በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከላይ፦ በ1930 በቭሎረ፣ አልባኒያ የነበሩት ወንድሞችና እህቶች። ከላይ በስተ ቀኝ፦ አልባኒያ ውስጥ በተለያየ ዘመን የታተሙ ብሮሹሮች። ከታች በስተ ቀኝ፦ የበላይ አካል አባል የሆነው ዴቪድ ስፕሌን በ2005 በተካሄደው “አምላካዊ ታዛዥነት” የተሰኘ አውራጃ ስብሰባ ላይ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ መውጣቱን ሲያበስር

ጥር 7, 2022
አልባኒያ

አልባኒያ የይሖዋ ምሥክሮች ለበርካታ አሥርተ ዓመታት እገዳ ቢጣልባቸውም ለ100 ዓመት ምሥራቹን ሰብከዋል

አልባኒያ የይሖዋ ምሥክሮች ለበርካታ አሥርተ ዓመታት እገዳ ቢጣልባቸውም ለ100 ዓመት ምሥራቹን ሰብከዋል

በ2022 የይሖዋ ምሥክሮች አልባኒያ ውስጥ መስበክ ከጀመሩ 100 ዓመት ሞላቸው።

ናሾ ኢድሪዚ እውነትን ከተቀበሉት የመጀመሪያዎቹ አልባኒያውያን አንዱ ነው። በ1920ዎቹ መጀመሪያ ላይ በዩናይትድ ስቴትስ ይኖር በነበረበት ወቅት ከዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጠና፤ በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩት በዚህ ስም ነበር።

ናሾ በ1922 ወደ አልባኒያ ተመለሰ። በኋላ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የሆኑ ሌሎች አልባኒያውያንም የተማሩትን ነገር ለሌሎች ለማካፈል ሲሉ ወደ አገራቸው ተመለሱ።

ታናስ ዱሊ

ታናስ ዱሊ በአልባኒያ ከነበሩት የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አንዱ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “በ1925 አልባኒያ ውስጥ ሦስት ጉባኤዎች እንዲሁም በተለያየ ቦታ ተበታትነው የሚኖሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችና ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ነበሩ።”

በወቅቱ የአምላክ በገና እና ተፈላጊ መንግሥት የሚሉትን መጻሕፍት ጨምሮ በርካታ ጽሑፎች ወደ አልባኒያኛ ተተርጉመው ነበር። የታኅሣሥ 1, 1925 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ወጥቶ ነበር፦ “ጥቂት የማይባሉ [የአልባኒያኛ ጽሑፎች] በሕዝቡ እጅ ገብተዋል፤ አልባኒያውያን እውነትን በደስታ እየተቀበሉ ነው።”

አንጂሮ እና ናሾ ዶሪ

የይሖዋ ምሥክሮች በቅንዓት ይሰብኩ ስለነበር ሰዎች ኡንጂሎረ ማለትም “ወንጌላውያን” ብለው ይጠሯቸው ነበር። በ1930 የተጠመቀው ናሾ ዶሪ እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “በ1935 ሰብሰብ ብለን አውቶቡስ ተከራይተን በከልሲረ ከተማ ለመስበክ ሄድን። ከዚያ በኋላ ደግሞ ሰፋ ያለ ዘመቻ አደራጅተን ወደ ፐርሜት፣ ሌስኮቪክ፣ ኤርሴከ፣ ኮርቸ፣ ፖግራዴስ እና ኤልባሳን ከተሞች ሄድን። በመጨረሻም ዘመቻችንን ቲራና ላይ አጠናቀን የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ አከበርን።”

በ1939 ፋሺስት ጣሊያን አልባኒያን ተቆጣጥሮ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እገዳ ጣለ። በዚህ ወቅት ወንድሞቻችን በገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት በግሪኮ ጣሊያን ጦርነት ወቅት ለመዝመት ፈቃደኛ አልሆኑም። a በእነዚያ ዓመታት 15 ወንድሞች እስር ቤት ገብተዋል። ወንድም ኒኮዲም ሺቲ ወደ ማጎሪያ ካምፕ የተላከ ሲሆን ከዚያ በኋላ የደረሰበት አልታወቀም።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መገባደጃ አካባቢ ማለትም በ1944 የኮሚኒስት ፓርቲ በአልባኒያ ሥልጣን ተቆናጠጠ። ሆኖም በወንድሞቻችን ላይ የሚደርሰው ስደት ቀጠለ። በርካታ ወንድሞቻችን ታስረዋል እንዲሁም ተሠቃይተዋል። ሌሎች ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው ርቀው ወደ ጉልበት ሥራ ካምፖች ተልከዋል። በእነዚያ ዓመታት አልባኒያ ከቀሪው ዓለም ተገልላ ቆይታለች። የ1959 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “የአገሪቱ መንግሥት የአልባኒያን ወንድሞች ከቀረው የአዲሱ ዓለም ኅብረተሰብ ቢያቆራርጣቸውም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በእነሱ ላይ እንዳይሠራ ማገድ ግን አይችልም።” አልባኒያ በ1967 የመጀመሪያዋ አምላክ የለሽ አገር ሆነች። ሆኖም በዚያ የቀሩት ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች በጥንቃቄ እምነታቸውን ማራመዳቸውን ቀጥለው ነበር።

የይሖዋ ምሥክሮች ከ50 ዓመታት በላይ በእገዳ ሥር ከቆዩ በኋላ ኮሚኒዝም ሲወድቅ ግንቦት 22, 1992 ሕጋዊ እውቅና አገኙ።

በአሁኑ ወቅት አልባኒያ ውስጥ በ89 ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ 5,550 የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። ከባድ ስደት ቢኖርም “የይሖዋ ቃል በኃይል እየተስፋፋና እያሸነፈ” በመሄዱ ከወንድሞቻችን ጋር አብረን እንደሰታለን።—የሐዋርያት ሥራ 19:20

a የግሪኮ ጣሊያን ጦርነት በግሪክና በጣሊያን መካከል የተካሄደ ውጊያ ነበር፤ ጦርነቱ ጥቅምት 28, 1940 ተጀምሮ ሚያዝያ 23, 1941 አብቅቷል። የሁለተኛው የዓለም ጦርነት የባልካን ዘመቻ የጀመረው በዚህ ጦርነት ነው።