በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ተኩስ የተከፈተበት የስብሰባ አዳራሽ። የሃምበርግ ነዋሪዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናት ሐዘናቸውን ለመግለጽ መግቢያው ላይ አበቦች አስቀምጠዋል

መጋቢት 20, 2023
ጀርመን

በሃምበርግ፣ ጀርመን አንድ ታጣቂ በይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሽ ተኩስ ከፈተ

በሃምበርግ፣ ጀርመን አንድ ታጣቂ በይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሽ ተኩስ ከፈተ

ቀደም ሲል እንደዘገብነው፣ መጋቢት 9, 2023 አንድ ታጣቂ በሃምበርግ ዊንተርሁድ ጉባኤ ተሰብሳቢዎች ላይ ተኩስ ከፍቷል፤ ይህ የሆነው የሳምንቱ መሃል ስብሰባ ካበቃ በኋላ ነበር። ፖሊሶች ወደ አዳራሹ ከመግባታቸው በፊት ግለሰቡ የተወሰኑ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ሕይወት ቀጥፏል፤ በአንዳንዶቹም ላይ ጉዳት አድርሷል። በመጨረሻም የራሱን ሕይወት አጥፍቷል። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ባለሥልጣናት፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች የሐዘን መግለጫዎችን ልከዋል፤ በጀርመንም ሆነ በመላው ዓለም ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ብዙዎች በዚህ መንገድ ላሳዩት ደግነትና ፍቅር በጣም አመስጋኝ ናቸው።

በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት

  • የሚያሳዝነው 4 ወንድሞችና 2 እህቶች ሕይወታቸው አልፏል፤ ነፍሰ ጡር የነበረች አንዲት እህት ደግሞ ፅንሱ ተጨናግፎባታል

  • 2 ወንድሞችና 7 እህቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል

የእርዳታ እንቅስቃሴ

  • የማዕከላዊ አውሮፓ ቅርንጫፍ ቢሮ ተወካዮች፣ ሁለት የወረዳ የበላይ ተመልካቾች እንዲሁም በአካባቢው ያሉ ሽማግሌዎች ማጽናኛና ድጋፍ እየሰጡ ነው

መላው የወንድማማች ማኅበር በዚህ አሳዛኝ ክስተት ለተጎዱት ሁሉ እየጸለየ ነው። ‘በጭንቀት ቀን መሸሸጊያ’ የሆነው ይሖዋ አምላካችን፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እሱን እያመለክን የሚደርሱብንን እነዚህን አስቸጋሪ ሁኔታዎች በጽናት ለማለፍ እንደሚረዳን እንተማመናለን።—ናሆም 1:7