በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከእሳት ጋር የሚደረገውን ውጊያ ማሸነፍ

ከእሳት ጋር የሚደረገውን ውጊያ ማሸነፍ

“እሳት! እሳት!” በአማቶቿ ቤት ቁርስ እየበላች የነበረችው ዛንድራ ከቤቱ አጠገብ ካለው የዕቃ ማስቀመጫ ክፍል በር ሥር ጭስ እየተትጎለጎለ ሲወጣ አየች። እሷና ባለቤቷ ቶማስ ቶሎ ብለው እርምጃ ወሰዱ። ዛንድራ የእሳት ማጥፊያውን ልታመጣ ስትሄድ ቶማስ ደግሞ ሁኔታውን ለማጣራት ወደ ዕቃ ማስቀመጫ ክፍሉ እየሮጠ ሄደ። ዛንድራ በፍጥነት ለቶማስ የእሳት ማጥፊያውን ሰጠችው፤ ከዚያም ቶማስ እሳቱን አጠፋው። ዛንድራ እንዲህ ብላለች፦ “ቶሎ እርምጃ ባንወስድ ኖሮ የዕቃ ማስቀመጫ ክፍሉ ሙሉ በሙሉ ይቃጠል ነበር።”

ቶማስና ዛንድራ በሁኔታው ሳይደናገጡ ቶሎ እርምጃ መውሰድ የቻሉት ለምንድን ነው? ቶማስንና ዛንድራን ጨምሮ በሴልተርስ፣ ጀርመን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚሠሩ 1,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች እሳት በሚነሳበት ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሥልጠና ወስደዋል።

በሴልተርስ በሚገኘው 30 ሄክታር የሚያክል መሬት ላይ ቢሮዎችና መኖሪያ ክፍሎች ብቻ ሳይሆኑ የልብስ ንጽሕና መስጫ ክፍል፣ ማተሚያ ክፍል እንዲሁም የተለያዩ ወርክሾፖች አሉ፤ በእነዚህ ቦታዎች እሳት የመነሳቱ አጋጣሚ በጣም ሰፊ ነው። በመሆኑም የቅርንጫፍ ቢሮው የደህንነትና የአካባቢ ዲፓርትመንት ከእሳት አደጋ ጋር የተያያዘ ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችል ፕሮግራም አዘጋጀ። በመጀመሪያ “የድንገተኛ አደጋ ቡድን” ተብሎ የሚጠራ ቡድን ከአካባቢው የእሳት አደጋ ሠራተኞች ጋር ሆኖ ልምምድ ያደርጋል። ቀጥሎም በቅርንጫፍ ቢሮው የሚሠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች በሙሉ የሚከተሉትን ነገሮች ይለማመዳሉ፦

  • እሳት አደጋ ሲነሳ ሕንፃውን ለቅቀው መውጣት የሚችሉበትን መንገድ

  • ለእሳት አደጋ በማያጋልጥ ሁኔታ መሥራት የሚችሉበትን መንገድ እንዲሁም

  • እሳት አደጋ ሲከሰት ወዲያውኑ ማጥፋት የሚችሉበትን መንገድ

በዚህ መንገድ በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ የሚሠሩት ፈቃደኛ ሠራተኞች አደጋ ሲከሰት በጣም የሚጠቅማቸውን ችሎታ ያዳብራሉ።

ጉዳት በማያስከትል መንገድ እሳትን ማጥፋት

ሥልጠናውን የሚወስዱት ሰዎች ጉዳት በማያስከትል መንገድ እሳት ማጥፋት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ይማራሉ። ክሪስቲን እሳት አደጋን መከላከል የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለመጨረሻ ጊዜ የተማረችው የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለች ነበር፤ ክሪስቲን በቅርንጫፍ ቢሮው የሚሰጠውን ሥልጠና ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “የእሳት ማጥፊያውን አንስቼ ከከፈትኩት በኋላ ነፋስ በሚነሳበት አቅጣጫ በኩል ወደ እሳቱ ተጠጋሁ። እንዲህ ባላደርግ ኖሮ ወላፈኑ ወደ እኔ ይመጣ ነበር። ከዚያም ለብቻዬ እሳቱን አጠፋሁት! አራት ወይም አምስት ሆኖ በቡድን እሳት ማጥፋት የሚቻለው እንዴት እንደሆነም ተምሬያለሁ።”

ቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ የእሳት አደጋ መከላከያ አሠልጣኝ የሆነው ዳንዬል የልምምድ ፕሮግራሙ ሰዎች ለእሳት ያላቸውን ፍርሃት እንደሚቀንስ ተናግሯል። ዳንዬል ጉዳዩን ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “አብዛኞቹ ሰዎች እሳት ሲነሳ በጣም ይደነግጣሉ። ‘ምን ብናደርግ ይሻላል? የእሳት ማጥፊያውን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?’ ብለው ግራ ይጋባሉ። ምን ማድረግ እንዳለባቸው ካወቁ ግን የተነሳው እሳት ከመባባሱ በፊት በቀላሉ እርምጃ መውሰድ ይችላሉ።” ዳንዬል ልምምዱ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝ ሲናገር “ሰዎቹ እሳት አደጋ ሲከሰት የእሳት ማጥፊያውን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸውና እሳቱን እንዴት ማጥፋት እንደሚችሉ ይማራሉ። ልምምዱ በራስ የመተማመን ስሜታቸውን ስለሚያሳድግላቸው አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ድፍረት ያገኛሉ።”

