በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥማትም በጽናት ቀጥላለች

አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥማትም በጽናት ቀጥላለች

 የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ቨርጂኒያ ሎክድ ኢን ሲንድሮም በተባለ በሽታ ትሠቃያለች። ሰውነቷ በሙሉ ሽባ ነው። ማየትና መስማት፣ ዓይኗን መግለጥና መጨፈን እንዲሁም ጭንቅላቷን በትንሹ ማንቀሳቀስ ትችላለች። መናገርም ሆነ መብላት አትችልም። በአንድ ወቅት ጤናማና ጠንካራ ነበረች። ሆኖም አንድ ቀን ጠዋት (በ1997) ጭንቅላቷ ላይ ከኋላ በኩል ኃይለኛና የማያቋርጥ ሕመም ተሰማት። ባለቤቷ ወደ ሆስፒታል ይዟት የሄደ ሲሆን ያን ምሽት ራሷን ሳተች። ከሁለት ሳምንት በኋላ ስትነቃ ራሷን ያገኘችው ልዩ የሕክምና ክትትል በሚደረግበት ክፍል ውስጥ ነው። ሰውነቷን ማንቀሳቀስ የማትችል ከመሆኑም ሌላ የመተንፈሻ መሣሪያ ተገጥሞላት ነበር። ለተወሰኑ ቀናት ምንም ነገር ማስታወስ ሌላው ቀርቶ ማንነቷን እንኳ ማወቅ አልቻለችም።

 ቨርጂኒያ ቀጥሎ የሆነውን ነገር ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ቀስ በቀስ አንዳንድ ነገሮችን ማስታወስ ጀመርኩ። አጥብቄ ጸለይኩ። ትንሹን ልጄን ያለእናት ትቼ መሞት አልፈለግኩም። ድፍረት ለማግኘት እንዲረዳኝ፣ የቻልኩትን ያህል ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ለማስታወስ ጥረት አደረግኩ።

 “ከጊዜ በኋላ ሐኪሞቹ ልዩ የሕክምና ክትትል ከሚደረግበት ክፍል እንድወጣ ወሰኑ። በተለያዩ ሆስፒታሎችና ማገገሚያ ማዕከል ውስጥ ስድስት ወራት ካሳለፍኩ በኋላ ወደ ቤት ተመለስኩ። ሰውነቴ ሙሉ በሙሉ ሽባ ስለሆነ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ የሌሎች እርዳታ ያስፈልገኛል። በጣም ተስፋ ቆረጥኩ! ለሌሎችም ሆነ ለይሖዋ ምንም እንደማልጠቅም ተሰማኝ። ልጄን መንከባከብ አለመቻሌም በጣም አስጨነቀኝ።

 “እንደኔ ዓይነት ሁኔታ ስላጋጠማቸው ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች የሚገልጹ ተሞክሮዎችን ማንበብ ጀመርኩ፤ እነዚህ ወንድሞችና እህቶች በይሖዋ አገልግሎት ማከናወን ስለቻሉት ነገር ሳነብ በጣም ተገረምኩ። በመሆኑም ማድረግ በምችለው ነገር ላይ በማተኮር አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ጥረት አደረግኩ። ከመታመሜ በፊት በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ያለኝ ጊዜ ውስን ነበር። አሁን ግን በየዕለቱ፣ ሙሉ ቀን ለዚህ የሚሆን ጊዜ አለኝ። ስለዚህ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ይሖዋን ማገልገል በምችልበት መንገድ ላይ ትኩረት አደረግኩ።

 “ስለ ኮምፒውተር አጠቃቀም ተማርኩ። የጭንቅላቴን እንቅስቃሴ በሚያነብ የኮምፒውተር ፕሮግራም ተጠቅሜ እጽፋለሁ። ይህ አድካሚ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንዲሁም ተስፋዬን በደብዳቤና በኢ-ሜይል አማካኝነት ለሌሎች ለማካፈል ያስችለኛል። በዙሪያዬ ካሉ ሰዎች ጋር ለመነጋገር የፊደላት ዝርዝር የያዘ ሰሌዳ እጠቀማለሁ። የማነጋግረው ሰው አንድ በአንድ ፊደላቱን ይጠቁመኛል። ትክክል ያልሆነውን ፊደል ከመረጠ ዓይኔን በደንብ እገልጣለሁ፤ ትክክል የሆነውን ፊደል ከመረጠ ደግሞ ዓይኔን እጨፍናለሁ። ይህንኑ ሂደት በመደጋገም ቃላትንና ዓረፍተ ነገሮችን ለመሥራት እንሞክራለን። አብረውኝ ብዙ ጊዜ የሚያሳልፉ አንዳንድ እህቶች፣ ማለት የፈለግኩትን ነገር በመገመት ረገድ ተክነዋል። አንዳንድ ጊዜ የተሳሳተ ቃል ሲገምቱ አብረን እንስቃለን።

