በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ

ፍቅርን መግለጽ የሚቻለው እንዴት ነው?

ፍቅርን መግለጽ የሚቻለው እንዴት ነው?

 አንዳንድ ባልና ሚስቶች ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የቀድሞውን ያህል አንዳቸው ለሌላው ፍቅራቸውን አይገልጹም። ይህ ሁኔታ በእናንተም ትዳር ውስጥ የሚታይ ከሆነ ጉዳዩ ሊያሳስባችሁ ይገባል?

 ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

 ፍቅር ለጠንካራ ትዳር በጣም አስፈላጊ ነው። ሰውነታችን ምንጊዜም ጠንካራና ጤነኛ እንዲሆን አዘውትረን ምግብ መብላትና ውኃ መጠጣት እንደሚኖርብን ሁሉ ትዳርም ጠንካራ እንዲሆን ባለትዳሮቹ አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር አዘውትረው መግለጽ ይኖርባቸዋል። በትዳር ብዙ አሥርተ ዓመታት ያሳለፉ ባለትዳሮችም እንኳ የትዳር ጓደኛቸው በጥልቅ እንደሚወዳቸውና እንደሚሳሳላቸው ዘወትር እንዲያረጋግጥላቸው ይፈልጋሉ።

 እውነተኛ ፍቅር ራስ ወዳድ አይደለም። እውነተኛ ፍቅር ያለው ሰው፣ የሚወደውን ግለሰብ ለማስደሰት ይጥራል። በመሆኑም አሳቢ የሆነ ባል ለሚስቱ ያለውን ፍቅር የሚገልጽላት እሱ ሲያሰኘው ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ሚስቱ ፍቅሩን እንዲገልጽላት እንደምትፈልግ በማስተዋል ይህን ለማድረግ ይጥራል።

 በጥቅሉ ሲታይ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች የትዳር ጓደኛቸው ፍቅሩን እንዲገልጽላቸው ይፈልጋሉ። አንድ ባል ሚስቱን በጥልቅ ይወዳት ይሆናል። ይሁን እንጂ ፍቅሩን የሚገልጽላት ጠዋት ወደ ሥራው ሲሄድና ማታ ሲመለስ አሊያም ደግሞ የፆታ ግንኙነት ሊፈጽሙ ሲሉ ብቻ ከሆነ ሚስቱ ከልቡ እንደሚወዳት እርግጠኛ ላትሆን ትችላለች። የተሻለ የሚሆነው በቀኑ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር መግለጻቸው ነው።

 ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

 ፍቅራችሁን በቃላት ግለጹ። “እወድሻለሁ” ወይም “በልቤ ውስጥ ልዩ ቦታ አለሽ” እንደሚሉት ያሉ የፍቅር መግለጫዎች አንዲት ሚስት ባሏ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጣት እንዲሰማት ያደርጋሉ።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነው።”—ማቴዎስ 12:34

 ጠቃሚ ምክር፦ ፍቅራችሁን የምትገልጹት በንግግራችሁ ብቻ መሆን እንዳለበት ሊሰማችሁ አይገባም። ለትዳር ጓደኛችሁ ማስታወሻ መጻፍ፣ ኢ-ሜይል ማድረግ አሊያም አጭር የጽሑፍ መልእክት መላክም ትችላላችሁ።

 ፍቅራችሁን በተግባር ግለጹ። የትዳር ጓደኛህን እቅፍ ማድረግ፣ መሳም ወይም እጇን መያዝ ብቻ እንኳ “እወድሻለሁ” የምትላት ከልብህ እንደሆነ እንዲሰማት ያደርጋል። ለትዳር ጓደኛችሁ ያላችሁን ፍቅር በመደባበስ፣ በፍቅር አየት በማድረግ ወይም አልፎ አልፎ ስጦታ በመስጠትም መግለጽ ትችላላችሁ። ሚስትህን ለመርዳት አንዳንድ ነገሮች ብታደርግ፣ ለምሳሌ የያዘችውን ዕቃ ብታግዛት፣ በር ከፍተህ ብትይዝላት፣ ዕቃ ወይም ልብስ ብታጥብላት አሊያም ምግብ ብትሠራላት ፍቅርህን በተግባር እየገለጽክ ነው። ብዙ ሚስቶች የትዳር ጓደኛቸው እነዚህን ነገሮች ሲያደርግላቸው፣ እያገዛቸው ብቻ ሳይሆን ፍቅሩን እየገለጸላቸውም እንደሆነ ይሰማቸዋል!

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ልጆቼ ሆይ፣ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።”—1 ዮሐንስ 3:18

 ጠቃሚ ምክር፦ ትጠናኑ በነበረበት ወቅት ታደርጉት እንደነበረው ለትዳር ጓደኛችሁ አሳቢነት አሳዩ።

 አንዳችሁ ለሌላው ጊዜ መድቡ። ሁለታችሁ ለብቻችሁ ሆናችሁ ጊዜ ማሳለፋችሁ ትዳራችሁን ያጠናክረዋል፤ ከዚህም ሌላ የትዳር ጓደኛችሁ ከእሱ ጋር መሆን እንደሚያስደስታችሁ እንዲሰማው ያደርጋል። እርግጥ ነው፣ ልጆች ካሏችሁ ወይም በየቀኑ የምትወያዩበት ብዙ አስፈላጊ ጉዳይ ካለ ለብቻችሁ የምትሆኑበት ጊዜ መመደብ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን ሁለታችሁ ብቻችሁን ሆናችሁ በእግር እንደ መንሸራሸር ያሉ ቀላል ነገሮችን አዘውትራችሁ ማድረግ ትችላላችሁ።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”—ፊልጵስዩስ 1:10

 ጠቃሚ ምክር፦ ሥራ የሚበዛባቸው አንዳንድ ባልና ሚስቶች፣ ሁለቱ ብቻ አንድ ላይ ሆነው ጊዜ የሚያሳልፉበት ቋሚ ፕሮግራም ያወጣሉ።

 የትዳር ጓደኛችሁ ምን እንደሚፈልግ እወቁ። የእያንዳንዱ ሰው ፍላጎት የተለያየ ነው። በመሆኑም የትዳር ጓደኛችሁ ፍቅሩን በምን መንገድ እንዲገልጽላችሁ እንደምትፈልጉ መነጋገራችሁ አስፈላጊ ነው፤ በዚህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋችሁ እንደሆነም መወያየታችሁ ጠቃሚ ነው። ከዚያም የትዳር ጓደኛችሁን ፍላጎት ለማሟላት ከልባችሁ ጥረት አድርጉ። ፍቅር ለጠንካራ ትዳር በጣም አስፈላጊ እንደሆነ አስታውሱ።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ፍቅር . . . የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም።”—1 ቆሮንቶስ 13:4, 5

 ጠቃሚ ምክር፦ የትዳር ጓደኛችሁ ፍቅሩን እንዲገልጽላችሁ ከመጠየቅ ይልቅ ‘የትዳር ጓደኛዬ ይበልጥ ፍቅሩን እንዲያሳየኝ እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ።