በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በዚምባብዌ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ የ​jw.org ኪዮስክ የብዙ ጎብኚዎችን ትኩረት ስቧል

ሰኔ 13, 2023
ዚምባብዌ

በ2023 በዚምባብዌ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ምሥክርነት ተሰጠ

በ2023 በዚምባብዌ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ምሥክርነት ተሰጠ

ከሚያዝያ 25 እስከ 29, 2023 ዚምባብዌ ውስጥ ቡላዋዮ በተባለች ከተማ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ተካሂዷል። የንግድ ትርዒቱ በአገሪቱ ከሚካሄዱት ትላልቅ አውደ ርዕዮች አንዱ ነው፤ ከ22 አገራት የመጡ 500 ሰዎች ሥራቸውን ለእይታ ያቀረቡበትና ከ60,000 በላይ ጎብኚዎችን የሳበ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የተሳተፉት በአውደ ርዕዩ የትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ላይ ነው።

ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ጎብኚዎችን በማሰብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በ10 ቋንቋዎች ለእይታ ቀርበዋል፤ ከእነዚህ አንዱ የዚምባብዌ ምልክት ቋንቋ ነው። ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ደግሞ አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ኮርስ ተዋውቋል። በአውደ ርዕዩ መጨረሻ ላይ ከ12,000 በላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ተሰራጭተዋል፤ እንዲሁም ከ450 በላይ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው እንዲያነጋግሯቸው ጥያቄ አቅርበዋል። ኪዮስኩ ጋ ጎብኚዎችን ታስተናግድ የነበረች ዩሴቢያ መኩራ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ብዙዎች፣ አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮርሱን እንዲሞክሩ የቀረበላቸውን ግብዣ በደስታ ተቀብለዋል። በጣም ብዙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው እስኪጠይቋቸው በጉጉት እንደሚጠብቁ ሲናገሩ መስማት በጣም የሚያስደስት ነው።”

ኪዮስኩ ላይ ለእይታ ከቀረቡት መጻሕፍት አንዱ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አንድ ሰው ኪዮስኩ ጋ በእንድቤሌ ቋንቋ የተዘጋጀውን ይህን ትርጉም ጮክ ብሎ ሲያነብ አንዲት ሴት ስታልፍ ሰማች፤ የትርጉሙ ግልጽነት በጣም ስላስገረማት አንድ ቅጂ እንዲሰጣት ጠየቀች። አንዲት ወጣት ደግሞ JW Library አፕሊኬሽንን ስልኳ ላይ እንደጫነች በደስታ ለአንዲት እህታችን ነገረቻት። ይህን ለማድረግ የወሰነችውም የራሷ አዲስ ዓለም ትርጉም ቅጂ እንዲኖራት ስለፈለገች እንደሆነ አስረዳቻት።

እንግዶችን ትቀበል የነበረች ጂሊያን ኤለርማን የተባለች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “በጣም ልዩ ተሞክሮ ነው። ሰዎች ያለማቋረጥ ወደ ኪዮስካችን ይመጡ ነበር። ለይሖዋ የሚቀርበው ውዳሴ ደምቆ የተሰማበት አጋጣሚ ነው!”

የዚምባብዌ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን “የእውነትን ትክክለኛ እውቀት” ለሰዎች ለማካፈል አጋጣሚዎቹን ሁሉ እንዴት ግሩም አድርገው እንደሚጠቀሙባቸው ማየት በእርግጥም የሚያበረታታ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 2:4