬ ሱቮርኮቭ ከቁም እስር እንዲለቀቅ ወሰነ

ነሐሴ 13, 2019 የኪሮቭ ከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የ26 ዓመቱ ወንድም አንድሬ ሱቮርኮቭ ከቁም እስር እንዲለቀቅ ወሰነ። ወንድም ሱቮርኮቭ ተጨማሪ ነፃነት ቢያገኝም በእሱ ላይ የተመሠረተው የወንጀል ክስ አልተዘጋም።

ቀደም ሲል እንደተዘገበው ወንድም ሱቮርኮቭ ከእንጀራ አባቱና ከሌሎች ሦስት ወንድሞች ጋር የታሰረው ጥቅምት 9, 2018 የአካባቢው ፖሊሶችና ጭምብል ያጠለቁ ልዩ ኃይሎች በኪሮቭ የሚገኙ 19 ቤቶችን በፈተሹበት ወቅት ነበር።

ወንድም ሱቮርኮቭ ቤቱ ስለተበረበረበት ጊዜ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ውድ ንብረቶች ተወስደውብናል። እኔና ባለቤቴ ግን ቀላል ሕይወት ስለምንመራና ለቁሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ ስለማንሰጥ ብዙም አልተጨነቅንም። በማቴዎስ 6:21 ላይ የሚገኘው ‘ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይሆናልና’ የሚለው ምክር እንድንረጋጋ ረድቶናል።”

ከፍተሻው በኋላ ወንድም ሱቮርኮቭ፣ እንጀራ አባቱና ሌሎቹ ሦስት ወንድሞች መንፈሳዊ መዝሙሮችን በመዘመራቸው፣ ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን በማጥናታቸውና በሩሲያኛ የተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በእጃቸው ላይ በመገኘቱ ክስ ተመሠረተባቸው። ፍርድ ቤቱ እነሱን ለመልቀቅ አሊያም እስኪፈረድባቸው ድረስ እስር ቤት እንዲቆዩ ለማድረግ እስኪወስን ድረስ ሁሉም ወደ ማረፊያ ቤት ተወሰዱ።

ወንድም ሱቮርኮቭ ሁኔታውን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ማረፊያ ቤቱ ውስጥ ሁለት ቀን አደርኩ። መጀመሪያ ላይ ያለማቋረጥ እጸልይ ነበር። ይሖዋ ጸሎቴን እንደሚሰማና እንደሚደግፈኝ እርግጠኛ ነበርኩ። የመዝሙሮቻችንን ዜማ እያስታወስኩ መዘመር ጀመርኩ። ከ50 በላይ መዝሙሮችን ከነግጥማቸው ማስታወስ ችያለሁ።”

ፍርድ ቤቱ ወንድም ሱቮርኮቭና ሌሎቹ ወንድሞች እስኪፈረድባቸው ድረስ እስር ቤት እንዲቆዩ ወሰነ። ታስረው በነበሩበት በመጀመሪያው ሳምንት ላይ ወንድም ሱቮርኮቭ ሌሎችን ለመርዳት ጥረት ያደርግ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “የወንድሞችን ስም እየጠቀስኩ ለመጸለይና አድራሻቸው ላለኝ ወንድሞች አበረታች ደብዳቤዎች ለመጻፍ ወሰንኩ። እንዲህ ማድረጌ ደስታ አስገኝቶልኛል።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35

ከተወሰኑ ወራት በኋላ ከወንድም አንጄይ ኦኒስጁክ በስተቀር ሁሉም ወንድሞች ከእስር ቤት ወደ ቁም እስር ተዛወሩ። በቁም እስር ካሉት የኪሮቭ ወንድሞች መካከል መጀመሪያ የተለቀቀው ወንድም ሱቮርኮቭ ነው።

ወንድም ሱቮርኮቭ እንዲህ ብሏል፦ “መለስ ብዬ ሳስበው በእስር ቤት እንዲህ ያለ ተሞክሮ በማሳለፌ በጣም ደስተኛ ነኝ። . . . ወደፊት ምን እንደሚያጋጥመኝ አላውቅም፤ እንደገና ልታሰር እችላለሁ። ሆኖም እስር ቤት ብሆንም እንኳ የይሖዋና የድርጅቱ ድጋፍ እንደማይለየኝ እርግጠኛ መሆን ችያለሁ። ከዚህ በኋላ መታሰር አያስፈራኝም።”