ሥልጠና ጥሩ ውጤት ያስገኛል

አብዛኞቹ ሠልጣኞች ሥልጠናውን በማግኘታቸው እንደተጠቀሙ ገልጸዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ክሪስቲን እንዲህ ብላለች፦ “በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ የእሳት ማጥፊያ የያዝኩት በልምምዱ ወቅት ነው። ሁሉም ሰው እንዲህ ያለውን ሥልጠና ቢያገኝ ጥሩ ይመስለኛል።” አየር ማረፊያ ውስጥ የምትሠራውና በሳምንት ለተወሰኑ ቀናት ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው እየመጣች የፈቃደኝነት አገልግሎት የምትሰጠው ናድያ እንዲህ ብላለች፦ “ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በአየር ማረፊያው ያገኘሁት የእሳት አደጋ መከላከል ትምህርት በተግባር የተደገፈ አልነበረም። በቅርንጫፍ ቢሮው ያገኘሁት ተግባራዊ ሥልጠና ግን በራስ የመተማመን ስሜቴን አሳድጎልኛል። አሁን እሳት ቢነሳ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አውቃለሁ።”

ዛንድራ በአማቾቿ ቤት እሳት አደጋ ሲከሰት በፍጥነት እርምጃ ለመውሰድ ያስቻላት በቅርንጫፍ ቢሮው ያገኘችው ሥልጠና እንደሆነ ይሰማታል። እንዲህ ብላለች፦ “የእሳት ማጥፊያውን መጠቀም እንደ ቀድሞው አያስፈራኝም። በየዓመቱ የሚሰጠን ሥልጠና ጠቅሞናል። በጣም እንደረዳኝ ይሰማኛል።”

ከአካባቢው የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍል ጋር ልምምድ ማድረግ

የአካባቢው የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍል በቅርንጫፍ ቢሮው ግቢ ውስጥ በየተወሰነ ጊዜው የልምምድ ፕሮግራም ያዘጋጃል። የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኛ የሆነው ቲዮ ነከማን ይህን የሚያደርጉት ለምን እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍላችን የሚሠራው ገጠራማ አካባቢ በሆነው በሴልተርስ ነው። በአብዛኛው የሚያጋጥመን በቤት ወይም በአፓርታማ ውስጥ የሚነሳ የእሳት አደጋ ነው። ቅርንጫፍ ቢሮው ግን ሰፊ ቦታ የሚሸፍን፣ ትላልቅ ሕንፃዎች ያሉትና የፋብሪካ ዓይነት ሥራ የሚሠራበት ቦታ ስለሆነ በአካባቢው ካሉት ሁሉ የተለየ ነው። እዚህ ቦታ ላይ እሳት ቢነሳ እርምጃ መውሰድ እንድንችል ተጨማሪ ሥልጠና ማግኘት ያስፈልገናል። በመሆኑም ቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ ልምምድ ማድረግ በመቻላችን ደስተኞች ነን።”

ከመቶ በላይ የሚሆኑት የቅርንጫፍ ቢሮው የድንገተኛ አደጋ ቡድን አባላት ከአካባቢው የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍል ጋር ሆነው እሳት አደጋ ቢነሳ ሕይወት ማዳንና ሕንፃውን ለቅቆ መውጣት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ይለማመዳሉ። ቲዮ ነከማን እንዲህ ብሏል፦ “የድንገተኛ አደጋ ቡድናችሁን በጣም እናደንቃለን። የእነሱ እርዳታና አመራር ባይኖር ኖሮ የእሳት አደጋ ልምምዱ በተሳካ ሁኔታ መካሄድ አይችልም ነበር።”

አንድ ሰው እየነደደ ያለን ዘይት በውኃ ለማጥፋት መሞከር ያለውን አደጋ በሠርቶ ማሳያ መልክ ሲያሳይ

የካቲት 2014 አንድ ምሽት፣ የአካባቢው የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍልና የቅርንጫፍ ቢሮው የድንገተኛ አደጋ ቡድን ያገኙትን ሥልጠና ተግባራዊ የሚያደርጉበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። ከቅርንጫፍ ቢሮው የመኖሪያ ሕንፃዎች አንዱ በጭስ ተሞላ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዳንዬል እንዲህ ብሏል፦ “ጭሱ በጣም ጥቅጥቅ ያለ ከመሆኑ የተነሳ ፊት ለፊታችን ያለውን ነገር እንኳ ማየት አንችልም ነበር። ወዲያውኑ ወደ እሳት አደጋ መከላከያ ክፍሉ ደወልን፤ ከዚያም በሰማንያ ስምንቱም መኖሪያ ክፍሎች ውስጥ ያሉትን ሰዎች ማስወጣት ጀመርን። የእሳት አደጋ ሠራተኞቹ ሲደርሱ በሕንፃው ውስጥ የነበሩት ሰዎች በሙሉ ወጥተው ነበር።” ቲዮ ነከማን እንዲህ ብሏል፦ “እንደ ፍራንክፈርት ባለ ከተማ ውስጥ እንኳ እንዲህ ባለ ትልቅ ሕንፃ ውስጥ ያሉ ሰዎችን በሙሉ በዚህ ፍጥነት ማስወጣት የሚቻል አይመስለኝም። ሁላችሁም መመሪያ አክባሪ ናችሁ፤ የድንገተኛ አደጋ ቡድኑም በጣም አስደናቂ ነው!” የእሳት አደጋ ሠራተኞቹ የጭሱን መንስኤ አግኝተው ችግሩን አስወገዱ። ጉዳት የደረሰበት አንድም ሰው አልነበረም፤ በንብረትም ላይ ቢሆን ከባድ ጉዳት አልደረሰም።

በሴልተርስ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ የሚሠሩ ሰዎች በሙሉ ከባድ የእሳት አደጋ መቼም ቢሆን ባይከሰት ደስ ይላቸዋል። አደጋ ቢከሰት ግን ከእሳት ጋር የሚደረገውን ውጊያ ማሸነፍ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ስለተማሩ እሳቱን ለማጥፋት ዝግጁ ናቸው።