በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

“ሴቶች በግንባታ ሥራ ላይ ቦታ አላቸው”

“ሴቶች በግንባታ ሥራ ላይ ቦታ አላቸው”

በብሪታንያ የሚገኝ አንድ ታዋቂ የግንባታ ሥራ ድርጅት የይሖዋ ምሥክሮች በቼልምስፎርድ፣ ኤሴክስ በሚሠሩት አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ላይ ሴቶች በከባድ ማሽኖች ላይ እንዲሠሩ ለሚሰጡት ሥልጠና ያለውን አድናቆት ገልጿል። ኮንሲደሬት ኮንስትራክተርስ ስኪም a (ሲ ሲ ኤስ) የተባለው ድርጅት የይሖዋ ምሥክሮች ለሴቶች የግንባታ ሥልጠና ለመስጠት የሚጠቀሙበት ዘዴ “አዲስ” እንደሆነ የገለጸ ሲሆን ለዚህ የሥልጠና ዘዴያቸው ከፍተኛ ነጥብ ማለትም 10 ከ10 ሰጥቷቸዋል። ድርጅቱ ለይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያለ ከፍተኛ ነጥብ የሰጠው ለምንድን ነው?

ብሪታንያ ውስጥ ካሉት የግንባታ ሠራተኞች መካከል የሴቶች ቁጥር ከ13 በመቶ ያነሰ ነው። አንድ የብሪታንያ ድርጅት ያካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው በግንባታው መስክ ለመሰማራት የሚያስቡ ወጣት ሴቶች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው። ከዚህ በተቃራኒ ግን በቼልምስፎርድ የግንባታ ቦታ ከሚሠሩት ሰዎች መካከል 40 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ከባድ ማሽኖች ላይ ከሚሠሩት ሰዎች መካከል ደግሞ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።

ሴቶች በቼልምስፎርድ የግንባታ ቦታ ከወንዶች ጋር ሲሠሩ

የይሖዋ ምሥክር የሆኑት እነዚህ ሴቶች በሥራቸው ስኬታማ እንዲሆኑ የረዳቸው ምንድን ነው? የሚሰጣቸው ሥልጠና እንዲሁም የሚያገኙት ድጋፍ ለዚህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። እነዚህ ሁለት ነገሮች ደግሞ የሲሲኤስ አባላት እንዲያሟሉ ከሚጠበቅባቸው መሥፈርቶች መካከል ይገኙበታል። የሲሲኤስ መመሪያ፣ አሠሪዎች “ሁሉንም ሰው በአክብሮትና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በመያዝ፣ ማበረታቻና ድጋፍ በመስጠት” እንዲሁም “ጥሩ ሥልጠና በመስጠት” ለሠራተኞቻቸው ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡ እንዲያሳዩ ያበረታታል።

ሴቶች ከባድ ማሽኖች ላይ እንዲሠሩ ማሠልጠን

በግንባታ ቦታው ላይ ኤክስካቫተርና የጭነት መኪና ላይ ለመሥራት ሥልጠና ያገኘች ጄድ የምትባል ሴት እንዲህ ብላለች፦ “በጣም ይገርማል! እንዲህ ያለ ሥራ መሥራት እችላለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። ሥራው አንዳንድ ጊዜ ይከብዳል፤ ግን ሁልጊዜም ሥልጠና አገኛለሁ እንዲሁም አዲስ ነገሮች እማራለሁ።” እንደ ጄድ ሁሉ ከባድ ማሽኖች ላይ የምትሠራው ሉሲም እንዲህ ትላለች፦ “ወደ ግንባታ ቦታው ስመጣ ምንም ዓይነት ሙያ ስላልነበረኝ ምንም አስተዋጽኦ ማበርከት እንደማልችል ተሰምቶኝ ነበር። ሆኖም ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ ሥልጠና አግኝቻለሁ። እስካሁን ከአምስት የተለያዩ ቡድኖች ጋር ሠርቻለሁ፤ ስለዚህ የተለያየ ሥልጠና አግኝቻለሁ።”

ቴሌሃንድለር ለተባለው ማሽን የአጠቃቀም ሥልጠና ሲሰጥ

እነዚህ ሴቶች ያላቸው ችሎታ ማሽኖችን በማንቀሳቀስ ብቻ አይወሰንም። ኤሪክ የተባለ የአንድ ቡድን ኃላፊ እንዲህ ብሏል፦ “ከወንዶች የበለጠ ማሽኑን ጥሩ አድርገው የሚይዙት ሴቶች ናቸው። ማሽናቸው የሆነ ችግር ካለበት ደግሞ ቶሎ ይህን አስተውለው ችግሩን ያሳውቃሉ።”

