በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የካቲት 22, 2023
ናይጄርያ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በፒጅን (ምዕራብ አፍሪካ) እና በኡሮቦ ቋንቋዎች ወጣ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በፒጅን (ምዕራብ አፍሪካ) እና በኡሮቦ ቋንቋዎች ወጣ

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ዊንደር፣ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በፒጅን (ምዕራብ አፍሪካ) እና በኡሮቦ ቋንቋዎች መውጣታቸውን አብስሯል። የካቲት 12, 2023 ይህን ያበሰረበት ፕሮግራም ለጉባኤዎች በቀጥታ የተላለፈ ሲሆን በናይጄርያ በድምሩ 559,326 ሰዎች ተከታትለውታል። መጽሐፍ ቅዱሶቹ መውጣታቸው እንደተነገረ ኤሌክትሮኒክ ቅጂዎች ኢንተርኔት ላይ ተለቅቀዋል። የታተሙት ቅጂዎች ደግሞ በ2023 ትንሽ ቆየት ብሎ አንባቢዎች እጅ እንደሚገቡ ይጠበቃል።

በ2015 የመጀመሪያው የፒጅን (ምዕራብ አፍሪካ) ጉባኤ ተቋቋመ። በአሁኑ ወቅት ናይጄርያ ውስጥ ከ1,100 በላይ የፒጅን (ምዕራብ አፍሪካ) ጉባኤዎች አሉ፤ በሌሎች አገራትም ለምሳሌ በእንግሊዝ እና በአሜሪካ በርካታ የፒጅን ጉባኤዎች ተቋቁመዋል። ቀደም ሲል ጉባኤዎቹ እንግሊዝኛውን አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ከመጠቀም ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም። አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ከዚህ በፊት በፒጅን እየሰበክን፣ ጥቅስ የምናነበው ከእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር፤ ይህ ትንሽ የማይመች ነበር። የምናነጋግራቸው ሰዎች ያነበብነውን ጥቅስ መረዳት የሚቸግራቸው ጊዜ ነበር። አሁን ግን በፒጅን እንሰብካለን፤ ከፒጅን መጽሐፍ ቅዱስ ላይም እናነብላቸዋለን። ጥቅስ የምናነብላቸው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ከተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለሆነ መልእክታችን ይበልጥ ግልጽ እንደሚሆንላቸው እንጠብቃለን።”

ጽድቅ የሚሰፍንበትን አዲስ ዓለም ተስፋ እያደረጉ መኖር (በአማርኛ አይገኝም) የተሰኘው ወደ ኡሮቦ ቋንቋ የተተረጎመው የመጀመሪያው ቡክሌት

የመጀመሪያው የኡሮቦ ጉባኤ የተቋቋመው በ1933 ነው። በ1968 ወደ ኡሮቦ ቋንቋ የተተረጎመ የመጀመሪያው ቡክሌት ወጣ፤ ቡክሌቱ፣ ጽድቅ የሚሰፍንበትን አዲስ ዓለም ተስፋ እያደረጉ መኖር (እንግሊዝኛ) የተሰኘ ነው። ከዚያ ጊዜ ወዲህ በኡሮቦ የሚመሩ ጉባኤዎች ብዛት 103 ደርሷል። ለዛውን በጠበቀና በቀላሉ በሚገባ ቋንቋ የተተረጎመው የኡሮቦ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ለጉባኤዎቹ በረከት እንደሚሆን እንተማመናለን።

እነዚህ ትርጉሞች፣ ሌሎች ብዙ ሰዎች በአምላክ ፈቃድ “ትክክለኛ እውቀት [እንዲሞሉ]” ያግዙ ዘንድ ጸሎታችን ነው።—ቆላስይስ 1:9