በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የብሪታንያ ፎቶ ጋለሪ 1 (ከጥር እስከ ነሐሴ 2015)

የብሪታንያ ፎቶ ጋለሪ 1 (ከጥር እስከ ነሐሴ 2015)

በብሪታንያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በሚል ሂል፣ ለንደን ያለውን ቅርንጫፍ ቢሯቸውን ለቀው በስተ ምሥራቅ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኝ ቦታ (ቼልምስፎርድ፣ ኤሴክስ ከተማ አቅራቢያ) ሊዛወሩ ነው። ሠራተኞች ከጥር እስከ ነሐሴ 2015 ባለው ጊዜ ውስጥ፣ ግንባታው ሲጀመር ለግንባታ ሥራው ድጋፍ ለመስጠት የሚያገለግሉ ጣቢያዎችን ገንብተዋል።

ጥር 23, 2015—የቅርንጫፍ ቢሮው የግንባታ ቦታ

የአካባቢውን ባለሥልጣናት ፈቃድ በመጠየቅ ሠራተኞች የወደቁ ዛፎችን እያነሱ ነው፤ ይህም አካባቢው ወደፊት ለሚደረገው ግንባታ ምቹ እንዲሆን ያደርጋል። ሠራተኞቹ ወፎች ጎጇቸውን የሚሠሩበት ወቅት ከመድረሱ በፊት ይህን ሥራ ለመጨረስ ጥረት አድርገዋል። ከእነዚህ ዛፎች የሚገኘው ሰጋቱራ የእግረኛ መንገዶችን ለመሥራት የሚያገለግል ሲሆን እንጨቶቹ ደግሞ ወደፊት ለግንባታ ስለሚውሉ ተሰብስበው ይቀመጣሉ።

ጥር 30, 2015—የመመገቢያ ቦታ

አንድ የኤሌክትሪክ ሠራተኛ ለስክሪኖቹ የሚሆን ሶኬት እየገጠመ ነው። ከዚህ ቀደም ሞቴል የነበረው ይህ ሕንፃ ኩሽናና የመመገቢያ አዳራሽ ሆኖ ያገለግላል። ስክሪኖቹ የግንባታ ሠራተኞች እንደ ማለዳ አምልኮና የቤቴል ቤተሰብ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ያሉ መንፈሳዊ ፕሮግራሞችን እንዲከታተሉ ያስችሏቸዋል።

የካቲት 23, 2015—የቅርንጫፍ ቢሮው የግንባታ ቦታ

ሠራተኞች በግንባታ ቦታው አካባቢ አጥር እያጠሩ ነው፤ ወደፊት አብዛኛው የግንባታ አካባቢ ይታጠራል። አካባቢው ገጠራማ ስለሆነ ግንባታው በዱር እንስሳት ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቀነስ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው። ለምሳሌ አጥሩ ከሥር 20 ሴንቲ ሜትር ያህል ክፍተት እንዲኖረው ተደርጓል፤ ይህም ምግባቸውን ሌሊት የሚፈልጉ እንስሳት የተለመደውን እንቅስቃሴያቸውን እንዲያከናውኑ ያስችላቸዋል።

የካቲት 23, 2015—የቅርንጫፍ ቢሮው የግንባታ ቦታ

የመኖሪያ አካባቢውን ከግንባታ አካባቢው ጋር ለማገናኘት የሚያስችል ጊዜያዊ መንገድ እየተሠራ ነው።

መጋቢት 5, 2015—የቅርንጫፍ ቢሮው የግንባታ ቦታ

የተጠናቀቀው ጊዜያዊ መንገድ ከምሥራቅ በኩል ሲታይ። በስተ ቀኝ ከላይ በኩል እንደሚታየው መንገዱ ወደ ዋናው የግንባታ አካባቢ ይወስዳል። በስተ ግራ በታች በኩል የሚታዩት ሕንፃዎች የግንባታ ሠራተኞች መኖሪያ ሆነው እንዲያገለግሉ ለማድረግ አንዳንድ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ከጎን ባለው ሜዳ ላይ የመኖሪያ ቤቶች ይሠራሉ።

ሚያዝያ 20, 2015—የመኖሪያ አካባቢ

አንድ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባልና የዋናው መሥሪያ ቤት ተወካይ የግንባታ ቡድኑን ጎብኝተው ነበር። በዚያው ሳምንት የተደረገው ልዩ ስብሰባ በብሪታንያና በአየርላንድ ወደሚገኙ የመንግሥት አዳራሾች በሙሉ ተላልፎ ነበር። በስብሰባው ላይ፣ ከዚያ በፊት በነበረው ምሽት የቼልምስፎርድ ከተማ ምክር ቤት ለግንባታ ፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ፈቃድ እንደሰጠ የሚገልጽ ማስታወቂያ ተነገረ።

ግንቦት 13, 2015—ዋና ጣቢያ

ሠራተኞች በሁለት ትላልቅ ዛፎች መካከል፣ የዛፎቹን ሥሮች ከጉዳት ለመከላከል የሚረዱ መሣሪያዎች እየገጠሙ ነው። ይህ መተላለፊያ ዋናውን ጣቢያ ግንባታ ከሚካሄድበት አካባቢ ጋር የሚያገናኝ ሲሆን በዚያ በኩል ተጭነው የሚያልፉት መሣሪያዎች ክብደት የዛፎቹን ሥር እንዳይጎዳ ይከላከላል።