በግንባታ ሥራ የሚካፈሉት ሴቶች የሚደረግላቸው ድጋፍ

ከከባድ ማሽኖች ጋር የተያያዘ ሥራ የሚሠሩ በርካታ ቡድኖች ኃላፊ የሆነው ካርል እንዲህ ብሏል፦ “ሴቶቹ ሥልጠና አግኝተው ማሽኖቹን የሚያንቀሳቅሱበት መንገድ በጣም አስደንቆኛል። እንዲያውም የብዙ ዓመት ልምድ ያላቸው ወንዶች እያሉ እነዚህ ሴቶች ማሽኖቹ ላይ እንዲሠሩ የምመርጥበት ጊዜ አለ።”

የፕላስቲክ ቱቦዎችን የሚያገናኝ ማሽን ላይ መሥራት

የሥራ ኃላፊዎች ለሥራ ባልደረቦቻቸው የሚሰጡት ድጋፍ ሠራተኞቹ በራስ የመተማመን ስሜት እንድያድርባቸው ያደርጋል። ተሪስ የተባለች ሴት ይህ እውነት መሆኑን ትመሠክራለች። ተሪስ በከባድ ማሽኖች ላይ ለረጅም ጊዜ ሠርታለች፤ በመሆኑም ከባድ ማሽኖች ላይ መሥራት ከባድ ኃላፊነት መሸከምና ምንም ዓይነት አደጋ እንዳይከሰት አንዳንድ ውሳኔዎችን ማድረግ እንደሚጠይቅ ታውቃለች። ተሪስ እንዲህ ትላለች፦ “የሥራ ኃላፊዬ እንደሚደግፈኝ ማወቄ እምነት የሚጣልበት ሰው እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ ሌላ ጊዜ ከማደርገው የበለጠ እንድሠራ ያስችለኛል። ሰዎች የማደርገውን አስተዋጽኦ እንደሚመለከቱና እንደሚያደንቁት ሳይ ልፋቴ መና እንዳልቀረ ይሰማኛል።”

በኤክስካቫተርና የጭነት መኪና ላይ የምትሠራ አቢጋኤል የተባለች ሴት ደግሞ አብረዋት የሚሠሩት ሰዎች ስለሚያደርጉላት ድጋፍና ትብብር ያላትን አድናቆት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “እዚህ የሚሠሩት ወንዶች ከእነሱ እንደማንስ አድርገው አይመለከቱኝም። እርዳታ ሲያስፈልገኝ ሊረዱኝ ፈቃደኞች ናቸው፤ እኔን አስቁመው ሥራውን ራሳቸው ለመቀጠል አይሞክሩም። ከዚህ ይልቅ ሥራውን ራሴ እንድጨርስ ያደርጋሉ።”

ታታሪና ጠንቃቃ ሠራተኞች

በቼልምስፎርድ የግንባታ ቦታ የሚሠሩት ሴቶች የተለያዩ ከባድ ማሽኖች ላይ ከመሥራት በተጨማሪ በቅየሳ ሥራ፣ በመሬት አጠቃቀም፣ በማሽን ጥገናና መወጣጫዎችን በመገጣጠም ሥራ መስክ ሥልጠና አግኝተዋል። ከሴቶች ጋር በተለያዩ ፕሮጀክቶች የሠራው ሮበርት፣ ሴቶች “የሥራ ተነሳሽነት ያላቸውና ለእያንዳንዱ ነገር ትኩረት የሚሰጡ” እንደሆኑ ተናግሯል። የቅየሳ ሥራ የሚሠራው ቶም ደግሞ “በእኔ ቡድን ውስጥ ያሉት ሴቶች በጣም ጠንቃቃና ሁሉን ነገር በትክክል የሚሠሩ ናቸው። ትንሽ እንኳ ዝንፍ እንዲል አይፈልጉም።”

ከዚህ አንጻር፣ የሥራ ኃላፊ የሆነው ፈርገስ “በእርግጥም ሴቶች በግንባታ ሥራ ላይ ቦታ አላቸው!” ብሎ መናገሩ አያስገርምም።

a ኮንሲደሬት ኮንስትራክተርስ ስኪም የተባለው ድርጅት ብሪታንያ ውስጥ የግንባታው ዘርፍ ያለውን ገጽታ ለማሻሻል የሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው።