በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የ2023 “በትዕግሥት ጠብቁ”! የክልል ስብሰባ ተሰብሳቢዎች እና የስብሰባው ፕሮግራሞች፤ (በስተ ግራ) በኦልድ ሃርበር፣ ጃማይካ በጃማይካ ክሪኦል ቋንቋ እና (በስተ ቀኝ) በፒትስበርግ፣ ፔንስልቬንያ ዩ ኤስ ኤ በፔንስልቬንያ ጀርመን ቋንቋ

ጥቅምት 18, 2023
ዓለም አቀፋዊ ዜና

በጃማይካ ክሪኦል እና በፔንስልቬንያ ጀርመን ቋንቋዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የክልል ስብሰባዎች ተካሄዱ

በጃማይካ ክሪኦል እና በፔንስልቬንያ ጀርመን ቋንቋዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የክልል ስብሰባዎች ተካሄዱ

ሐምሌ 2023 በጃማይካ ክሪኦል እና በፔንሲልቫኒያ ጀርመን ቋንቋዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የክልል ስብሰባዎች በአካል ተካሂደዋል። “በትዕግሥት ጠብቁ”! የተባለውን የክልል ስብሰባ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ለመከታተል በጉጉት ሲጠባበቁ የነበሩ ወደ 2,000 የሚጠጉ ሰዎች በስብሰባዎቹ ላይ ተገኝተዋል።

የጃማይካ ክሪኦል፣ ጃማይካ

የጃማይካ ክሪኦል ቋንቋ ተናጋሪ እህቶች “እንኳን ደህና መጣችሁ!” የሚል ጽሑፍ ይዘው ለተሰብሳቢዎች አቀባበል ሲያደርጉ

የጃማይካ የሥራ ቋንቋ እንግሊዝኛ ነው። ነገር ግን አብዛኞቹ የደሴቲቱ ነዋሪዎች የጃማይካ ክሪኦልንም ይናገራሉ። በስብሰባው ላይ ከተገኙት 1,700 ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ከዩናይትድ ኪንግደም እና ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡ ነበሩ። ፕሮግራሙ የተካሄደው ከሐምሌ 14 እስከ 16, 2023 ጃማይካ ውስጥ በኦልድ ሃርበር ከተማ በሚገኘው ማርሊ ቴክኖሎጂ ፓርክ ነበር። አሥራ ሁለት ሰዎች ተጠምቀዋል።

የጃማይካ ክሪኦል ተናጋሪ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የክልል ስብሰባ መካፈል በመቻላቸው በጣም ተደስተዋል። እህት ቴኔሻ ጎርደን እንዲህ በማለት የተሰማትን ደስታ ገልጻለች፦ “ፕሮግራሙ ሲጀምርና ወንድም በጃማይካ ክሪኦል ሰላምታ ሲያቀርብ ዓይኔ እንባ አቀረረ። የሰማሁትን ማመን አልቻልኩም። ስብሰባው ባያልቅ ደስ ባለኝ ነበር!”

የፔንስልቬንያ ጀርመን፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ተሰብሳቢዎቹ “ለመጀመሪያው የፔንስልቬንያ ጀርመን የክልል ስብሰባችን እንኳን ደህና መጣችሁ” የሚል ጽሑፍ ይዘው

በካናዳና በዩናይትድ ስቴትስ የፔንስልቬንያ ጀርመን ቋንቋ የሚናገሩ ወደ 400,000 ገደማ ሰዎች አሉ። ይህ የጀርመንኛ ቀበሌኛ በዋነኝነት የሚነገረው ራቅ ብለው በሚኖሩ የአሚሽ እና የሜኖናውያን ማኅበረሰቦች ውስጥ ነው። በፔንስልቬንያ ጀርመን ቋንቋ ከሚመሩ አምስት ጉባኤዎችና አንድ ቡድን የተውጣጡ ወንድሞችና እህቶች በክልል ስብሰባው ላይ ለመገኘት ከተለያዩ ግዛቶች ተሰባስበዋል። ከ200 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከሐምሌ 7 እስከ 9, 2023 በፒትስበርግ፣ ፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የኮራኦፖሊስ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ፕሮግራሙን ተከታትለዋል።

ወንድም ዴቪድ ሚለር ከልጅነቱ ጀምሮ የፔንስልቬንያ ጀርመን ቋንቋን ይናገራል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በእንግሊዝኛ ያጠናው ከ25 ዓመታት በፊት ነው። በወቅቱ በአፍ መፍቻ ቋንቋው የክልል ስብሰባ ሊካሄድ ይቅርና በዚህ ቋንቋ ጉባኤዎች እንኳ ይኖራሉ ብሎ አያስብም ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “እጅግ የሚደንቅ ነው! ፕሮግራሙ በጣም ነበር የመሰጠኝ። ንግግሮቹ የቀረቡት በአፍ መፍቻ ቋንቋዬ ስለነበር ትምህርቱ ልቤን ነክቶኛል።”

በእነዚህ ታሪካዊ ስብሰባዎች ላይ የተገኙትን ወንድሞችና እህቶች ደስታ እኛም እንጋራለን። ይሖዋ አንድነት እንዲኖረን ስለረዳንና ሰዎች ሁሉ ንጹሑን ቋንቋ እንዲናገሩ አጋጣሚውን ስለከፈተ አመስጋኞች ነን።—ሶፎንያስ 3:9