በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ኢያሱ 1:9—“ጽና፣ አይዞህ”

ኢያሱ 1:9—“ጽና፣ አይዞህ”

 “ደፋርና ብርቱ ሁን ብዬ አዝዤህ አልነበረም? አምላክህ ይሖዋ በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር ስለሆነ አትሸበር፤ አትፍራ።”—ኢያሱ 1:9 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “በምትሄድበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ጽና፣ አይዞህ፤ አትፍራ፣ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?”—ኢያሱ 1:9 የ1954 ትርጉም

የኢያሱ 1:9 ትርጉም

 ይሖዋ a አምላክ እነዚህን ቃላት የተናገረው ታማኝ አገልጋዩን ኢያሱን ለማበረታታት ነው፤ ተፈታታኝ ሁኔታዎችና የሚታለፉ የማይመስሉ እንቅፋቶች ቢያጋጥሙትም ‘ደፋርና ብርቱ በመሆን’ ሊጋፈጣቸው እንደሚችል አረጋግጦለታል። ኢያሱ የአምላክን ትእዛዛት እስከጠበቀ ድረስ ስለወደፊቱ ጊዜ የሚፈራበት ምንም ምክንያት አልነበረውም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ከእሱ ጋር ሆኖ እንዲሳካለት ይረዳዋል። አምላክ ለኢያሱ መመሪያዎችን በመስጠትና በጠላቶቹ ላይ ድል እንዲቀዳጅ በመርዳት አብሮት እንደሆነ አሳይቷል።

 ኢያሱን ‘ደፋርና ብርቱ እንዲሆን’ የሚረዳው ምንድን ነው? ይሖዋ በዚያን ወቅት በመንፈሱ መሪነት ያጻፋቸው ጽሑፎች የድፍረትና የብርታት ምንጭ ይሆኑት ነበር። ከእነዚህ ጽሑፎች መካከል ‘የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ ኢያሱን ያዘዘው ሕግ በሙሉ’ ይገኝበታል። b (ኢያሱ 1:7) ይሖዋ ሕጉን “ቀንም ሆነ ሌሊት በለሆሳስ አንብበው [“አሰላስልበት”]” በማለት ለኢያሱ ነግሮታል። (ኢያሱ 1:8 የግርጌ ማስታወሻ) ኢያሱ እንዲህ ባለ መንገድ ማንበቡና ማሰላሰሉ የአምላክን ሕግ ለመፈጸም ያለውን ቁርጠኝነት ያጠናክርለታል። በተጨማሪም ኢያሱ በአምላክ ቃል ላይ ‘የተጻፈውን በጥንቃቄ መፈጸም’ ማለትም የተማረውን ነገር ተግባር ላይ ማዋል ነበረበት። እንዲህ ካደረገ ማንኛውንም ነገር በጥበብ ማከናወንና ስኬታማ መሆን ይችላል። በኢያሱ ሕይወት ላይ የታየውም ይኸው ነው። ኢያሱ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ በመሆን አርኪና አስደሳች ሕይወት መርቷል።—ኢያሱ 23:14፤ 24:15

 ይሖዋ ለኢያሱ የተናገረው ሐሳብ እኛንም ያበረታታናል። ይሖዋ ለሁሉም፣ በተለይ ደግሞ ተፈታታኝ ሁኔታ ላጋጠማቸው አገልጋዮቹ ምን ያህል እንደሚያስብ ያሳያል። ይሖዋ እነዚህ አገልጋዮቹ ልክ እንደ ኢያሱ መንገዳቸው እንዲቃናላቸው ይፈልጋል! እነሱም ልክ ኢያሱ እንዳደረገው የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረው በማንበብና ባነበቡት ነገር ላይ በማሰላሰል እንዲሁም ከዚያ ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖር ‘ደፋርና ብርቱ መሆን’ ይችላሉ።

የኢያሱ 1:9 አውድ

 ሙሴ ከሞተ በኋላ ይሖዋ የእስራኤልን ብሔር እንዲመራ ኢያሱን ሾመው። (ኢያሱ 1:1, 2) በዚያ ወቅት እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ማለትም ወደ ከነአን ለመግባት እየተዘጋጁ ነበር። ሆኖም ኃያል የሆኑ ጠላቶቻቸውን መጋፈጥ ይጠበቅባቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢያሱ በክፋታቸው ይታወቁ ከነበሩት ከከነአናውያን ጋር መዋጋት ነበረበት። c (ዘዳግም 9:5፤ 20:17, 18) ከነአናውያኑ በቁጥር ከእስራኤላውያን ይበልጡ የነበረ ከመሆኑም ሌላ የተሻለ ወታደራዊ ኃይል ነበራቸው። (ኢያሱ 9:1, 2፤ 17:18) ኢያሱ ግን በድፍረት የይሖዋን መመሪያ ተከትሏል። ደግሞም አምላክ ከእሱ ጋር እንደሆነ አሳይቷል፤ ምክንያቱም እስራኤላውያን በስድስት ዓመት ውስጥ ብቻ በአብዛኞቹ ጠላቶቻቸው ላይ ድል ተቀዳጅተዋል።—ኢያሱ 21:43, 44

a ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም የዕብራይስጡ ስም የአማርኛ አጠራር ሲሆን ይህ ስም ቴትራግራማተን ተብለው በሚታወቁት አራት ፊደላት (יהוה [የሐወሐ]) ይወከላል። የ1954 ትርጉም እዚህ ጥቅስ ላይ ይህን ስም “እግዚአብሔር” በማለት ተርጉሞታል። ስለ ይሖዋና አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ስም ስላልተጠቀሙበት ምክንያት ለማወቅ “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

b በኢያሱ ዘመን የነበሩትና አሁን ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት በመንፈስ መሪነት የተጻፉት ጽሑፎች አምስቱን የሙሴን መጻሕፍት (ዘፍጥረት፣ ዘፀአት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኁልቁ እና ዘዳግም)፣ የኢዮብን መጽሐፍ እንዲሁም አንድ ወይም ሁለት መዝሙሮችን የሚያካትቱ ሳይሆኑ አይቀሩም።

c እንዲህ ያሉ ጦርነቶችን ማድረግ አስፈላጊ የነበረበትን ምክንያት ለማወቅ በጥር 1, 2010 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “አምላክ በከነዓናውያን ላይ ጦርነት ያወጀው ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።