በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በስተ ግራ፦ በአውሎ ነፋሱ የወደመ የስብሰባ አዳራሽ። በስተ ቀኝ፦ በአውሎ ነፋሱ ጉዳት የደረሰበትን አካባቢ የሚያሳይ ካርታ

ግንቦት 28, 2020
ፊሊፒንስ

ቮንግፎንግ የተባለው አውዳሚ አውሎ ነፋስ ፊሊፒንስን መታ

ቮንግፎንግ የተባለው አውዳሚ አውሎ ነፋስ ፊሊፒንስን መታ

ሳማር የተባለችው ደሴት ግንቦት 14, 2020 ላይ ቮንግፎንግ (የአገሪቱ ሰዎች አምቦ በማለት ይጠሩታል) በተባለው አውሎ ነፋስ ተመታለች። የምድብ ሦስት ደረጃ የተሰጠውና ሳማርን ያወደመው ይህ አውሎ ነፋስ በ2020 የምዕራብ ፓስፊክ ውቅያኖስን አካባቢ የመታ የመጀመሪያው አውሎ ነፋስ ሲሆን በሰዓት 185 ኪሎ ሜትር ይጓዝ ነበር። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል፤ መንግሥት ያወጣቸው የአካላዊ ርቀት ደንቦች ይህን ሂደት ይበልጥ ከባድ አድርገውታል።

ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን መካከል በአደጋው የተጎዳ ባይኖርም 59 የሚያህሉት መኖሪያቸውን ለቀው ለመሄድ ተገደዋል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች በትምህርት ቤቶች ወይም በእምነት ባልንጀሮቻቸው ቤቶች ውስጥ ተጠልለዋል። በተጨማሪም 82 የሚያህሉ የወንድሞች ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል ወይም ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። ከዚህም ሌላ አምስት የስብሰባ አዳራሾች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን አንድ አዳራሽ ሙሉ በሙሉ ወድሟል። የፊሊፒንስ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ ጉዳት የደረሰባቸውን ወንድሞችና እህቶች ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ሁለት የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን አቋቁሟል።

አውሎ ነፋሱና ወረርሽኙ ያስከተለባቸውን ድርብ መከራ እየተቋቋሙ ላሉ በፊሊፒንስ ያሉ ወንድሞቻችን መጸለያችንን እንቀጥላለን። እንዲሁም ‘የዘላለም ዓለታችን የሆነው ይሖዋ’ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እንደሚያሟላላቸው ሙሉ በሙሉ እንተማመናለን።—ኢሳይያስ 26:4