የፊደል ዝርዝር በያዘ ሰሌዳ አማካኝነት ከሌሎች ጋር ለመነጋገር ጥረት ስታደርግ

 “በጉባኤ እንቅስቃሴዎች መካፈል ያስደስተኛል። በኢንተርኔት አማካኝነት ሁሌም ስብሰባዎችን እከታተላለሁ፤ አሁን እንዲህ የማደርገው በቪዲዮ ኮንፈረንስ ነው። በጥያቄና መልስ በሚሸፈኑት ክፍሎች ላይ ሐሳብ መስጠት ስፈልግ እጽፈውና ሌላ ሰው እንዲያነብልኝ አደርጋለሁ። በተጨማሪም በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ከተወሰኑ ወንድሞችና እህቶች ጋር አብሬ የ​JW ብሮድካስቲንግ ወርሃዊ ፕሮግራሞችን እመለከታለሁ። a

 “ይህ በሽታ ከያዘኝ አሁን 23 ዓመት ሆኖኛል። አንዳንዴ ሐዘን ይሰማኛል። ሆኖም ወደ ይሖዋ መጸለዬ፣ ከወንድሞች ጋር ጊዜ ማሳለፌና በመንፈሳዊ ንቁ ሆኜ መቀጠሌ አልፎ አልፎ የሚሰማኝን ይህን ስሜት ለማሸነፍ ረድቶኛል። እንዲያውም በጉባኤው እርዳታ ያለፉትን ስድስት ዓመታት ረዳት አቅኚ መሆን ችያለሁ። ለልጄ ለአሌሳንድሮ ጥሩ ምሳሌ ለመሆን ጥረት አድርጌያለሁ፤ አሁን ትዳር የመሠረተ ሲሆን የጉባኤ ሽማግሌ ነው። ከሚስቱ ጋር በዘወትር አቅኚነት ያገለግላል።

 “ወደፊት ገነት ውስጥ ማድረግ በምችላቸው ነገሮች ላይ ብዙ ጊዜ አሰላስላለሁ። መጀመሪያ ማድረግ የምፈልገው በራሴ ድምፅ ስለ ይሖዋ ለሌሎች መናገር ነው። ወደ ገጠራማ አካባቢ ሄጄ ወንዝ ዳር በእግሬ እየተጓዝኩ ውብ የሆነውን ተፈጥሮ ማድነቅ እፈልጋለሁ። ላለፉት 20 ዓመታት በቱቦ የሚሰጥ ፈሳሽ ብቻ ስመገብ ስለኖርኩ ከዛፍ ላይ ፖም ቀጥፌ ለመግመጥ እጓጓለሁ። ጣሊያናዊ እንደመሆኔ መጠን ደግሞ ፒዛን ጨምሮ የምወዳቸውን የጣሊያን ምግቦች እየሠራሁ የምመገብበት ጊዜ ይናፍቀኛል!

 “‘የመዳን ተስፋ’ አስተሳሰቤን ለመጠበቅ ረድቶኛል። (1 ተሰሎንቄ 5:8) አካላዊ እክል ቢኖርብኝም አዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖረኝን ሕይወት በዓይነ ሕሊናዬ መሣሌ ደስተኛ እንድሆን ያደርገኛል፤ በቅርቡ ያለብኝ ችግር ሁሉ እንደሚወገድ እርግጠኛ ነኝ። ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት እንደሚሰጠን ቃል የገባውን ‘እውነተኛ የሆነ ሕይወት’ ለማግኘት ከልብ እጓጓለሁ።”—1 ጢሞቴዎስ 6:19፤ ማቴዎስ 6:9, 10

a ወደ JW ብሮድካስቲንግ የሚወስድ ሊንክ jw.org ላይ ማግኘት ይቻላል።