በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ነሐሴ 16, 2019
ዴንማርክ

የይሖዋ ምሥክሮች በዴንማርክ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ቤተ መዘክር ከፈቱ

የይሖዋ ምሥክሮች በዴንማርክ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ቤተ መዘክር ከፈቱ

ከኮፐንሃገን 65 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በሆልቤክ፣ ዴንማርክ ባለው የይሖዋ ምሥክሮች የስካንዲኔቪያ ቅርንጫፍ ቢሮ ሐምሌ 2019 አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ቤተ መዘክር ተከፈተ። የቤተ መዘክሩ ጭብጥ “መጽሐፍ ቅዱስ እና መለኮታዊው ስም በስካንዲኔቪያ” የሚል ነው።

በቤተ መዘክሩ ላይ በዴኒሽ፣ በፌሮኛ፣ በግሪንላንድኛ፣ በአይስላንድኛ፣ በኖርዌይኛ፣ በሳሚ እና በስዊድንኛ ቋንቋዎች የተዘጋጁ በቀላሉ የማይገኙና ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ከ50 የሚበልጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ቀርበዋል።

በቤተ መዘክሩ ላይ ከቀረቡት ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው መጽሐፍ ቅዱሶች አንዱ በ1541 የተዘጋጀው ጉስታቭ ቫሳ ባይብል ነው። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በስካንዲኔቪያ አገሮች የተዘጋጀው የመጀመሪያው ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ጉስታቭ ቫሳ ባይብል ለስዊድንኛ ቋንቋ ሰዋስውና የቃላት ክምችት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከዚህም በተጨማሪ በቀጣዮቹ 300 ዓመታት በስዊድንኛ ለተዘጋጁት መጽሐፍ ቅዱሶች እንደ ዋነኛ ማመሣከሪያ ሆኖ አገልግሏል።

በ1541 የተዘጋጀው የጉስታቭ ቫሳ ባይብል ዋና ቅጂ በቤተ መዘክሩ ላይ ቀርቦ

በቤተ መዘክሩ ላይ ከቀረቡት በቀላሉ የማይገኙ መጽሐፍ ቅዱሶች ሌላኛው ደግሞ በ1550 የተዘጋጀው የሣልሳዊ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ይህ ትርጉም በዴኒሽ ቋንቋ የተዘጋጀ የመጀመሪያው ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። የሣልሳዊ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ በዴኒሽ ቋንቋ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ ከመሆኑም ሌላ ለአብዛኛው የሰሜን አውሮፓ ሕዝብ ትልቅ ጥቅም አስገኝቷል።

በ1550 የተዘጋጀው የሣልሳዊ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ዋና ቅጂ

በስካንዲኔቪያ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግለው ኤሪክ ዮርገንሰን እንዲህ ብሏል፦ “ይህ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ቤተ መዘክር ስካንዲኔቪያ ውስጥ ላለፉት በርካታ መቶ ዓመታት ለአምላክ ቃል እንዲሁም ለይሖዋ ታላቅ ስም ከፍተኛ ክብር ይሰጥ እንደነበር የሚያሳይ ነው።”