በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ቁልፉ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ቁልፉ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የሚያስችለው ቁልፍ የሚገኘው ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። አስተዳደግህም ሆነ ሕይወትህ ምንም ይሁን ምን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የአምላክ መልእክት “ይህን ያህል አስቸጋሪ ወይም ከአንተ የራቀ” አይደለም።​—ዘዳግም 30:11

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የሚያስችሉ ቁልፎች

  1.   ትክክለኛ ዝንባሌ ይኑርህ። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ ተቀበል። አምላክ ትዕቢተኞችን ስለሚቃወም ትሑት ሁን። (1 ተሰሎንቄ 2:13፤ ያዕቆብ 4:6) ይሁን እንጂ ሁሉንም ነገር በጭፍን አትቀበል፤ ምክንያቱም አምላክ ‘የማሰብ ችሎታህን’ እንድትጠቀምበት ይፈልጋል።​—ሮም 12:1, 2

  2.   ጥበብ ለማግኘት ጸልይ። መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 3:5 ላይ “በራስህ ማስተዋል አትደገፍ” ይላል። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጥህ ‘አምላክን ያለማሰለስ ለምን።’​—ያዕቆብ 1:5

  3.   ቋሚ ፕሮግራም ይኑርህ። መጽሐፍ ቅዱስን አልፎ አልፎ ሳይሆን በቋሚነት የምታጠና ከሆነ ብዙ ጥቅም ታገኛለህ።​—ኢያሱ 1:8

  4.   በአንድ ጊዜ አንድ ርዕስ አጥና። መጽሐፍ ቅዱስን ርዕስ በርዕስ ማጥናትህ ማለትም ስለ አንድ ጉዳይ የሚናገረውን ነገር መመርመርህ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ለመረዳት የሚያስችል በጣም ጠቃሚ ዘዴ ነው። “ከመሠረታዊ ትምህርት” ጀምርና ቀስ በቀስ “ወደ ጉልምስና” የሚያደርሱ ከበድ ያሉ ትምህርቶችን አጥና። (ዕብራውያን 6:1, 2) ጥቅስን ከጥቅስ እያነጻጸርክ ካጠናህ “ለመረዳት የሚከብዱ” የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንኳ እርስ በርስ እንዴት እንደሚደጋገፉ ማየት ትችላለህ።​—2 ጴጥሮስ 3:16

  5.   ሌሎች እንዲረዱህ ጠይቅ። የቅዱሳን መጽሐፍት እውቀት ያላቸው ሰዎች እንዲረዱን መጠየቅ እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 8:30, 31) የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ያለምንም ክፍያ ያስተምራሉ። እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉ ሰዎች ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንዲያውቁ ለመርዳት በቅዱሳን መጻሕፍት ይጠቀማሉ።​—የሐዋርያት ሥራ 17:2, 3

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የማያስፈልጉ ነገሮች

  1.   የላቀ የማስተዋል ችሎታ ወይም ከፍተኛ ትምህርት። አንዳንዶች የኢየሱስ 12 ሐዋርያት ‘እንዳልተማሩና ተራ ሰዎች እንደሆኑ’ ቢሰማቸውም ሐዋርያቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ ከመረዳታቸውም በላይ ሌሎችን ያስተምሩ ነበር።​—የሐዋርያት ሥራ 4:13

  2.   ገንዘብ። መጽሐፍ ቅዱስን ያለክፍያ መማር ትችላለህ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ” ብሏቸዋል።​—ማቴዎስ 10:8