ግንቦት 21, 2015—የመኖሪያ አካባቢ

የመሠረት ግንባታ የሚያከናውኑት ሠራተኞች ለጊዜያዊ የመኖሪያ ቦታው እንደ ውኃና ኤሌክትሪክ ያሉ አገልግሎቶች የሚያልፉባቸውን መስመሮች ለመዘርጋት የሚያገለግሉ ቦዮች እየቆፈሩ ነው። ከጀርባ የሚታዩት ለግንባታ ሠራተኞቹ የተሠሩት የመጀመሪያዎቹ 50 ቤቶች ናቸው።

ሰኔ 16, 2015—የመኖሪያ አካባቢ

አንድ የቧንቧ ሠራተኛ ለጊዜያዊ የመኖሪያ ቤቶቹ የውኃ መስመር እየዘረጋ ነው።

ሰኔ 16, 2015—የመኖሪያ አካባቢ

አዲስ የተሠሩት ጊዜያዊ የመኖሪያ ቤቶች ከቀኝ በኩል ሲታዩ። ከፊት ለፊት በሚታዩት ቦታዎች ላይ ተጨማሪ መኖሪያ ቤቶችን ለመሥራት መሠረት እየተጣለ ነው። በስተ ግራ የሚታዩት ሕንፃዎች የግንባታ ሠራተኞች የመመገቢያ አዳራሽና መኖሪያ ቤቶች ናቸው። ቅርንጫፍ ቢሮው የሚገነባው ከበስተ ጀርባ ባለው አካባቢ መሃል ላይ ነው።

ሰኔ 16, 2015—የመኖሪያ አካባቢ

አንዲት የቴክኒክ ባለሙያ በቴሌኮምዩኔኬሽን ክፍሉ ውስጥ ፋይበር ኦፕቲክ ሽቦዎችን እየቀጠለች ነው። ፕሮጀክቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከግንባታው ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን ለመከታተል፣ ከሌሎች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ጋር ለመገናኘት እንዲሁም ከዋናው መሥሪያ ቤት የሚመጡ መመሪያዎችን ለመቀበል የኮምፒውተር ኔትወርክና ኢንተርኔት ያስፈልግ ነበር።

ሐምሌ 6, 2015—የቅርንጫፍ ቢሮው የግንባታ ቦታ

አንድ ሠራተኛ የጂፒኤስ መሣሪያ በመጠቀም ለምርምር የተቆፈሩ ጉድጓዶች የሚገኙበትን ርቀት እየለካ ነው። እነዚህ ጉድጓዶች ግንባታ ከመጀመሩ በፊት የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በአካባቢው ላይ ጥናት ማድረግ እንዲችሉ ይረዷቸዋል። ሮማውያን በአቅራቢያው በሚገኘው በቼልምስፎርድ ይኖሩ የነበረ ቢሆንም በዚህ ስፍራ ላይ በተደረገው የመጀመሪያው ጥናት ወቅት በተቆፈሩት 107 ጉድጓዶች ውስጥ ትኩረት የሚስቡ ጥንታዊ ዕቃዎች አልተገኙም።

ሐምሌ 6, 2015—ዋና ጣቢያ

የበር ክፈፎችን በልክ መቁረጥ። በዋናው ጣቢያ የሚገኙ አንዳንድ ሕንፃዎች በአዲስ መልክ ተሠርተው የጥገና ክፍል ወይም ወርክሾፕ እንዲሆኑ እየተደረጉ ነው። ጊዜያዊ ቢሮዎችና አንዳንድ አገልግሎቶች የሚሰጡባቸው ክፍሎችም በእነዚህ ሕንፃዎች ውስጥ ይሆናሉ።

ሐምሌ 6, 2015—ዋና ጣቢያ

የተቆፈሩትን ጉድጓዶች መልሶ ለመሙላት የሚውል አፈር በአንድ ከባድ መኪና ላይ እየተጫነ ነው።

ሐምሌ 7, 2015—የቅርንጫፍ ቢሮው የግንባታ ቦታ

የብሪታኒያ ገጠራማ አካባቢ 34 ሄክታር ስፋት ካለው የቅርንጫፍ ቢሮው የግንባታ ቦታ ደቡባዊ ክፍል ሲታይ። በአቅራቢያው ያለ አንድ አውራ ጎዳና (በፎቶው ላይ አይታይም) ዕቃዎችን ወደ ወደብ፣ ወደ አየር ማረፊያ እንዲሁም ወደ ለንደን ከተማ በቀላሉ ለማጓጓዝ ያስችላል።

ሐምሌ 23, 2015—የቅርንጫፍ ቢሮው የግንባታ ቦታ

ሠራተኞች ለአዲሱ ቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ አካባቢውን ነፃ ለማድረግ ሲሉ ቀድሞ የነበሩትን ሕንፃዎች እያፈረሱ ነው።

ነሐሴ 20, 2015—ዋና ጣቢያ

ስልሳ ቶን መሸከም የሚችል ክሬን የሚገጣጠም ተንቀሳቃሽ ቤት እያወረደ ነው። ፊት ለፊት በሚታየው አካባቢ ላይ ተጨማሪ ተንቀሳቃሽ ቤቶችን ለማስቀመጥ የሚያስችል መሠረት ተጥሏል። እነዚህ ቤቶች የግንባታ ፕሮጀክቱን ለማስተባበር የሚያገለግሉ ቢሮዎች ይሆናሉ።